የእለት ዜና

አባቴ በመንገዱ አልመራኝም

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

“የኔ ልጅ የቆንጆዎች ሁሉ ቀንዲል ንግሥት ናት፤ ከሴቶች ሁሉ የተለየ ውበት አላት፤ በውበቷ ብቻ ዓለም ይደመምባታል፤ ከልጅነት እስከእውቀት ስሰማው የነበረው፣ አባቴ ስለውጫዊ ውበቴ የሚሰጠኝ አስተያየት ነው።” ትእግስት ይማም ትባላለች(ስም ተቀይሯል)። የካቲት ሆስፒታል እናቴን ሳስታምም፣ እሷም ለአንድ ሳምንት አልጋ ይዛ ታማ በነበረችበት ወቅት ያጫወተችኝ ታሪክ ነበር። ሆስፒታል በተኛችበት ጊዜ፣ ምንም እንኳን ፊቷ በሕመም ምክንያት ቢጠወልግም፣ ቁንጅናዋን ግን ሊደብቀው አልቻለም። ታዲያ ትእግስት አባቷን አሁን ላለችበት ምስቅልቅል ሕይወት ምክንያት ስለሆናት አምርራ ትጠላዋለች።

አባቷ ያለእናት ነበር ያሳደጋት። ይሁን እንጂ፣ ልጁን በሥነ-ምግባር እና በትምህርት የበረታች እንድትሆን ከማድረግ እና በላቀ የቤተሰብ ፍቅር ከማሳደግ ይልቅ፣ የውጪ ውበቷን በማድነቅ፣ ቁንጅናዋ ወደከፍታ የሚያወጣት መሰላል አድርጎ በመቁጠር ፣ ሲያንቆለጳጵስ ነው ያሳደጋት። ትእግስት ይሄንን በራሷ ጥረት ባላገኘችው ውጫዊ ውበት ስትኮፈስ፣ ሌሎች የሕይወት ተልዕኮዎቿን በቅጡ ባለመወጣት ለአቅመ ሔዋን ደረሰች። ውበቷ ሁሉን የሚያማልል ስለነበረ፣ ተከታዮቿ በርካቶች ነበሩ፣በተለይ ወንዶች። ይሁን እንጂ ወንዶች ከጊዜያዊ ፍላጎት ውጪ ለቁም ነገር የሚፈልጓት አልነበሩም። በመጨረሻ ዕድሜዋ 25 ሲሞላ ከቤት በመጥፋት የቡና ቤት ሴት ሆነች። ከአባቷ ጋር ለ 8 ዓመት ሳይተያዩ ቆይተው ለሕመም ተዳረገች።

ታሪኳን ትቀጥላለች፣ “አባቴ ልጅን እንዴት ማሳደግ እንዳለበት አልገባውም። እኔን የጠቀመ መስሎት፣ በጥረቴ ባላመጣሁት ውበት ብቻ እንድመካ ፣ ለትምህርት እና ለሙያ ዋጋ እንዳይኖረኝ በማድረጉ ለጉዳት ዳረገኝ” በማለት በሀዘን ትናገራለች።
እዚህ ጋር አንድ ነገር ማስተዋል ግድ ይላል፣ ልጆች የቤተሰብ ማቆሚያ ዋልታዎች ናቸው። ሲያድጉ ደግሞ የአገር ካስማ በመሆን ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት አገርን ለትውልድ ያስተላልፋሉ።ልጅን በጥበብ እና በዕውቀት ማሳደግ ካልተቻለ፣ ለራሱ፣ ለቤተሰቡም ፣ ከፍ ሲል ደግሞ ለአገሩ የማይጠቅም ይሆናል።

ውበት፣ ቁስ፣ ገንዘብ፣ ወዘተ. ሕልውናቸው በጊዜ እና በቦታ የተወሰኑ ናቸው። ሁልጊዜ ከሰው ልጅ ጋር አብሮ ሊቆይ የሚችሉት፣ ዕውቀት እና መልካም ሰብዕና ናቸው። በታሪኩ ፣ የትእግስት አባት ልጁን እንደ ጠዋት ጀንበር ታይቶ ለሚጠፋው ውበት ትኩረት እንድታደርግ እና ቁንጅናዋ ብቻ ወደስኬት ማማ ሊያወጣት እንደሚችል እየነገረ አሳደጋት። በኋላ ግን ውጤቱ መጥፎ ሆነ። ቤተሰብ ልጁን ሲያሳድግ፣እጅግ በጣም ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት የትእግስት ታሪክ ምስክር ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 159 ሕዳር 11 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com