የእለት ዜና

የአዲስ አበባና የለገጣፎ ወጣቶች አለመግባባታቸውን የፈቱበት መንገድ

የሠላምና ልማት ማዕከል ለትርፍ ያልተቋቋም፣ መንግሥታዊ ያልሆነ አገር በቀል ድርጅት ሲሆን፣ ከማንኛውም የፖለቲካም ሆነ የሌላ ወገንተኝነት የጸዳ፣ በአገሪቱ የሠላም ባህል እንዲስፋፋ፣ በውይይት እና በንግግር የሚያምን ማሕበረሰብን ለመፍጠር የሚሰራ ተቋም ነው።
ተቋሙ ከተመሰረተበት 1982 ዓ/ም አነስቶ በተለያዩ የሠላም ግንባታ ሥራዎች ላይ ተሰማርቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። በተለይም ደግሞ ግጭትን ለመፍታት እና የሠላም ባህልን ለመገንባት የሚያስችሉ አገር በቀል እውቀቶችን በማዳበር በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ ሲያደርግ ቆይቷል። በተለይም ደግሞ በቦታ እና በሁኔታ አለመመቸት ምክንያት ለብዙ ተቋማት ለመድረስ አመቺ አይደሉም የሚባሉ የአገራችን አካባቢዎች ጭምር ሳይቀር በመግባት ከታችኛው የማሕበረሰብ አደረጃጀቶች ጋር ሰፊ የሠላም ግንባታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። ተቋሙም በተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ምንም እንኳ እንደአገር ያለብን ችግር ዘርፈ ብዙ እና ሰፊ ቢሆንም የአቅሙን በማበርከት ላይ ከመሆኑም በላይ አመርቂ የሚባሉ ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ ይገኛል። ተቋሙም አሁን ያሉ ፕሮጅክቶችን በማስፋት እና ወደተጨማሪ ቦታዎች በመንቀሳቀስ፣ እንዲሁም የተለያዩ ማሕረሰብ አቀፍ የሆኑ የሰላም ጥረቶችን በመደገፍ እንዲሁም አቅማቸውን ጭምር በመገንባት ለችግሮች ተመጣጣኝ የሆነ ምላሽ ለመስጠት የበኩሉን አስተዋፅኦ በማበርከት የሚቀጥል ይሆናል።
ሠላምና ልማት ማዕከል

ኢትዮጵያ ውስጥ አለመግባባቶችን በንግግር መፍታት የተለመደ ባህል ነው። ከማኅበረሰብ ማኅበረሰብ የግጭት ዓፈታቱ መንገድ ይለያይ እንጂ፣ አለመግባባቶች የሚቋጩት በሽማግሌዎች አማካኝነት በወጣቶቹ ዕርቅ ነው። የዕርቁ መንገድም ሆነ የማቀራረቢያ ሒደቱ ከቦታ ቦታ ቢለያይም ዓላማው ግን አንድ ሲሆን፣ የተጋጨም ሆነ የተራራቀ ተቀራርቦ አለመግባባቱን በመፍታት ወደነበረበት ጥሩ ግንኙነት እንዲመለስ ነው።

በዘመናዊት ኢትዮጵያ ሽምግልና እየሰጠ ከሚገኘው ጥቅም በተጨማሪ፣ መንግሥታዊም ሆኑ ግብረሰናይ ተቋማት የሚያደርጉት አስተዋጽኦ እየጨመረ መጥቷል። ከነዚህም ተቋማት መካከል ለበርካታ ዓመታት አለመግባባት በሚከሰትባቸው ቦታዎች እየተዟዟረ በሠላም ግንባታ ሒደቶች ላይ ኋላፊነቱን ሲወጣ የኖረው የሠላምና ልማት ማዕከል አንዱ ነው።

ማዕከሉ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችንም ሆነ አለመግባባቶችን ሲያበርድ እና በኋላም ማኅበረሰቡ ተቀራርቦ ወደነበረበት ወዳጅነቱ እንዲመለስ የማቀራረብ ሥራን ሲሠራ ቆይቷል። ማዕከሉ በኹሉም ክልሎች ማለት በሚባል መልኩ፣ አቅሙ እስከፈቀደ ድረስ ከመንግሥታዊና ለጋሽ ድርጅቶች ጋር በመሆንም ውጤታማ ሥራን ሲሠራ መቆየቱን ከዚህ በፊት በወጡት ዕትሞች ላይ ይዘንላችሁ ቀርበናል።

የአዲስ አበባ ወጣቶች በዙሪያቸው ካሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ማለትም ከኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች ጋር በተለያዩ ጊዜዎች አለመግባባት ውስጥ ገብተው ነበር። በተለይ የቡራዩ ወጣቶችና የአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ነዋሪዎች መካከል የነበረ አለመግባባትን ለመቅረፍና በመካከል የነበረ ግጭት እንዳይደገም ለማድረግ፣ እንዲሁም ወደ መቀራረብ እንዲያመሩም ለማስቻል ማዕከሉ በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን የየአካባቢዎቹን ነዋሪዎች ዕማኝ በማድረግ በተከታታይ ዕትሞች ሒደቱንና ውጤቱን ስናቀርብላችሁ ቆይተናል። ለዛሬ ደግሞ የአዲስ አበባ የአዲሱ ክፍለ ከተማ የለሚ ኩራ ነዋሪዎች ከአጎራባቻቸው ከለገጣፎ ለገዳዲ ነዋሪዎች ጋር ገብተውበት የነበረውን አለመግባባት ለመቅረፍ ስለነበረው ሒደት የየአካባቢዎቹን ተወካዮች አነጋግረናል።

ቴዎድሮስ ግርማ ይባላል። የአዲስ አበባ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ነው። ሰሜን ሸዋ ተወልዶ ከ6 ዓመት በፊት ወደ ከተማዋ የመጣው ይህ የ27 ዓመት ወጣት፣ 12ኛ ክፍልን ተምሮ ጨርሶ ከአካባቢው ወጣት ጋር ተደራጅቶ የኮንስትራክሽን ቁሶችን በማቅረብ ሥራ የሚተዳደር ነው። በተለምዶ አያት በሚባለው አካባቢ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅቶ የሚኖረው ይህ ወጣት፣ የአካባቢውን ልጆች ወክሎ የሠላምና ልማት ማዕከል ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ አስተባባሪ የነበረ ነው።

ቴዎድሮስ እንደሚለው፣ በኹለቱ አካባቢዎች የሚኖሩ ወጣቶች አልፎ አልፎ ከሚፈጠሩ አለመግባባቶች ውጭ ያን ያህል የተበላሸ ግንኙነት አልነበራቸውም። በመካከላቸው ሠላም ነበረ ለማለት ቢቻልም፣ አልፎ አልፎ ግን ግጭት የሚፈጥሩ አለመግባባቶች ይከሰቱ እንደነበር ያስታውሳል። ከሁሉም ምክንያቶች ለልዩነት በር ከፍተው የነበሩት የቋንቋና የባንዲራ ጉዳዮች እንደነበሩ የሚያስታውሰው ቴዎድሮስ፣ ማዕከሉ ባዘጋጃቸው ተከታታይ ውይይቶች አማካይነት በኹለቱ ወጣት የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል የነበሩ አለመግባባቶችና የአመለካከት ልዩነቶች እንዲፈቱ ተደርጓል።

ቋንቋን በተመለከተ ይነሳ የነበረው የልዩነት ጥያቄ በውይይቱ ወቅት ተነስቶ ከመግባባት ላይ መድረስ መቻሉን ያነሳው ይህ ወጣት፣ ቋንቋ መግባቢያ እንጂ መለያያ አይደለም በሚል ከስምምነት መደረሱን አመላክቷል። ማንም ሰው የፈለገውን ቋንቋ በፈለገበት የመናገር መብቱ ተጠብቆለት ሊኖር ይገባል የሚለው ወጣቱ፤ ወጣቶችን ወደአለመግባባት የሚከተው ይህ ጉዳይ እራሱን የቻለ እልባት የሚያገኝበት በመንግሥት ደረጃ ሕጋዊ አሠራር ሊበጅለት እንደሚችል በማመን፣ ለችግሩ ያለውን አመለካከት ማስተካከልን በወጣቱ ዘንድ መፍትሔ እንዲገኝለት ውይይቱ አስተዋጽዖ ማድረጉን እማኝነቱን ሰጥቷል። ሁሉ ነገር በአንድ ቀን አይለወጥም የሚለው ይህ የውይይቱ አስተባባሪ፣ በመድረኩ ተገኝተን የአመለካከት ለውጥ ያደረግን ለሌሎች ያገኘነውን ጥቅም እንድናካፍል ዕድል ተሰጥቶናል ብሏል።

ሠንደቅ ዓላማን በተመለከተም፣ ሁሌ የሚነሳው ጭቅጭቅ ተገቢ አለመሆኑን በማንሳትም፣ ለግጭትም ይሁን ላለመግባባት መንስዔ መሆን እንደማይገባው ከስምምነት ላይ መደረስ መቻሉን ይናገራል። ማንነትን በተመለከተ የሚነገሩ የአመለካከት ችግሮችም ተነስተው እንደነበር የሚያስታውሰው ቴዎድሮስ፣ ማንም ከአያት ቅድመ አያቱ በኋላ ያለውን አለማወቁ ብቻ ሳይሆን፣ ያልተቀላቀለ ማንነት ያለው ስለመኖሩ መናገር የሚችል እንደሌለ በውይይቱ ወቅት እንድንረዳ ተደርጓል ሲል የመድረኩን ጠቃሚነት ያስረዳል።

አብዛኛው የውይይቱ ተሳታፊ በፊት ስለነበረበው የተዛባ ግንዛቤ ሁኔታ በመቆጨት ነው መድረኩ የተጠናቀቀው የሚለው ይህ ወጣት፣ ከዚህ በፊት ራሱ የግጭት ተሳታፊ እንደነበረና በኮማንድ ፖስት ጭምር ታስሮ መፈታቱን ያምናል። ካለማወቅ የተነሳ እሱና መሰሎቹ ወጣቶች ጎራ ለይተው ይጋጩ እንደነበር የሚያስታውስ ሲሆን፣ ያን ዓይነት ሁኔታ አልፈው አሁን በእዚህ ደረጃ የተስተካከለ አመለካከት ለመያዝ እንዲበቁ የሠላምና ልማት ማዕከል አስተዋጽዖ ከፍተኛ ነበር ይላል። እንደትልቅ ሰው ከባድ ኃላፊነት ተሰጥቶኝ ተወያይቼ የወከልኩትን ማኅበረሰብ ለመለወጥ እንዳግዝ መጠራቴ ደስተኛ አድርጎኛል የሚለው ቴዎድሮስ፣ በራሱ ተነሳሽነት በርካታ ወጣቶችን ሰብስቦ ያገኘውን ልምድ በማካፈል ሁሉም የአመለካከት ለውጥ እንዲያደርግ እየጣረ እንደሆነ ይናገራል።

የሠላምና ልማት ማዕከል የጀመረው እንቅስቀሴ ጥሩ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን የሚናገረው ይህ የውይይቱ አስተባባሪ፣ “እኛ ዝም ተባልን” ብለው የሚጠብቁ ያልተካተቱ ወጣቶችን ለማወያየት ሠፊና ዘላቂነት ያለው መድረክ ቢያዘጋጅ መልካም ነው ይላል። ሰው ፊትለፊት በፈተና ካልተፈተሸ ለውጥ ማምጣት አይቻልም ብሎ የሚያስበው ይህ ወጣት፣ አንድ ወቅት የሚደረግ ጥረት ብቻውን ዘላቂ መቀራረብን ለማምጣት አዳጋች ያደርገዋል ብሏል። ወጣቱ በተደጋጋሚ እንዲገናኝ ቢደረግ ቅርርቡን ማጠናከር እንደሚቻል የሚያምን ሲሆን፣ በውይይት ደረጃ የተፈጠረውን መጸጸትና የአመለካከት ለውጥ በተግባር በማዋል ይበልጥ ወጣቶች በዘላቂነት እንዲቀራረቡና እንደወዳጅ እንዲተያዩ የሚያደርግ ይህን መሠል ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ይናገራል።

ሌላዋ የለገጣፎ ለገዳዲ ወጣቶችን ወክላ በውይይቱ ላይ የተካፈለችው ሐዊ አለማየሁ ናት። ተወልዳ ያደገችበት አካባቢ የምትኖረው ይህች የ24 ዓመት ወጣት ከጅማ ዩኒቨርስቲ በተመረቀችበት ‹ቲያትሪካል አርት› ሥራ መፈለግ ከጀመረች ኹለት ዓመት አልፏታል። እንደወጣቷ ዕይታ በአዲስ አበባና ለገጣፎ ወጣቶች መካከል ችግሮችና አለመግባባቶች ሲፈጠሩ የነበረ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሠላምና ልማት ማዕከል በጉዳዩ ላይ በመግባት አለመግባባቱ እንዲቀረፍ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

ማዕከሉ ባዘጋጃቸው የውይይት መድረኮች አማካይነት በመካከል የነበሩ አለመግባባቶች ተወግደው ግንኙነቱን ለማስተካከል መቻሉን ትመሰክራለች። የነበረውን ችግር መቅረፍ ብቻ ሳይሆን፣ ለወደፊትም ችግር ቢፈጠር ወደሌላ ነገር ከመግባት ይልቅ በውይይት መፍታት እንዳለብን የተገነዘብንበት ነው ስትል ወጣቷ ትናገራለች። የኹለቱ አካባቢ ወጣቶች በተለያዩ ምክንያቶች የምንገፋፋ፣ እንዲሁም አንዳችን አንዳችንን አሳንሰን ለማሳየት የምንፈልግ የሚመስለንን ተቀራርበን ስንነጋገር ትክክል አለመሆኑን እንድንረዳ አድርጎናል ስትልም ውጤቱን ታስረዳለች።
ውይይት ሊካሄድ ነው ሲባል ትልቅ ደስታ ነበር የተሰማኝ የምትለው ሐዊ፣ እኛ ብቻ ነን ትክክል የሚል በኹለታችንም በኩል የነበረን አስተሳሰብ እንድናስቀርና በሚያግባቡን ነገሮች ላይ እንድናተኩር መድረኩ ጠቅሟል ትላለች። ተለያይተንና ተነጣጥለን መኖር እንደማንችል ውይይቱ አስገንዝቦናል ያለች ሲሆን፣ የውይይቱ ሒደት ግልጽና አስደሳች ስለነበር ሌሎችም ከተለመደው ደረቅ የውይይት ይዘት እንዲላቀቁ ሊማሩበት ይገባል ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች።

ጨዋታ አዘል የማቀራረቢያ መንገዳቸው በጣም ጥሩ ነበር ስትል ማዕከሉ የተጠቀመበትን መንገድ የምታደንቀው ይህች ወጣት፣ አሰልቺ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን የማንግባባቸውን በማቀራረብና እንድንረዳቸውም በማድረጉ ማዕከሉ ሊመሰገኑ ይገባል ትላለች።
ሰውን ዝም ብለን መገምገምና መፈረጅ እንደሌለብን አውቀናል ያለችው ይህች ወጣት፣ ችግርን ለመፍታት ውይይት ያለውን ጠቀሜታ እንድንረዳ፣ ሌላን ማዳመጥ ያለውን ጥቅም እንድንገነዘብ፣ እንዲሁም መተጋገዝና መረዳዳት እንዳለብን እንድናውቅ ያደረገ ሒደት ነበር ስትል ውይይቱን ትገልፀዋለች።

የኹለቱ አካባቢ ወጣቶች ተቀራርበው አንድ ሆነው ከሰሩ የማይለወጥ ነገር የለም የምትለው ሐዊ፣ ማዕከሉ ከወጣቱ ጎን ሆኖ የበለጠ ለውጥ እንዲመጣ ሥራውን አስፍቶ መቀጠል አለበት ትላለች። የወጣቱ ግንኙነት አሁን ካለበትም ከፍ ማለት አለበት የምትል ሲሆን፣ የሠላምና ልማት ማዕከልም ተልዕኮውን በበለጠ ስኬት እንዲወጣ የሚመለከታቸው አካላት እገዛ ሊያደርጉለት ይገባል ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች።


ቅጽ 4 ቁጥር 159 ሕዳር 11 2014

Comments: 1

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!