የእለት ዜና

የማኅበራዊ ሥነ-ልቦና ቀውስ እና የአገራችን የፖለቲካ ግለት

ኩርት ሌዊን የተባለው የማኅበራዊ ሥነ-ልቦና ተመራማሪ እንደተናገረው፣ ማኅበራዊ ሥነ-ልቦና የሥነ-ልቦና ጥናት አንዱ ክፍል ሲሆን፣ እንዴት የግለሰብ ወይም የቡድን አስተሳሰብ በማኅበረሰቡ አመለካከት ተጽዕኖ ስር ይወድቃል የሚለውን የሚያጠና ሳይንስ ነው። ይህ ሳይንስ በርካታ ጠቀሜታ አለው። ማኅበረሰቡን በተሻለ ለመረዳት እና ቡድኖች ወይም የተወሰኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች በአንድ ሰው ምርጫ እና ውሳኔዎች ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ለመረዳት አይነተኛ ጠቀሜታ አለው።

ለፖለቲካ እንቅስቃሴ የግለስብ አስተሳሰብ፣ ዕምነት፣ ዕውቀት ወይም ስሜት ብዙም ጠቀሜታ እንደሌለው ምሁራን ይናገራሉ። ሪቸር ሐስላም እና ሬይኖልድ የተባሉት የማኅበራዊ ሥነ-ልቦና ተመራማሪዎች እንዳጠኑት፣ የቡድን ወይም የማኅበረሰብ አስተሳሰብና አመለካከት ለፖለቲካ አብዮት አዎንታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በአገራችንም የፖለቲካ እንቅስቃሴ እና አብዮት የቡድን፣ ከፍ ሲል የማኅበረሰብ አስተሳሰብ ተጽዕኖ ሥር ሲወድቅ እንጂ፣ የግለሰብ የፖለቲካ ዕምነት የጎላ ለውጥ ሲያመጣ አይስተዋልም። ይህ የሚያሳየው የማኅበራዊ ሥነ-ልቦና ከፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም ጋር ያለውን ቁርኝት ነው።
ታዲያ ግለሰብ እንደ የነጻ ፈቃድ ባለቤት የራሱን አስተሳሰብ፣ ዕምነት፣ ዕውቀት፣ስሜትና ችሎታ መግለጽ፣ ማንጸባረቅ ባልቻለበት ሁኔታ የአገራችንን የፖለቲካ ምህዳር ለሕዝቡ ምቹ ማድረግ ይቻል ይሆን ወይ? የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ግድ ይላል። ማንነትን ማረጋገጥ ወይም እራስን መረዳት የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ከኢትዮጵውያን የተነፈገ እስኪመስል ሁሉም በቡድን ማሰብን የተለመደ አድርጎ እየኖረበት እንደሆነ በርካታ የሥነ-ልቦና ባለሙያዎች በተለያየ ጊዜ ሲናገሩ ይስተዋላል።

አቶ መኮንን በለጠ በርካታ የሥነ-ልቦና ሥልጠናዎችን ለተለያዩ ግለሰቦች፣ለመንግሥት ሠራተኞች፣ እንዲሁም ለተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሠራተኞች በመስጠት የአስተሳሰብ ልክነትን እንዲላበሱ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። አዲስ ማለዳም የኢትዮጵያውያን የማኅበረሰብ የሥነ-ልቦና ቀውስን በተመለከተ አነጋግራቸዋለች።

እንደ አቶ መኮንን በለጠ ገለጻ ማኅበራዊ ሥነ-ልቦናን መረዳት፣ የሕብረተሰብን አስተሳሰብ፣ ግለሰብ ምርጫ ወይም ውሳኔ ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ለመረዳት ይረዳል። ከዛም ባለፈ፣ አንድ ሰው የሚኖርበትን ማኅበረሰብ መልካም ዕሴት ለመውረስ፣ የራሱ አድርጎ ለመተግበር እንደሚረዳው ተናግረዋል። ይሁን እንጂ እራስን አለማወቅና ነገሮችን አለማረጋገጥ፣ እንዲሁም የራስን አስተሳሰብ አዳብሮ ለማኅበረሰብ መግለጽ አለመቻል ትልቅ ጉዳት እንዳለው ጠቁመዋል።

እንደ አቶ መኮንን ገለጻ አብዛኞቹ ሠልጣኞቻቸው ላይ የሚያዩት ክፍተት፣ እራስን በትክክል ያለማወቅ ጉዳይ ነው። አክለውም እራስን ማወቅ በሥራና በትምህርት የበለጠ ውጤታማ ለመሆን፣ ፍላጎት ፣አቅም ፣ዓላማንና ግብን ለማሳካት ይጠቅማል። ራስን ለመግዛት፣ አገልጋይ ለመሆን ፣መልካምና ለጋስ ለመሆን፣ መሃሪና ይቅር ባይነትን ለመላበስ፣ እንዲሁም ከሰው ጋር ተስማምቶ ለመኖር ይጠቅማል። ራስን መቀበል ፣ድክመትን እና ጥንካሬን ተቀብሎ አቻችሎ ለመኖር እንደሚረዳ ያስረዳሉ። በራስ መተማመንን ፣የራስን አስተሳሰብ፣ ዕውቀት ክህሎትን ለማወቅና ለማውጣት እንደሚያግዝ፣ ከዚያ ባለፈም በራስ መተማመንን እንደሚያላብስ አቶ መኮንን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ከ1960ዎቹ የወጣቶች ተቃውሞ ጀምሮ እስክ አሁን ድረስ ያልተቋጨው ለውጥ የማምጣት እንቅስቃሴ ውጤታማነት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ያደረገው፣ በኅብረት የማሰብ፣ የአንድ ቡድን መሪ የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለምን እንደወረደ መቀበል እና እሱን ለማስፈጸም የመሮጥ አባዜ ውጤት እንደሆነ የሥነ-ልቦና ምሁሩ ይናገራሉ። አክለውም ይህ ሕዝብ ራሱን ያወቀ ቢሆን፣ የራሱን አስተሳሰብ እንዲመረምር፣ ተጨባጭ በሆነ መረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ እንዲሰጥ ፣ግጭትንና ንዴትን እንዲቀንስ፣ ከጭፍን ጥላቻ እንዲርቅ እና አዲስ የፖለቲካ ሐሳብ ሲመጣለት እንደወረደ እንዳይቀበል ይሆን ነበር በማለት የትውልዱን ክፍተት አሳይተዋል።

እራሱን የማያውቅ ሕብረተሰብ የራሱን መብት አያከብርም የሚሉት መኮንን፣ተጠራጣሪ ይሆናል። ከራሱ ፍላጎት ውጪ የሌሎችን ሐሳብ አስፈጻሚ ነው፤የራሱን ትክክለኛ ስሜትና ፍላጎት በመረጃ አስደግፎ መግለጽ ይሳነዋል። ሌሎች እናውቅልሀለን ሲሉትም ‹እሺ› ይላል። ሌሎችም እንዲያግዙት እሱ ከሚያወቀው ይልቅ አንድ የፖለቲካ መሪ እሱን ወክሎ የሚናገርለትን እንደ እውነት ይወስዳል።በዚህም አለመረጋጋት፣ በራስ አለመተማመን እንዲሁም ክፋት መገለጫዎቹ እንደሚሆኑ ለአዲስ ማለዳ በዝርዝር አስረድተዋል።

“እኔ አውቅልሀለሁ” ከሚለው ሐሳብ ጋር ተያይዞ አንድ ታሪክ ሲያካፍሉ፣ “አንድ ሰው ሚስቱን ሊፈታ ፈልጎ ለጠበቃው ይነግረዋል። ከሚስቱ ጋር መስማማት ስላልቻለ መፍታት እንደሚፈልግ ሲነግረው፣ ጠበቃውም በሚቀጥለው ቀን የፍቺውን ማመልከቻ አጠናክሮ እንደሚያመጣለት ቃል ገብቶ ይለያያሉ።ከዚያም በሚቀጥለው ቀን 5 ሙሉ ገጽ ደብዳቤ አምጥቶ ያነብለት ጀመር። ባልየው በጽሁፉ ርዝማኔ እና የሱን ሕመም፣ ጉዳት፣ ስቃይ እና በሚስቱ ሲበደል የቆየውን፣ አብሯት ሲኖር ሊሰማው አለመቻሉን የሚያሳይ በመሆኑ ከልቡ ለራሱ አዘነ። በዚህ ደረጃ መበደሉ እንደ እግር እሳት አንገብግቦት፣ ይህቺንማ መፍታት ሳይሆን መግደል ነው የሚያስፈልገው ብሎ ሊገድላት ሔደ” በማለት ከነባራዊው የፖለቲካችን ትኩሳት ጋር የተገለጸውን ታሪክ ለማያያዝ ሞክረዋል።

ሰው የራሱን ስሜት በግልጽ ማወቅ አለመቻሉ ፣ ሌሎች በራሳቸው የአስተሳሰብ መዘውር ውስጥ እንዲከቱት መንገድ ይከፍታል። በውጤቱም ያለፍላጎቱ ስህተት ውስጥ እንዲወድቅ ያደርጉታል በማለት “የኔ አውቅልሀለሁ” ፖለቲካን ትክክል አለመሆን አስረድተዋል።
ጆሴፍ ስታሊን በሩሲያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የሩሲያ ኮሚዩኒስት ፓርቲ መሪ ሆኖ የዘር ፖለቲካን አቀንቃኝ ነበር። በኢትዮጵያም በ1960 ዎቹ የፖለቲካ የተማሪዎች እንቅስቃሴ እና ተቃውሞ የስታሊንን የዘር ጭቆናን ፅንሰ-ሐሳብ የሚያቀነቅኑ መጻሕፍትን በማንበብ ትልቅ አብዮት ለመፍጠር የሚጥሩ የወቅቱ ወጣት ፖለቲከኞች የነበሩበት ጊዜ ነበር። ይሁን እንጂ የጆሴፍ ስታሊን የዘር ፖለቲካ ዉጤቱ ሩሲያን ከመበታተን የዘለለ ፋይዳ እንዳልነበረው የሚታይ ሐቅ ነው። ነገር ግን፣ በዘመኑ የነበሩ በርካታ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችን ያሳተ እንደነበር የአደባባይ ሐቅ እንደሆነ ምሁራን ይናገራሉ።

የማኅበራዊ ፖለቲካ ድርሻ በአግባቡ ሊተረጎም እና ሊተገበር እንደሚገባ በዘርፉ ያሉ ምሁራን ይናገራሉ። አንድ የፖለቲካ ሐሳብ ወይም ርዕዮተ-ዓለም ሲፈጠር፣ወጣቶች እንደወረደ ከመውሰድ፣ሒሳዊ አስተሳሰብን በመጠቀም መመርመር፤በጥልቀት ማየት ፣ከተለያየ የፖለቲካ ንድፈ ሐሳብ አንጻር መመልከት ይገባል።ከዚያ ባለፈ፣ ከአገራችን ነባራዊ የፖለቲካ እውነታ ጋር በማዛመድ መተንተን ያስፈልጋል ይላሉ የሥነ-ልቦና ባለሙያው መኮንን በለጠ።

ሒሳዊ አስተሳሰብ፣ “የሒሳዊ አስተሳሰብ መሠረት” በሚለው መጽሐፍ እንደተቀመጠው፣ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ማሰላሰል፣ በጥልቀት መመልከት፣በክሂል አሰላስሎ ፣በአመክኒዮ ሐሳቦችን መውሰድ ማለት ነው። የኢትዮጵያ ነባራዊ የፖለቲካ ችግር ምን እንደሆነ ማወቅ የመጀመሪያው ወደ መፍትሔ የሚያደርስ ጥያቄ ነው። የኢኮኖሚ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የዘር ጭቆና፣ ኢ-ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፣ ብዝኃነትን ያላማከለ የትምህርት ሥርዓት፤ ሥራ ዓጥነት፣ ሥልጣንን ለኪስ መሙያ መጠቀም፣ ሙስና፣ ወይስ ሌላ? የሚለውን በትትክክል መለየት ለለውጥ ወደሚውስደው ጎዳና እንደ ድልድይ ያገለግላል። ሒሳዊ አስተሳሰብ እዚህ ጋር እንደሚገባ መኮንን ይናገራሉ። አክለውም፣ በትክክል ወጣቱ የሰላ ሰብዕና ባለቤት ቢሆን፣ ሠላማዊና ለኹሉም የሚመች የፖለቲካ ዓውድ ይፈጠር እንደነበር ይናገራሉ።

አሁን የምትታየው ኢትዮጵያ ሠላማዊ፣ በዕድገት ጎዳና የምትራመድ፣ ልጆቿም እርስ በርስ የሚዋደዱ፣ በአመክኒዮ እንጂ በስሜት የማይነዱ ይሆኑ ነበር ይላሉ።ራስን ማወቅ ፣ማብቃት፣ ለራስ ጤነኛ ግምት መስጠትን መለማማድ አገርን ከጥፋት የሚያድን ትልቅ መፍትሔ እንደሆነ ምሁሩ ያሰምሩበታል። ራሱን ያላወቀ ሰው የሌሎችን መብት በመድፈር የራሱን ሕጋዊ ጥቅም ያስከብራል።የሌሎችን ሐሳብ እና ስሜት ከመረዳት ይልቅ እኔን ብቻ ስሙኝ ባይነት ያዘወትራል። ጮሆ በመናገር ሌሎችን መዝለፍ፣ መወንጀል ፣መውቀስና መናቅ ይታይበታል። ራሱን የበላይ አድርጎ ይቆጥራል። የራሱን ጥቅም ለማስከበር ሲል ሌሎችን ይጎዳል። በጥላቻና በፍርሀት ላይ የተመሠረተ ብቀላ ውስጥ ይገባል በማለት ለአዲስ ማለዳ ባለሙያው ያስረዳሉ።

ለራሱ ጤነኛ ግምት ያለው ወይም ራሱን ያወቀ ሰው ፣የሌሎችን መብት በማክበር የራሱን ሕጋዊ ጥቅም ያስከብራል። ራሱን ከሌሎች ጋር በእኩል ያያል፤ያከብራል፤ ይወዳል፤ በሚያቅደው ዕቅድ ኹሉ ውጤታማ ይሆናል። ዕቅዱን ለማሳካት ይሠራል፤ በራሱም ይተማመናል፤ በግብታዊነት አይናገርም፤ ግልጽ፣ቀጥተኛና ለራሱና ለሌሎችም ታማኝ ነው። ተፈላጊና የተከበረ ነው፤ ችግርን የመፍታት አቅሙ ትልቅ ነው፤ ራሱን ያከብራል፤ በራሱ ይተማመናል፤ ሌላውን ለመውደድ ችግር የለበትም፤ ከምቀኝነትና ከጭፍን ጥላቻ ይርቃል፤ ተጨባጭ በሆነ መረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ይሰጣል፤ ግጭትን ማስወገድ ይችላል፤በማለት ምሁሩ እራስን የማወቅን ጥቅም ያስረዳሉ።

በመጨረሻም ራስን ማወቅና መረዳትን ትውልዱ እንዴት ሊያመጣው እንደሚችል ሲየስረዱ፣ የሰው ልጅ በሒደት የሚለወጥ ባህሪ ያለው ማኅበራዊ እንስሳ በመሆኑ ፍላጎት፣ ጥረት እና ቅንነት ካለ የማይለወጥ ባህሪ አለመኖሩን በአጽንዖት ይገልጻሉ። ማንበብ ዋነኛው ራስን የማወቂያ መንገድ መሆኑን ያስረዳሉ። ማንበብ የተሻለ አስተሳሰብ ባለቤት ያደርጋል፤ ሌሎች ሐሳባቸውን ሊጭኑ ሲፈልጉ አለመቀበልን ያስተምራል። ኹሉም አስተሳሰብ ትክክል ነው ማለትን ያስተዋል፤ ነገሮችን በጥልቀት የመርመር ብቃትን ያላብሳል፤ ለችግሮች መፍትሔ ሰጪ ያደርጋል። ግለሰባዊ፣ ቤተሰባዊ ፣ማኅበራዊና አገራዊ ኃላፊነትን የመወጣት ብቃትን ያላብሳል። በመጨረሻም ራስን ለመረዳት ፣አካባቢን ለመረዳት፣ እና የሰዎችን አስተሳሰብ ለማወቅ ይረዳል በማለት መኮንን በለጠ ሐሳባቸውን ያጠቃልላሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 158 ሕዳር 4 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com