የእለት ዜና

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ ለአስቸኳይ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት የሚውል 40 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን አስታውቋል

የተባበሩት መንግሥታት የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ማስተባባሪያ ጽ/ቤት (ኦቻ) በኢትዮጵያ ሕይወት አድን የሰብዓዊ ዕርዳታዎችን ለማከናወን እና ንጹኅን ዜጎችን ለመጠበቅ ከማዕከላዊ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ፈንድ 25 ሚሊዮን ዶላር መመደቡ ተነግሯል።
እንዲሁም ከዚህ የሰብዓዊ ዕርዳታ ፈንድ በተጨማሪ፣ 15 ሚሊዮን ዶላር የቀረበ ሲሆን፣ በዚህም በጠቅላላው በኢትዮጵያ ለሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት 40 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚሆን ነው የተገለጸው።
በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች የሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲጠብቁ እንዳስገደዳቸው የመንግሥታቱ ድርጅት አስታውቆ፣ ዕርዳታው የሚፈልጉ ዜጎች አኃዝም 7.1 ሚሊዮን መሆኑን ገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሰብዓዊ ዕርዳታ የ40 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን ይፋ ባደረገበት ወቅት፣ ሰብዓዊ ቀውስ እየተስፋፋ በሔደበት በሰሜን ኢትዮጵያ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መራር ሕይወትን እየገፉ ነው ሲል ጠቁሟል።
በመንግሥታቱ ድርጅት የተመደበው ገንዘብ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች በግጭቱ ምክንያት ለተጎዱ ጥበቃ እና ሕይወት አድን ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚረዳ ሲሆን፣ ገንዘቡ በጦርነት ለችግር ተጋላጭ ከሆኑት በተጨማሪ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች በድርቅ የተጎዱትን ለመደገፍ እንደሚውልም ተመላክቷል።
በተጨማሪም በመላው ኢትዮጵያ ለሰብዓዊ አቅርቦት የሚደረገው ጥረት ለመደገፍ 1.3 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ዕጥረት እንደገጠመው ተመድ አስታውቋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 159 ሕዳር 11 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!