የእለት ዜና

በአፋር የተካሄደው ተደጋጋሚ ውጊያ ሲዳሰስ

በሐምሌ 2013 የመጨረሻዎቹ ቀናት፣ በአፋር ክልል ዞን 4 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፣ በጋሊኮማ የገጠር ጤና ጣቢያ ላይ በተፈጸመ የከባድ መሣሪያ ጥቃት ከቀያቸው ተፈናቅለው በቦታው የተጠለሉ በርካታ ዜጎች ለሞት እና ለጉዳት መዳረጋቸውን በወቅቱ የክልሉ ባለሥልጣናት ገልጸው ነበር። በወቅቱ የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አሕመድ አሎይታ የተፈናቀሉ ሰዎች ላይ ጥቃት የፈጸሙት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ህወሓት ኃይሎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

የህወሓት ቡድን በፈንቲ ረሱ በኩል ጥቃት በመክፈቱ ምክንያት ከያሎና ጎሊና ከ30 ሺሕ በላይ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን በመተው በዚህ መጠለያ ጣቢያ እንደሚገኙ አሕመድ አሎይታ ጠቁመው ነበር። መንግሥት በሰኔ ወር 2013 ማገባደጃ የተናጥል ተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል ካስወጣ በኋላ የህወሓት ኃይሎች በአማራና አፋር ክልል ላይ ጥቃት መፈጸም ጀመሩ። በወቅቱ የህወሓት ቡድን በአፋር በኩል አልፎ ጦርነቱን አማራ ክልል ላይ ለማድረግ ጥረት ቢያደርግም፣ የአፋር ክልል መንግሥትና ሕዝብ ሊፈቅድላቸው ባለመቻሉ ምክንያት በጋሊኮማ ከ200 በላይ ተፈናቃይ ዜጎች ያለቁበትን ጥቃት መፈጸማቸውን ኃላፊው ተናግረዋል። በጥቃቱ ሰለባ ከሆኑት መካከል በርካታ ሕፃናትና ሴቶች ይገኙበት እንደነበር ያታወቃል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ከ200 በላይ ንጹኃን በህወሓት ጥቃት ያለቁበትን ክስተት አውግዞ እንደነበር አዲስ ማለዳ በወቅቱ ዘግባ ነበር።

ህወሓት ጋሊኮማ ላይ ከፈጸመው አሰቃቂ ጭፍጨፋው በኋላ ይህ ዜና እሰከተዘገበበት ጊዜ ድረስ በአፋር ክልል፣ በተለያዩ አቅጣጫዎች ፣ ከ 7 ጊዜ በላይ ጥቃት ለመፈጸም ቢሞክርም እንዳልተሳከለት የክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዋና አሰተባባሪ አሕመድ ኑር ሳሊ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ዋና አሰተባባሪው እንዳሉት፣ የህወሓት ጥቃት ለመጀመሪያ ጊዜ የተጀመረው በያሎ በኩል መሆኑን ጠቅሰው፣ የህወሓት ቡድን ከአፋር ሕዝብ ጋር ምንም ዓይነት ግጭት እንደማይፈልግ ፣ አፋርና ትግራይ አንድ መሆናቸውን፣ ጸብ ያለውም ከመንግሥት እና ከአማራ ጋር ብቻ መሆኑን በመግለጽ መንገድ እንዲከፈትለት ጠየቀ። የክልሉ መንግሥትና ሕዝብም በምላሹ ኢትዮጵያን ለሚወጋ ቡድን መንገድ ሊከፍቱ እንደማይችሉ አስረግጠው ስለነገሩት፣ ጥቃቱን በያሎ በኩል ጀምሮ ኡዋንና አውራን ህወሓት ተቆጣጠረ። የአፋር አርብቶ አደር እና ልዩ ኃይል ያለምንም የመንግሥት ድጋፍ፣ እጁ ላይ በነበረው መሣሪያ ህወሓትን በመመከት ወደመጣበት ሊመልሰው ችሏል።በዚህ ቂም ምክንያት፣ የህወሓት ቡድን፣ በጋሊኮማ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የተጠለሉ ንጹኃን ዜጎችን በግፍ ጨፍጭፏል ሲሉ አስተባባሪው ገልጸዋል። በግድያውም ከ200 በላይ ንጹኃን አፋሮች በግፍ አልቀዋል።

በመቀጠል፣ ዞን 4 አካባቢ ህወሓት ኡዋና ጭፍራ ላይ ሌላ ጥቃት ጀመረ። አሁንም የአፋር ሕዝብ ሉዓላዊነቱን ለማስጠበቅ እልህ አስጨራሽ ውጊያ ካደረገ በኋላ በርካታ ታንኮች እና የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን ከህወሓት ሊማርክ ችሏል። የአፋር ሕዝብ በአንድነት ትኩረቱን ሙሉ ለሙሉ እዚሁ አካባቢ በማድረጉ የህወሓት ኃይል አቅጣጫ ቀየረ። ለሦስተኛ ጊዜ በበረሐሌ በኩል፣ ህወሓት የሀብትና የመሬት የቆየ ጥያቄም ስለነበረው እሱን አስታኮ፣ ሕፃናትና ወጣትን በመድፍ በመደብደብ በርካቶችን ገደለ። በምላሹ፣ የበረሐሌ ነዋሪ፣ በከፍተኛ ቁጭትና እልህ፣ እጁ ላይ በነበረው ጦር መሣሪያ፣ መንግሥትን ሳይጠብቅ ህወሓትን ደምስሶ በርካታ የጦር መሣሪያዎችን፣ የመገናኛ ቁሶችን፣ ታንኮችን፣ የቡድኑ አባላትን፣ ወዘተ. በመማረክ ቦታውን መልሶ ተቆጣጠረ። በዚህ ውጊያ በርከት ያሉ የህወሓትን ወታደሮች መማረካቸውን ባለሥልጣኑ ተናግረዋል።

የበረሐሌ ከተማ ነዋሪዎች የተለያዩ ቀጠናዎችን በመያዝ ህወሓት ላይ ድል ተቀዳጁ። ከዚያም በህወሓት የተያዙት ቦታዎችን አስለቅቀው በማለፍ ወደ ህወሓት ቀጠና ሊገቡ ቻሉ በማለት፤ የአፋርን አልበገር ባይነት እና አትንኩኝ ባይነትን በዝርዝር አስረድተዋል። በመቀጠል፣ ህወሓት ወራሌ የምትባለውን አነስተኛ የገጠር ከተማን ለመቆጣጠር እና በቆረጣ ለመግባት ቢሞክርም፣ የከተማው ነዋሪዎች ኃይላቸውን አስተባብረው ስለመከቱት በመጣበት ሊመልስ እንደቻለ ገልጸዋል። የተማረኩት የህወሓት ወታደሮች በተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንደነበሩ፣ ረሀብ እና እንግልት እንዳጎሳቆላቸው፣ ከሰውነታቸው እና ከአጠቃላይ ሁኔታቸው መረዳት ይቻላል ብለዋል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስተባባሪ።

እንደ አሕመድ ኑር ሳሊ አያይዘውም፣ የአፋር ሕዝብ ኢትዮጵያን ሊያፈርሱ ቀን ከሌሊት ከሚሠሩ ኃይሎች ጋር በምንም መልኩ መደራደር የሚችልበት ነባራዊ ሁኔታ ባለመኖሩ፣ እስከመጨሻው ህወሓትን ለመፋለም ቆርጦ እንደተነሳ አብራርተዋል። ስለሆነም የህወሓት ግብአተ መሬት እስካልተፈጸመ ድረስ የአፋር ሕዝብ ትግል እንደማይቆም ተናግረዋል። የሕዝቡም ቁርጠኝነት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በግልጽ እየታየ እንደሆነ በተደጋጋሚ በህወሓት ላይ የሚቀዳጀው ድል ሕያው ምስክር ነው።

ህወሓት በአፋር ላይ ጥቃቱን በተደጋጋሚ በመቀጠል ወደ አካባቢው ዘልቆ ለመግባት በያሎ በኩል እንደገና ቢሞክርም ሕዝቡ እራሱን አደራጅቶ ከጥቃት በመመክት የህወሓትን አከርካሪ ለመስበር ችሏል። ለአምስተኛ ጊዜ ጭፍራና በሀማን ይዞ ዋናውን የኢትዮ-ጅቡቲ መንገድ ለመዝጋት ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረገ ቢሆንም፣ ያን ማድረግ ሊሳካለት አልቻለም በማለት አስተባባሪው ገልጸዋል። በአፋር በኩል በኹሉም አቅጣጫ፣ ከጭፍራ አስከ ዞን 5 ድረስ ባለው መንገድ፣ ህወሓት መፈናፈኛ በማጣቱ በባቲ በኩል ሙከራውን አልተወም ብለዋል።

በጥቅምት 2014 ለተከታታይ15 ቀናት ከሌሊቱ 9 ሰዓት እስከ ጠዋቱ 2 ሰዓት ድረስ በአፋር የተለያዩ ወሳኝ የሚባሉ ቦታዎች ላይ ህወሓት ጥቃት ለመፈጸም ቢሞክርም፣ በሕዝቡ የተባበረ ክንድ ከሽፎበታል። ጠላት በብዛት እንደጎርፍ ፣ በሰው ማዕበል አፋርን ለማጥለቅለቅ እየጣረ ቢሆንም ሳይሳካለት ቀርቷል። ቁበኦ ተራራ ለባቲ ቅርብ በመሆኗ፣ የህወሓት ቡድን በአካባቢው በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት አሕመድ ኑር ሳሊ፣ነገር ግን በአፋር በኩል መንገዱ ኹሉ የተዘጋ በመሆኑ የወራሪው ቡድን ዕቅድ ሊሳካለት አይችልም ብለዋል የክልሉ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስተባባሪ።

ህወሓት በ ኅዳር 6 እና 7/2014 በካሳ ጊታ እና በሚሌ በኩል ጥቃት ለመፈጸም ቢሞክርም ሳይሳካለት ቀርቷል። ይህ ሆኖ እያለ ህወሓት የኢትዮ-ጅቡቲን ጥቁር አሰፓልት ለመቁረጥ ሚሌን ተቆጣጠርኩ ያለው ፍጹም ውሸት መሆኑን ገልጸዋል። የሽብር ቡድኑ ተሽሎክሉኮ በአፋር ክልል በገባባቸው አካባቢዎች ያልጠበቀው ከፍተኛ የሰው እና የንብረት ኪሳራ ስለደረሰበት፣ በተራረፈው ትንሽ ኃይል ሔድ መለስ እያለ ጥቃት ለማድረግ ቢሞክርም፣ በአገር መከላከያ፣ በአፋር ሕዝባዊና ልዩ ኃይል እንዲሁም ሚሊሻ፣ ከጥቅም ውጪ እየሆነ ይገኛል ብለዋል። አሕመድ ኑር አክለውም፣ ጌታቸው ረዳና ደብረጸዮን ገ/ሚካኤል ፉከራቸውን ለማሳየት፣ በአፋር በ 5 ግንባሮች ማለትም በጭፍራ፣ እዋ፣ ካሳ ጊታ፣ ተላላን ጨምሮ በተለያዩ ግንባሮች ከፍተኛ የሰው ቁጥር በመያዝ ተዋግተን እያሸነፍን ነው የሚሉት ከፕሮፓጋንዳ ያለፈ ጉዳይ እንዳልሆነ ተናግረው፣ ከፍተኛ ሽንፈት በህወሓት አባላት ላይ እንደደረሰ አልደበቁም።

በተጨማሪም የሚሌን የኮማንድ ፖስት ኃላፊ የሆኑትን አብዱ ሐሰን አዲስ ማለዳ አናግራ ተከታዩን ምላሽ አግኝታለች። ህወሓት ሚሌን ይዣለሁ ብሎ የሚያናፍሰው ወሬ ፍጹም ሐሰት እንደሆነ እና አሁንም ነዋሪው የዕለት ተዕለት ተግባሩን በተለመደው መልኩ በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ ኃላፊው አብራርተዋል። የአገር መከላከያ ሠራዊትም ከአፋር ሕዝብ እና ሚሊሻ ጋር በመቀናጀት በጠላት ላይ ድል በተከታታይ እያስመዘገበ ይገኛል በማለት ህወሓት የሚናገረው ሁሉ ከሐቅ ያፈነገጠ እንደሆነ ገልጸዋል።

ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን የሰጡት አህመድ ኑር አያይዘውም፣ አፋር አገሩን ለመጠበቅ፣ የኢትዮጵያን ጠላት ለመመከት ሕይወቱንና ንብረቱን እየገበረ እንደሚገኝ ገልጸው፣ መንግሥት እና ኹሉም ኢትዮጵያዊ ይህንን በማወቅ ለክልሉ ኃሎችና ሕዝብ የሚያስፈልገውን ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ በአጽንዖት ተናግረዋል። አፋር ክልሉን ከጠላት እየተከላከለ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያውያን እየተዋጋ ነው። ባለሀብቶች እና ሌሎች በጎ አድራጊ ተቋማት በሚችሉት ሁሉ ይሄንን ሕዝብ ሊረዱት ይገባል። በተለይም በተሸከርካሪ፣ በምግብ፣ በተለያዩ የቁሳቁስ ዕርዳታ አቅርቦት አፋርን ኢትዮጵያውያን ሊያግዙት እንደሚገባ አስተባባሪው ተናግረዋል።

የአፋር አርብቶ አደር በርካታ ከብቶቹ፣ ግመሎቹ፣በጎቹ እና ፍየሎቹ በጦርነቱ በህወሓት በመገደላቸው ለከፍተኛ ችግር ተዳርጓል። ሕዝቡ በምግብ ዕጥረት ችግር ላይ በመውደቁ መንግሥት እና ሌሎች ኢትዮጵያን አይዞህ ሊሉት እንደሚገባ ተናግረዋል። ረሀብ ጊዜ ስለማይሰጥ ኹሉም ኢትዮጵያዊ በአስቸኳይ ለአፋር ሕዝብ ሊደርስ እንደሚገባው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የአፋር ሕዝብ በህወሓት በተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈጸምበት መቆየቱ ይታወቃል። ይሁን እንጂ የተከፈቱበትን ጥቃቶች ኹሉ በቆራጥነት በመመከት የጀግንነት ታሪኩን እየፃፈ ይገኛል። ለዚህም ምስጢሩ ሦስት መሠረታዊ ጉዳይ ነው፣ እንደ አህመድ ኑር ገለጻ፣ አንደኛው የአፋር ሕዝብ አርብቶ አደር በመሆኑ ጫካና ዱሩ ለሱ የቀን ቤቱ ነው። ስለዚህ እራሱን የሚጠብቅበት መሣሪያ ከእጁ አይጠፋም። በዚህ ምክንያት እራሱን ከጠላት መጠበቅ ያውቅበታል። ኹለተኛ፣ የአፋር ሕዝብ በታሪኩ ኢትዮጵያን በመውደድ፣ሉአላዊነቷን በማስጠበቅ፣ እንደሌላው ኢትዮጵያዊው ሁሉ ወደር የማይገኝለት ሕዝብ መሆኑ ሲሆን፣ በሦስተኛ ደረጃ የሚነሳው ደግሞ የአፋር ሕዝብ መሪውን ማክበሩ ነው። አፋር ጠንካራ መሪ አለው፣ እሱንም ይከተላል። ስለራሱ መብት፣ ስለሌሎች መብት በደንብ ያውቃል። በዚህ ምክንያት አፋር አገርን እንዴት ከጠላት እንደሚጠብቅ ያውቃል፤ በማለት ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ክንዳቸውን በማስተባበር የህወሓትን የሽብር ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማስወገድ ወደልማት ፊታቸውን ማዞር እንደሚገባ ጠቁመዋል። አሕመድ ኑር አክለውም፣ የአፋር ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን አገሩን ከጠላት ለመጠበቅ ቁርጠኛ እንደሆነ ኹሉም ሊያውቅ ይገባዋል በማለት ሐሳባቸውን አጠቃለዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 159 ሕዳር 11 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com