የእለት ዜና

በልኂቃንና በጁንታዎች ሥም እየታወጀ ያለው ዘመቻ ይታሰብበት!

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል ከተጀመረ አንድ ዓመት ያስቆጠረው ጦርነት ብዙ ግፎች እንዲፈፀሙ ያደረገ ነው። ኹነቱ ለዘመናት ሲብላላ የነበረ የጥቂቶች ጥላቻ አደባባይ እንዲወጣ በማድረጉ ሕዝብ በሕዝብ ላይ እንዲነሳሳ የሚያደርጉ በርካታ ቅስቀሳዎች በይፋ ተደርገዋል። ጎረቤት እንዳይተማመን የሚያደርጉ በርካታ ድርጊቶች ተፈጽመዋል፤ ዘግናኝ የሚባል መተላለቅ እንዲፈጸም የሚጥሩ መኖራቸውም ይነገራል። ስለጦርነቱ ዓላማ እንዲሁም በልኂቃኖች ስለሚደረገው ቅስቀሳ ግዛቸው አበበ ምልከታቸውን እንደሚከተለው አስቀምጠውታል።

በአሁኑ ጊዜ በሕዝብ ላይ ታርጋ እየለጠፉ ጥቃት ማካሄድ ኢትዮጵያ ውስጥ እየጀማመረ መሆኑ የሚካድ ነገር አይደለም። በዚህም ጥቂት የማይባሉ ወገኖች በግፍ ተገድለዋል።
ህወሓት የአማራ ልኂቃንን በጠላትነት ፈርጆ ጥቃት እየፈጸመ መሆኑን ሲናገር፣ ብልጽግና ደግሞ ጁንታዎች ከምድር ገጽ መጥፋት እንደሚገባቸው ጠላቶቹ አድርጎ ፈርጆ እየወጋቸው መሆኑን ይናገራል። ህወሓት የአማራ ልኂቃን እነማን እንደሆኑ ሲገልጽ፣ መሬት እናስመልሳለን የሚሉ ጥቂት ወገኖችን መሆኑን ሲናገር፣ ብልጽግናዎች ደግሞ ጁንታዎች እነማን መሆናቸውን ሲያብራሩ ከግድያና ከእስራት የተረፉ ጥቂት የህወሓት አውራዎች መሆናቸውን ይናገራሉ። ነገር ግን፣ የአማራ ልኂቃንን ማጥቃት በሚል ሽፋን በመላው አማራ ሕዝብ ላይ ሒሳብ የማወራረድ ሥራ እየተሠራ መሆኑና ጁንታዎችን ማጥፋት በሚል ሽፍንም የትግርኛ ተናጋሪዎች ሕይወት አጣብቂኝ ውስጥ እየገባ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው።

በአጭሩ አማራ የሚባለው ሕዝብ በሙሉ ጠላቴ ነው የሚሉ ተጋሩ፣ ትግሬ የሚባለው ሕዝብ ጠላቴ ነው ብለው የሚያስቡ አማራዎች እንዲበራከቱ ከፍተኛ ግፊት እየተደረገና ማቆሚያ የሌለው የመተላለቅ ምዕራፍ ለመክፈት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ግልጽ ነው። አንዳንዱ በምርጫው ሌላው ደግሞ ለሕልውናው ብሎ ግብግብ ወስጥ መግባት እንደሚገባው ሆኖ እንዲሰማው የሚደርግ ሁኔታ የነገሰበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። አንዳንድ ባለሥልጣናት እንደ ቀላል የሚናገሩት ነገር እንደ መመሪያ ሆኖ ሕዝብን በሕዝብ ላይ ለማነሳሳት ገፊ ምክንያት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የተለየ የዘርና የኃይማኖት ጥላቻ ያላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች የባለሥልጣናቱን ንግግር ያለ ልክ ለጥጠው ድብቅ ዓላማቸውን ለማራመድና የዓላማቸው ተባባሪዎች የሆኑ ሰዎችን ለማባዛት ጥቅም ላይ እያዋሉት ነው። በሌላ በኩል አንዳንዶች ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ይጠቅመናል ብለው ጭፍንና ጅምላ ጥላቻን ሲሰብኩ፣ ሌሎች ደግሞ ኢትዮጵያን እወዳለሁ በሚል ሽፋን የኢትዮጵያ ጠላቶች ናቸው ያሏቸውን ሕዝቦች በጅምላ ለማጥፋት በስሜታዊነት ጥላቻን ለማራመድ ቆርጠው ተነስተዋል።

ከዚህ ቀደም በፖለቲከኞች ሲስተጋባ የነበረው፣ “አንድ ሰውና አንድ ጥይት እስኪቀር እንዋደቃለን!” የሚለው መፈክር በዚህ ዘመን ሚሊዮኖችን በሚሊዮኖች በማጣፋት “እነሱ ሲያልቁ እኛ ትርፍ ሰው ይኖረናል” በሚል አረመኔያዊ ስሌት ተተክቶ በመስተጋባት ላይ ይገኛል።
ከጥቅምት 2013 መጨረሻ እስከ ሰኔ 2013 በትግራይ ክልል ተፈጸሙ ተብለው በትግራይ የዩኒቨርስቲ ምሁራንና ፖለቲከኞች የተነገሩ ድርጊቶች፣ ከሰኔ 2013 ዓም ጀምሮ በአማራ ክልል እየተፈጸሙ መሆኑን በአማራ ክልል ዩኒቨርስቲ መምህራንና ፖለቲከኞች እየተነገሩ ነው። የዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ምሁራን ምስክርነት እየተባለ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ጭምር በተከታታይ ይፋ የተደረገው የግፎችን ዝርዝርና በጎንደር ዩኒቨርስቲ ምሁራን የተካሄደ ጥናት ተብሎ ለሕዝብ በቀረበው ሠነድ ላይ የቀረቡት የሰቆቃ ድርጊቶች መመሳሰል አንዱ የሌላው ግልባጭ እስኪመስል ልዩነት የሌላቸው የግፍ ታሪኮችን የሚያትቱ ናቸው። የመመሳሰል ብቀላዎች መካሄዳቸውንና የክፋት ብድርን የመመለስ ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን የሚያመላክት ነው። ከኹለቱም ጎራዎች የቀረበው እሮሮ በሚከተለው ዓይነት መጠቃለል የሚችል ነው።

አንድን ሕዝብ ለመጨረስና የዘር ጥላቻን ለማራመድ ረሀብ እንዲከሰት ማድረግ እንደ ጦር መሣሪያ ተደርጎ ጥቅም ላይ መዋሉ በኹለቱም ወገኖች ተነግሯል። እርሻችንን እንዳናርስ ተከለከልን፤ አዝመራችን በታንኮችና በተሸከርካሪዎች ተረመረመብን፤ የደረሰ ሰብላችን ታጭዶ ተወሰደብን፤ በጎተራችን ያለ እህል ተወሰደብን፤ እህል የያዘ ጎተራችን በውኃ እንዲሞላ ተደርጎ እህላችን እንዲበለሽ ተደረገ፤ የዕርዳታ እህል እንዳናገኝ ተከለከልን፤ በረሀብ ልጄን አጣሁ፣ወዘተ. የሚሉ እሮሮዎች ለመቁጠር በሚያዳግት መጠን ተሰምተዋል።

ጾታዊ ጥቃትም እንደ ጦር መሣሪያ ሆኖ የዘር ጥላቻን፣ ብቀላንና አንድን ሕዝብ ለማዋረድ ጥቅም ላይ መዋሉም ይፋ ተደርጓል። በዚህ ጥቃት ለዓቅመ-ሔዋን ካልደረሱ ሕፃናት ጀምሮ እስከ መነኩሴዎችና በዕድሜ የገፉ እናቶች ሰለባ መደረጋቸው በዚህና በዚያ ተዘግቧል። ላለመደፈር ያንገራገረችን ወይም ግብግብ ውስጥ የገባችን ሴት በጥይት መምታት፣ አንዲትን ሴት በቡድን መድፈር፣ እናትና ሴት ልጅን አንድ ላይ መድፈር፣ ሚስትን በባሏ ፊት መድፈር፣ እናትን በልጆቿ ፊት መድፈር፣ የሴቶች ማሕጸን ባዕድ ነገር መጨመርና በስለት በመጉዳት ለችግር ማዳረግ፣ወዘተ. የዚህ የጥቃት ድርጊት ጥቂት ገጽታዎች መሆቸው ይፋ ተደርጓል።

አንድን ሕዝብ ለማደኽየት የኢኮኖሚ አውታሮችንና መሠረት ልማቶችን ማውደምና መዝረፍ ሌላው ጥቅም ላይ እንደዋለ የሚነገርለት የጦር መሣሪያ ነው። በሽሕዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች መዘረፍና ማውደም፣ የሕክምና ተቋማትን የሚያራቁት ዝርፊ መፈጸም፣ የግልም ሆኑ የመንግሥት ባንኮችንና ሌሎች የንግድ ተቋማትን በሠፊው መዝረፍ፣ ትንንሽ ኢንዱስትሪዎችንና ግዙፍ ፋብሪካዎችን መዝረፍና በቃጠሎ ማውደም፣ ወዘተ. ድህነት ባደቀቃት በኢትዮጵያችን ውስጥ መፈጸማቸውም ተነግሯል።

የተጋነኑ፣ ፈጠራ የታከለባቸውና አንዱ ወገን ሌላውን አምርሮ እንዲጠላ ሆነ ተብለው የተፈበረኩ ክሶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ቢገመትም፣ በየአካባቢው እነዚህን መሰል ጥቃቶች፣ ግፎችና ወንጀሎች መፈጸማቸው ግን ሊካድ በማይችልበት ደረጃ በብዙ ማስረጃዎች ተጨባጭ ሆኗል። ጊዜውን ጠብቆ ገለልተኛ በሆኑ ወገኖች ሊካሄዱ የሚገባቸው ምርመራዎችና የማጣራት ሒደቶች ሊካሄዱ እንደሚገባ አቤት የሚሉና የጦር ወንጀል ተፈጸመብኝ የሚሉ ክሶች ያለማቋረጥ እየተስተጋቡ ነው። ብዙዎች በሚፈጸመው ነገር ልባቸው እየደማ ቢሆንም፣ ጥቂቶች በየሚዲያው ቀርበው እንዳሻቸው የመደስኮር መብት ያላቸው ዕኩዮች ግን በሌላው ስቃይ ሲቦርቁና ወገኔ አይደለም ባሉት ሕዝብ ዕሮሮ ሲሳለቁ እየተሰሙና እየታዩ ነው። እነዚህ ወንጀሎችና ግፎች የሚፈጸሙት ኢትዮጵያ ጠላቴ እኔም ጠላቷ ነኝና ኢትዮጵያ ትፍረስ በሚል ቀረርቶ በሚታወቁ ግለሰቦችና ቡድኖች ብቻ ሳይሆን፣ ከእኔ በላይ ኢትዮጵያዊ የለምና ኢትዮጵያን ለማዳን እየሠራሁ ነው በሚል ሽፋን ጥላቻን በሚያራምዱ ግለሰቦችና ቡድኖችም ጭምር ነው።

ከ1950ዎቹ ጀምሮ እስከ 1983 ዓ.ም. የመጨረሻ ወራት፣ ወደ 30 ዓመታት ለሚሆን ጊዜ በኢትዮጵያና በኤርትራ ነጻ አውጭ ግንባሮች መካከል ጦርነት በተካሄደባቸው ዓመታት ዝቅ ባለ ደረጃ ሲፈጸሙ የነበሩ ሕዝብን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች፣ ሀብት-ንብረት የማውደምና የመዝረፍ ድርጊቶች፣ በ1990ዎቹ መጀመሪያ በተካሄደው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ትግራይና ኤርትራ ውስጥ በሠፊው ተካሂደዋል። ከ1968 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያና በትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር (TPLF) መካካል ለ17 ዓመታት ትግራይ ውስጥ በተካሄደው ጦርነት ያልተፈጸሙ ወይም አልፎ አልፎ ብቻ ሲፈጸሙ የነበሩ ሕዝብን እንዳለ ዒላማ የሚያርጉ ጥቃቶች፣ ሀብት-ንብረትን የማውደምና የመዝረፍ ድርጊቶች ከጥቅምት 2013 ዓም ጀምሮ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልል በመካሄድ ላይ ባለው ጦርነት በሰፊው ሆነ ተብሎ ሲፈጸሙ እየተሰሙና እየታዩ ነው።

የዘር ፖለቲካ በአራቱም ማዕዘን በተዘራባት በኢትዮጵያ ሕዝብን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች የተለመዱ ናቸው። ተጎራባች ሕዝቦችን ዒላማ ያደረጉ የክልል ለክልል መሰል ጥቃቶችና ግጭቶች በተደጋጋሚ እየታዩ ነው። ከክልሌ ውጡልኝ በሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች “መጤዎች” የተባሉ ወገኖችን ማሳደድ፣ መግደል፣ ሀብት ንብረታቸውን መዝረፍና ማውደምም ከዘመነ ኢሕአዴግ እስከ ዘመነ ብልጽግና ያለማቋረጥ ሲፈጸሙ የሚታዩ አሳሳቢ ጉዳዮች ናቸው። እነዚህን መሰል አደገኛ ድርጊቶች በሥውር ቡድኖች፣ ተቃዋሚ በሚባሉ ቡድኖች፣ ተቃዋሚ በሚባሉ ተጣቂዎች ብቻ ሳይሆን በመንግሥታዊ የሥልጣን ቦታዎች ላይ በተቀመጡ ሰዎችም ጠንሳሽነት፣ ገፋፊነት፣ ተባባሪነትና ሽፋን ሰጭነት እየተፈጸሙ ከቆዩ በኋላ ከጥቅምት 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ የመከላከያ ኃይልን በመቆጣጠር መከላከያን የብሔር ተኮር ጥቃቶችና ግጭቶች መሣሪያ ለማድረግ ወደ መሞከር አድጎ ታይቷል።

ለዚህ ግጭት ዋና መነሻ የሆነው የክልሎች እንጅ የኢትዮጵያ የግዛት ሉዓላዊነት አይደለም። ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር የሚል መፈክር አይሠራም፣ ክልሎች በፈለጉበት ጊዜ ከኢትዮጵያ ተገንጥለው ያራሳቸውን አገር መመስረት ይችላሉ ከሚል የሕገ-መንግሥቱን አንዳንድ አንቀጾች መሠረት ባደረገ አስተሳሳብ ተመርቶ የተካሄደ ግጭት መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። በዚህ አስተሳሳብ በመመራት መከላከያ ኃይልን ሊጠቀምበት የሞከረውና አልተባበርም አለ በሚል ሠበብ መከላከያን ያጠቃው የመጀመሪያ ኃይል ህወሓት ይሁን እንጅ፣ ይህን መሰሉን ድርጊት ለመፈጸም ህወሓት የመጨረሻው ይሆናል ብሎ መደምደም ትልቅ ስህተት ነው። ገዥ ሲሆን የተረኝነት ቁርን ሊጫወት የከጀለ ሌላ ቡድንም መከላከያን ለጠባብ ዘረኛ አጀንዳው ሊጠቀምበት እንደሚሞክር ካልሆነም መከላከያን ጠላቱ አድርጎ ሊያጠቃው እንዲነሳሳ መንገድ የሚከፍት ዘር ተኮር አስተሳሰብ የዳበረ መሆኑ ግልጽ ነው። በአሁኑ ጊዜ በግልጽና በአደባባይ፣ አመራሮች ሕዝብ በሕዝብ ላይ ሒሳብ እንዲያወራርድ፣ ሕዝብ ጥላቻን እንዲማርና ጭካኔን እንዲለምድ ሲመክሩ ተሰምተዋል። እነዚህ አመራሮች አጋጣሚውን ካገኙና ሁኔታዎች ከፈቀዱላቸው መከላከያ ለዚህ ዕኩይ ዓላማቸው ሊጠቀሙበት መከጀላቸውና መከላከያን በሕዝብ ላይ ሊያዘምቱት ሙከራ ማድረጋቸው አይቀሬ ነው።

በሰሜን ወሎ በመካሄድ ላይ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ አንዳንዶች የአማራን ሕዝብ ሌሎች ደግሞ የወሎን ሕዝብ ‘…ህወሓት ከትግራይ ውጭ ወረራውን እንዲያስፋፋ አደረገ…’ ብለው ተጠያቂ ለማድረግ እየሞከሩ ነው። የወልድያ ሕዝብ ወሎዬ ነው። የወልድያ ሕዝብ ለቀናት ህወሓትን እየተከላከለ እንደቆየና ህወሓት በከባድ መሣሪያ የሚሠነዝርበትን ጥቃት መቋቋም ስላልቻለ መረታቱን መርሳት አይገባም። የወልድያ ባለሥልጣናት የከባድ መሣሪያ ጥቃት እየደረሰባቸው ስለሆነ ተመሳሳዩን ዕርዳታ ከመንግሥት በኩል እንዲያገኙ ሲወተውቱ እንደነበረም የሚረሳ አይደለም። ታዲያ የሌሎች ከተሞችና የገጠር መንደሮች ነዋሪዎች ከዚህ ምን ይማራሉ? በመሠረቱ ሕዝብ በቀላሉ የታጠቀን ይሁን ያልታጠቀ ሽፍታን ፈርቶ አገሩን ጥሎ ሲሸሽ ሊፈረድበት ይቻላል። ነገር ግን መድፎችን፣ ታንኮችን፣ ቤኤም ሮኬት ተወንጫፊዎችን፣ ዲሽቃዎችንና ዙ-23 የተባሉ በኪሎ ሜትሮች ርቀት ተገዳዳሪን የሚገድሉ መሣሪያዎች የያዘን ጠላት ሕዝብ በተራ የጦር መሣሪያዎቹ መከላከል የሚችለው እንዴት ነው? ወያኔ ሕፃናትንና በዕድሜ የገፉ ሰዎችን ከፊት ለፊት እያሰለፈ ጦርነት እያካሄደ ነው፤ ወያኔ በሐሽሽ የነፈዙና በደመ ነፍስ ወደ እሳት የሚገቡ ሕፃናትንና ወጣቶችን በገፍ አሰልፎ ውጊያ እያካሄደ ነው፤ ወያኔ በሕዝብ ጎርፍ ወይም በሰው ማዕበል እየመጣ ወረራ እያካሄደ ነው፤ወዘተ. የሚሉ ምክንያቶች እየቀረቡና በሰብዓዊ ጋሻነት የተሰለፉ ሕፃናትን፣ መነኩሴዎችን፣ በዕድሜ የገፉ ሰዎችን ላለመጨፍጨፍ መከላከያ ማፈግፈጉ በተደጋጋሚ እየተነገረ በርካታ ከተሞች በህወሓት እጅ መውደቃቸው ይታወቃል። ታዲያ የራያና የወሎ ነዋሪዎች ከመከላከያ የተሻለ ስልት አላቸውና ነው ከተማቸውን እንዲጠብቁ የሚፈለገው?

እስከ ሰኔ 2013 ዓም ትግራይ ውስጥ በባንዳነት የተፈረጁ የትግራይ ሰዎች ነጻ ዕርምጃ ሲወሰድባቸው፣ ታፍነው ሲሰወሩና ሌላም ዓይነት ዕርምጃ ሲወሰድባቸው የነበረ ሲሆን፣ ከሰኔ 2013 ዓም በኋላ በተለይ በ2014 ዓም ደግሞ በህወሓት ቁጥጥር ሥር በገቡ ከተሞችና የገጠር መንደሮች የሚገኙ አማሮች በህወሓት ዕርምጃ እየተወሰደባቸው መሆኑ ይሰማል። በሌላ በኩል፣ በአዲስ አበባና በአማራ ክልል የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች የአፈሳ እስራት፣ አፈናና ግፍ እየተፈጸመብን ነው እያሉ በማረር ላይ ይገኛሉ። ይህን መሠረት በማድረግ አንዳንድ ሰዎች እያንዳንዱ ሰው በግሉ እየተነሳሳ በዙሪያው ባሉ ሰዎች ላይ ዕርምጃ እንዲወስድ ከፍተኛ ቅስቀሳ እያደረጉ ነው። በሐሰተኛ ስምና ምስል በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ አምድ ከፍተው አንድን ብሔር በስም ጠርተው በጅምላ ሊጠቃ እንደሚገባ የሚቀሰቅሱ ብቻ ሳይሆኑ፣ መንግሥት አለ በሚባልበትና መገናኛ ብዙኅን የሚገዙበት ሕግና ሥርዓት አለ ተብሎ ፈቃድ በሚሰጥበት ምድር፣ ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በአሜሪካና በአውሮፓ ምድር ተቀምጠው በቴሌቪዥን ሥርጭትና በዩትዩብ ላይ አንድን ሕዝብ በጅምላ በጠላትነት ፈርጀው ያለ ልዩነት ጥቃቶች እንዲፈጸሙ የሚቀሰቅሱ ግለሰቦችና ቡድኖች በግልጽ እየተንቀሳቀሱ ነው። ይህን አካሄድ የሚቃወሙ ወገኖችን በባንዳነት፣ በጁንታነትና በቅጥረኛነት በመፈረጅ ዝም ለማሰኘት መሞከርም የነዚህ ጋዜጠኞች ነን ባዮችና ዩትዩበሮች ዋና ሥራ ሆኖ እየታየ ነው።

ከ1983 የመጨረሻ ወራት ጀምሮ ላለፉት 30 ዓመታት የዘር ጥላቻ እየተዘራባት በዘለቀችው ኢትዮጵያ፣ ይህን መሰል ገደቡን ያለፈ የዘር ጥላቻ ቅስቀሳ በነጻነት መለፈፉ የሚገርም ባይሆንም፣ “እንተራረዳለን፤ እንጨራረሳለን፤ ደመ-ከልብ እናደርጋቸዋለን፤ መቀመቅ እናወራደቸዋለን”፣ ወዘተ. የሚሉ ዛቻዎች ሕጋዊ በሚባሉ የመገናኛ ዘዴዎች ላይ ጭምር በጩኸት እየተስተጋቡ የዕልቂት ቅስቀሳ ያለ ከልካይ መደረጉ አሳሳቢና እጅግ አደገኛው ነገር ነው። በዚህ ግርግር ውስጥ ኹኔታዎችን የአማራና የትግሬ እንዲሁም የኹለት ኦርቶዶክስ ሕዝቦች ፍልሚያ አስመስለው ትንታኔ እየሰሩ፣ ራሳቸውን የአንዱ ደጋፊ አስመስለው ለዕልቂት መነሳሳትን የሚያበረታቱና መጨራረስን ለችግሮች ኹሉ የመፍትሔ ምንጭ አስመስለው የሚሰብኩ ግለሰቦች መኖራቸው ሊስተዋል የሚገባው ጉዳይ ነው።

እያንዳንዱ ግለሰብ ጥርጣሬውን ይሁን ተጨባጭ የሆነ የአደጋ ፍንጭ ሲመለከት ጉዳዩን ወደ ሕግ አስከባሪ ተቋማት በማድረስ ጉዳዩ ተጠንቶና እስከ ሥር መሠረቱ ተመርምሮ አደጋው የሚወገድበትን መንገድ እንዲፈለግ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ሲገባው፣ ራሱ ዕርምጃ ወሳጅ መሆኑ የግል ጥላቻ ጠኔን ከመሙላት በስተቀር ለአገርና ለሕዝብ የሚፈይደው ነገር አይኖርም። ችግሮች ሲከሰቱና ጥርጣሬዎች ሲኖሩ የአሰቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን ተከትሎ የአገርንና የሕዝብ ደኅንነት ለመጠበቅ መተባበር ተገቢ ነው።

የአማራ ሕዝብ የሕልውና አደጋ የተጋረጠበት መሆኑ ግልጽ ነው። አንዳንድ ባለሥልጣናት፣ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች አዲስ አበባና በውጭ አገራት ተቀምጠው የአማራ ሕዝብ ጥላቻ እንዲጨምር፣ በጭካኔ እንዲነሳሳና ጠላቶቹን በጦር ሜዳ ብቻ ሳይሆን በየጎረቤቱም እየፈለገ ግድያዎችን እንዲፈጽም ሲወተውቱ ይሰማሉ። ነገር ግን፣ አማራ ሕልውናውን በዚህ መንገድ እንዴት እንደሚያስጠብቅ ግልጽ ስትራቴጂ ማስቀመጥ አይችሉም። ህወሓት በ1983 በስመ ኢሕአዴግ በርካታ ጀሌ ቡድኖችን አስከትሎና አሰልፎ ወደ ሥልጣን እንደገሰገሰው ሁሉ፣ አሁን ደግሞ የኦሮምያ፣ የጉምዝ፣ የጋምቤላ፣ የአፋር፣ የአገው፣ ቅማንት፣ ወዘተ. ሕዝብ ወኪል ነን የሚሉ ቡድኖችን በማሰለፍ በነዚህ ቡድኖች አማካኝነት ደጋፊዎቻቸው አማራውን በጠላትነት እንዲፈርጁትና በክልሉ ውስጥም ሆነ ከክልሉ ውጭ እንዲያጠቁት ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። ይህ አካሄድና የብልጽግና መንግሥት የጦርት አካሄድ የአማራ ሕዝብ ለመልከ ብዙ ሴራና ለችግር የተጋለጠ፣ የመረረና ረዥም ሕልውናን የማስጠበቅ ሥራ የሚጠብቀው መሆኑ በግልጽ ለመረዳት የሚያስችል ነው።

አማራው ሕዝብ ወገናዊነት የሚሰማውና በሳል አመራር የሌለው መሆኑን፣ ክልሉ ከ1983 ጀምሮ የአማራ ሕዝብ መሪ ተብለው ለአማራ ሕዝብና ለክልሉ በጠላትነት እስከ መሰለፍ የደረሰ ተላላኪነትን የተለማመዱ ራስ ወዳዶች በበዙበት አመራር መጫወቻ ሆኖ የኖረ መሆኑ ታሳቢ ተደርጎ፣ ራስን የማዳን ትግሉን መምራት ይገባል። እውነተኛ በሆነ መንፈስ የአማራን ሕዝብ አደራ መቀበል የሚችሉ መሪዎች በኩራዝም ቢሆን ተፈልገው ለአማራው ሕዝብ ጥብቅና መቆም አለባቸው። እነዚህ አመራሮች ከስሜታዊነት ርቀውና ሕዝብን ሳይሆን በሕዝብ ስም በጠላትነት የተነሱበትን ወገኖች ለመፋለም አማራውን ማዘጋጀት ይገባቸዋል።

ግዛቸው አበበን በዚህ ኢሜል አድራሻቸው (gizachewabe@gmail.com) ማግኘት ይችላሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 159 ሕዳር 11 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com