የእለት ዜና

ከቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርቶች 91.46 ሚሊዮን ዶላር ተገኘ

በጥቅምት ወር ውስጥ ለውጭ ገበያ ከቀረቡ የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርቶች 91.46 ሚሊዮን ዶላር እንደተገኘ ተገልጿል።
ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ገቢው የ44.41 ሚሊዮን ዶላር እና የ94.39 በመቶ ጭማሪ እንዳስመዘገበ ነው የተነገረው።
በዚህም በ2014 በጄት ዓመት ጥቅምት ወር 22,444.06 ቶን የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርት በመላክ 71.74 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 23,694.18 ቶን (ከዕቅዱ 106 በመቶ) በመላክ 91.46 ሚሊዮን ዶላር (ከዕቅዱ 127 በመቶ) ገቢ እንደተገኘ ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
አፈጻጸሙ ባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወር ከተላከው ጋር ሲነጻጸር በመጠን 8,782.57 ቶን (58.9 በመቶ) እና በገቢ 44.41 ሚሊዮን ዶላር (94.39 በመቶ) ጭማሪ ተመዝግቧል።
በበጀት ዓመቱ አራት ወራት 97,144.42 ቶን የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርት በመላክ 317.44 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 112,614.84 ቶን (ከዕቅዱ 116 በመቶ) በመላክ 425.0 ሚሊዮን ዶላር (ከዕቅዱ 134 በመቶ) ገቢ መገኘቱንም ለማወቅ ተችሏል።
በ2014 በጀት ዓመት አራት ወራት የተላከዉ ቡና በመዳረሻ አገራት በገቢ ሲታይ ደግሞ ጀርመን በመጠን 27,874.10 ቶን (26 በመቶ) ድርሻ እና በገቢ 90.85 ሚልዮን ዶላር (22 በመቶ) ድርሻ፣ ሳዑዲ አረቢያ በመጠን 15,928.77 ቶን(15 በመቶ) ድርሻ እና በገቢ 53.40 ሚሊዮን ዶላር (13 በመቶ ) ድርሻ፣ እንዲሁም ቤልጅየም በመጠን 11,023.14 ቶን (10 በመቶ) ድርሻ እና በገቢ 46.43 ሚሊዮን ዶላር (11 በመቶ) ድርሻ አፈጻጸም በማስመዝገብ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃን ይዘዋል ነው የተባለው።
በ2014 ከ 4ተኛ እስከ 10ኛ ያሉትን ደረጃዎች በገቢ ቅደም ተከተል ደግሞ አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጣልያን፣ ቻይና፣ ፈረንሣይ እና ታይዋን የያዙ ሲሆን ከ1 እስከ 10 ያሉት አገራት አጠቃላይ በመጠን 83 በመቶ እና በገቢ 82 በመቶ ይሸፍናሉ። በጥቅሉ የእነዚህ ዋና 10 መዳረሻ አገራት ከ2013 አፈጻጸም ጋር ሲወዳደር በመጠን 77 በመቶ እና በገቢ 94 በመቶ ጭማሪ ማሳየታቸው ተገልጿል።


ቅጽ 4 ቁጥር 159 ሕዳር 11 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com