አመሻሽን ተገን ያደረጉ የኪነ ጥበብ ድግሶች

0
788

የአዲስ አበባ ምሽቶች፤ የመጠጥ ቤቶች ማለዳ እንዲሁም ጭፈራ ብቻ የሚስተናገድባቸው መሆንን ከተዉ ከራርመዋል። ከፖለቲካ ይልቅ ማኅበረሰብ ላይ ለውጥ ማምጣትና ተጽዕኖ መፍጠር እንደሚቻላት የሚነገርላት ጥበብ በተለያዩ ሥያሜና ክዋኔዎች ምሽቶቹን ተጋርታለች። ከቴአትርና ሲኒማ ቤቶች ውጪ፤ ወጣቶች ሰብሰብ ብለው በትልልቅ አዳራሽ በሮች ላይ ጥበባዊ ክዋኔን ለመታደም ሲጠባበቁ ማየት እየተለመደ ነው። ያሳለፍነውን ሰኞና ማክሰኞን እንደማሳያ ብንጠቅስ እንኳ ብራና ግጥም በጃዝ እንዲሁም ጦብያ ግጥም በጃዝ የተባሉ ክዋኔዎችን እናገኛለን።

በእነዚህ ክዋኔዎች መታደም የቻለችው አዲስ ማለዳ አዳራሽ የሞላውን ታዳሚ እንዲሁም ለቀረቡ ዝግጅቶች ያለውን ግብረ መልስ መታዘብ ችላለች። በአማካይ አንድ መቶ ብር በሚከፈልባቸው እነዚህ ዝግጅቶች ላይ ታዳሚዎች ሳያንገራግሩ፣ የሚያደንቁና የሚያከብሯቸውን ሰዎች ለማየትና ለመስማት በመጓጓት፤ አዲስ ነገር ለማግኘት በአዳራሽ በሮች ላይ ከጥሪው ሰዓት ቀድመው ይገኛሉ። ይህ ከክዋኔዎቹ የወደዱት አንዳች ነገር እንዳለ ያሳብቃል። አዲስ ማለዳ ደግሞ ጠየቀች፤ “እነዚህ ጥበባዊ ክዋኔዎች ምን ፋይዳ አላቸው?” በዛውም ስለክዋኔዎቹ ጠቅላላ ገጽታ ከአዘጋጆች እንዲሁም የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎች ሐሳቦችን ተቀብላለች።

ብራና ግጥምን በጃዝ ከወራት በፊት በምንገኝበት ዓመት ቀዳሚው ወር መስከረም ላይ እንደተጀመረ አዘጋጁ ጋዜጠኛ በፍቃዱ ዓባይ አስታውሷል። ዝግጅቱ ሲጀመርም ቀድመው ከሚካሔዱት በተለየ በየወሩ በሚደረገው መርሃ ግብር አንድ ርዕሰ ጉዳይ መምረጥና ሥራዎች በዛ ዙሪያ እንዲሆኑ ማድረግን ይዞ ነበር። መነሻውም ኪነ ጥበብ በሁሉም አገራዊ ጉዳይ ላይ ሚና ሊኖራት ይገባል የሚል ነው።

በፍቃዱ በበኩሉ በቀደሙ መድረኮች ካያቸውና ቢሆን የሚመኛቸውን በማካተት ብራን ግጥም በጃዝን እውን እንዲሆን አድርጓል። በኪነ ጥበብ መድረኮች ያልተለመዱ የነበሩና በተለያየ ሙያ ላይ የሚገኙ ሰዎችን ለንግግር መጋበዝም በክዋኔው ተካትቷል። ታድያ እንደ በፍቃዱ ገለጻ እነዚህ ዝግጅቶች ለሥነ ጽሑፍ ወይም ለኪነጥበብ ብቻ ሳይሆን ፋይዳቸው ለአገር ነው።

በተለይም ሰዎች የሚቀበሉትንም ሆነ የማይቀበሉትን ሐሳብ ቁጭ ብለው ማድመጥ እንዲችሉና ነገሮችን በተለያየ አንጻር እንዲመለከቱ ያስችላል ባይ ነው። “በዚህም ኪነ ጥበብ ተከታይ መሆኗ ቀርቶ ወደ መሪነት ትሻገራለች” ሲልም ይገልጻል። የክዋኔው ሐሳብም ኪነ ጥበብ ላይ በተለየ ለውጥ ለማምጣት ሳይሆን አገር ላይ ለውጥ ማምጣት ነው።

በሙያው ጋዜጠኛ የሆነው ጌታቸው ዓለሙ ‘ሰምና ወርቅ’ የተሰኘ ወርሃዊ ኪነ ጥበባዊ ምሽት ያዘጋጃል። የዚህ ክዋኔ አጀማመር ደግሞ ከቀደመው በተለየ በአዲስ አበባ አማራጭ የመዝናኛና የቁም ነገር ምሽት መሆን ነው። አልፎም መድረክ ያላገኙ አዳዲስ የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎች ዕድል አግኝተውበታል። ጌታቸው እንዳለውም በቅርቡም በመድረኩ ላይ የቀረቡ ሥራዎችና ሌሎች የገጣምያኑ ሥራዎች በመጽሐፍ መልክ ለአንባቢ ይደርሳሉ።

ኪነ ጥበብ የማይነካው ነገር የለምና፤ እንደቀደመው ሁሉ በዚህም መድረክ አገራዊ የሆኑ ጉዳዮች ሁሉ ይነሳሉ። ታድያ የእነዚህ ጥበባዊ ክዋኔዎች ፋይዳን በሚመለከት ጌታቸው ሲናገር፤ በአንድ በኩል ብዙ ገጣምያን እንዲጽፉ ማነሳሳት አስችሏል ይላል።

ከዛም ባሻገር ሰዎች በሬድዮን እና በትዕይንተ መስኮቶች (‘ቴሌቪዥን’) ብቻ ያይዋቸው የነበሩና የሚያደንቋቸውን ሰዎች በአካል ለማግኘት፣ ሐሳባቸውን ለማካፈልና ለማነጋር ትልቅ ዕድል መፍጠሩንም አስታውሷል። አልፎም አሁን ላይ ለመመረቂያ ጽሑፍ ግብዓት እየሆኑም ነው። ጌታቸው “ጥናት የሚፈልግ ቢሆንም ለዘርፉ ትልቅ አስተዋጽዖ አድርጓል” ብሏል።

እነዚህን አዲስ ማለዳ እንደማሳያነት ያነጋገረቻቸው የክዋኔዎቹ አዘጋጆች የሚጋሯቸው ሐሳቦች ደግሞ አሉ። በአንድ በኩል የኪነ ጥበብ ምሽቶች እየተነገደባቸው ነው ከሚለው ሐሳብ አንጻር ነው። ብዙ እንቅስቃሴዎች በራስ ተነሳሽነት ሳይሆን “ያዋጣል” ተብሎ በሚገባት ጊዜ ላይ በዚህ መልክ ሊታዩ የሚችሉ ሁኔታዎች እንዳሉ አዘጋጆቹ ገልጸዋል። ነገር ግን ወረቱን አልፈው መዝለቅ የሚችሉት ጥቂቶች ናቸው።

ደግሞም ልፋት ያለው ሥራ መሆኑን ኹለቱም ጠቅሰዋል፣ ከፍ ሲልም በአዲስ አበባ ከተማ ክዋኔዎች በዝተዋል ቢባል እንኳ ካለው ሕዝብ አንጻር ያሉትም እዚህ ግባ የሚባሉ እንዳይደሉ ጠቁመዋል። የቦታ እጥረት፣ በገንዘብ በኩል ደጋፊ ማጣት፣ ሥራዎቻቸውን ለማስደመጥ፤ ሐሳባቸውንም ለማካፈል ፈቃደኛ የሆኑ አቅራቢዎችን እንደልብ ባለማግኘት ምክንያት ተመሳሳይ ሰዎችን በተደጋጋሚ ለማስተናገድ መገደድና የመሳሰሉት ደግሞ እንደተግዳሮት የጠቀሷቸው ናቸው።

ከዚህም ባሻገር መድረኮቹ ወቅታዊ ክስተቶች ላይ ከማተኮራቸው ጋር ተያይዞ፤ ለጉዳዮቹ ትኩረት መስጠቱ ቅድሚያ ለሚገባው ቅድሚያ መስጠት ስለመሆኑ አዘጋጆቹ ገልጸዋል። እንደውም በፍቃዱ በንግግሩ “እንደአገር ቅድሚያ የምንሰጣቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች አሉ። የመፍትሔ ሐሳብ እንዲቀርብባቸውና መነጋገሪያ እንዲሆኑ ወደ መድረክ ልናወጣቸው ይገባልና ነው” ብሏል።

በተመሳሳይ ጌታቸውም ሰው ይተነፍስበት ከኪነ ጥበብ ውጪ ሌላ መሣሪያ የለውም ይላል። ፖለቲከኞች ራስ ወዳድ በሆኑበት ጊዜም ጉዳዮች ላይ በግልጽ ለመነጋገር ከኪነ ጥበብ ውጪ ማን ሊመጣ ነው ሲል ይጠይቃል። “በእነዚህ መድረኮች የአገር ችግር የእኔ ነው ብለው የሚያስቡ ሰዎች ከነሕመማቸው አይቀመጡም፤ ይተነፍሳሉ” ሲል ገልጾታል።

ይህ ግን በትውልድ ላይ ስሜታዊነት በመፍጠር ሳይሆን፤ መፍትሔ አመላካች በመሆን ነው። ብዙ ለነፃነት የሚታገሉ የነበሩ ሰዎች አገር ጥለው ሲሸሹና ሲሰደዱ፤ ባሉበት በአቅማቸው እየተጋፈጡ ያሉት ግን የኪነ ጥበብ ሰዎች ናቸው። እናም የፖለቲካ ጉዳዮ እንዲሁም በጠቅላላው ወቅታዊ የማኅበራዊ ጉዳዮች መነሳታቸው በምክንያት እንደሆነ ነው አዘጋጆቹ በተመሳሳይ የገለጹ።

በኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር የጥበብ እልፍኝ ሬድዮ ፕሮግራም ላይ የሲሳይ ዳሰሳ አዘጋጅ በመሆን ከአራት ዓመታት በላይ አገልግሏል፤ ደራሲ ገዛኸኝ ሀብቴ። እርሱ በበኩሉ የግጥም ወይም የኪነ ጥበብ ምሽቶች ያበረከቱትን አስተዋጽዖ ለመዘርዘር ጥናት እንደሚያስፈልግ አጠንክሮ ይጠቅሳል። ይሁንና ግን ስምንት ዓመታት ካስቆጠረው ጦብያ ግጥምን በጃዝ አንስቶ በቅርቡ እስከተነሱት ድረስ፣ ጊዜው ረጅም በመሆኑ ብዙ የፈጠሩት ለውጥ እንዳለ ይገልጻል። ለምሳሌም የዚሁ የጥበብ ምሽት ውጤት የሆነውንና በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነት ያለው “እያዩ ፈንገስ” የአንድ ሰው ቴአትርን ይጠቅሳል።

ታድያ የእነዚህ ክዋኔዎች አስተዋጽዖ ለሥነ ጽሑፍ ተለይቶ የሚታይ ሳይሆን በጠቅላላው ኪነ ጥበብን የሚያካትት ነው። ይህም እነዚህ ክዋኔዎች ሙዚቃን፣ ተውኔትን፣ ዲስኩርና ወዘተ የመሳሰሉትን ያካትታሉና ነው። በተጨማሪም መድረኮቹን የፈጠሩት የኪነ ጥበብ ሰዎች ይገኛሉ፤ በዛው ልክ የደከሙት እንዳሉ ሆነው ማለት ነው።

ግጥምን በጃዝ በሚል መጠሪያ በሚታወቁ ክዋኔዎች ላይ የሚቀርቡ ሥራዎችን በተመለከተ፤ ምሽቶቹ የግጥም ብቻ እንዳይደሉ ገዛኸኝ ይጠቅሳል። እንደውም በአንዳንዶቹ መድረኮች ከግጥሙ ይልቅ ዲስኩር ሲበዛም እንደሚታይ ያነሳል። አልፎም ግጥሞቹ በዜማ ሲታጀቡና የሚቀርቡት ማጀቢያ ዜማዎች ደግሞ የተለመዱና የተወደዱ ሲሆኑ፣ ከግጥሙ ይልቅ ሰው ትዝታውን የማዳመጥ ዕድሉ ሲለሚጨምር፤ ታዳሚ በዜማው እየተደለለ ግጥሞችን ሳያደምጥ እየቀረ እንዳይሆን እንደባለሙያ ሥጋቱን ገልጿል።

መድረኮቹ በአንድ ጊዜ ነጻነታቸው ለታፈነ ሁሉ ድምጽና መተንፈሻ በመሆን ማገልገላቸውን የሚጠቅሰው ደራሲ ገዛኸኝ፤መድረኮቹና የሚቀርቡ ሃሳቦች ብዙውን ጊዜ በአገራችን እጦቶችና ሰቀቀኖች ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው ወቅታዊ ጉዳይ አጥተው ሊቀዛቀዙ እንደማይችሉ እምነቱን ይናገራል። በዚህም መሰረት ቀደም ባለው ጊዜ በእነዚህ መድረኮች ሕዝብ የጎደለውና ያጣው በተለያየ ኪነጥበባዊ መንገድ ሲተነፈስ ቆይቶ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ መንግሥት አጣሁት ያለው እየተንጸባረቀ መሆኑን ጠቆም አድርጓል።

ቅጽ 1 ቁጥር 37 ሐምሌ 13 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here