የእለት ዜና

የዋግ ኽምራ ተፈናቃዮች አስቸኳይ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተነገረ

በአካባቢው በነበረው ጦርነት ምክንያት ተፈናቅለው ከነበሩት የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ነዋሪዎች መካከል ከ85 ከመቶ የሚሆኑት ወደ ብሔረሰብ አስተዳደሩ ቢመለሱም አስፈላጊው የምግብ ዕርዳታ እየደረሳቸው አይደለም ተብሏል።
ከነሐሴ 2013 መጀመሪያ ጀምሮ ህወሓት በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ወረራ በመፈጸሙ ከ60 ሺሕ በላይ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ነዋሪዎች ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተፈናቅለው እንደነበር የብሔረሰብ አስተዳደሩ መረጃዎች ያመላክታሉ።
አሁን በወረራ ተይዘው የነበሩ ኹሉም ባይሆኑም አንዳንድ አካባቢዎች ነጻ በመውጣታቸው ከ85 በመቶ በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች ወደ ብሔረሰብ ዞኑ ዳህና ወረዳ በመመለስ ላይ መሆናቸው ተነግሯል።
ነገር ግን ለተፈናቃዮቹ ከአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገላቸው እንዳልሆነ ተሰምቷል።
በአማራ ክልል የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት በበኩሉ፣ መንግሥት በሚያውቀው መልኩ ከዘንዘልማና እብናት መጠለያ ጣቢያዎች ከ33ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች ወደ ዋግ ኽምራ መመለሳቸውን እና የዘገዬ ቢሆንም ዕርዳታ እየተጓጓዘ አንደሆነና 108 ኩንታል እህል ወደ ቦታው መጫኑን ገልጿል።
አሁንም የህወሓት ኃይሎች ከብሔረሰብ አስተዳደሩ ጨርሰው ባለመውጣታቸው በኃይል በያዟቸው ወረዳዎች ያለው ሕዝብ ለከፋ ርሀብና መጎሳቆል እየተጋለጠ በመሆኑ ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ተቋማት አሁንም ለእነዚህ ወገኖች እንዲደርሱ በብሔረሰብ አስተዳደሩ በኩል ጥያቄ መቅረቡ ተመላክቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 159 ሕዳር 11 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com