የእለት ዜና

“ክትባትን በተመለከተ በማኅበረሰቡ የሚነሱ የተለያዩ ብዥታዎች አሉ”

ቤተማሪያም አለሙ ይባላሉ። በጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ጀንደር ፎር ኮሚዩኒኬሽን ፕሮግራም የሚባል ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ ምክትል ዳይሬክተር ሆነው ላለፉት ሰባት ዓመታት በማገልገል ላይ ይገኛሉ። የማኅበረሰብ ጤና ባለሙያ የሆኑት ቤተማሪያም፣ በሕክምናው ዘርፍ ከ20 ዓመት በላይ ዩ. ኤስ. አይ. ዲ.ን በመሳሰሉ በተለያዩ ዓለም አቀፍና በሌሎች አገር በቀል ግብረ-ሠናይ ተቋማት ውስጥ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው። በእናቶች ጤና፣ በሥርዓተ ምግብ ላይ፣ እንዲሁም አሁን አሳሳቢ ከሆነው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በርካታ ሥራዎችን በመሥራት ይታወቃሉ። ከሰሞኑ በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚጀመረው የኮቪድ የክትባት ዘመቻ፣ ሥልጠና ሲሰጡ ከቆዩት እኚህ ምሁር ጋር የአዲስ ማለዳው ቢኒያም ዓሊ ቆይታ አድርጓል።

ሰሞኑን በአገር አቀፍ ደረጃ ስለሚጀመረው የኮቪድ ክትባት ዘመቻ አጠቃላይ ዓላማ ቢነግሩን?
እንደሚታወቀው ቮሮና ቫይረስ አገራችን ውስጥ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ በርካታ ልናጣቸው የማይገቡ የማኅረሰብ ክፍሎችን አጥተናል። ይህ የክትባት መርኃ ግብሩ የመጣው ከዚህ በፊት ስንሠራቸው የነበሩ የመከላከል ሥራዎችን የበለጠ ለማጠናከር ስለሚረዳ ነው። ስለዚህ፣ ከዚህ በፊት ስንሠራቸው የነበሩ የመከላከል ሥራዎች ላይ ይህ እንደ ተጨማሪ የመከላከል ሥራ አብሮ እየተሠራ ያለ እንቅስቃሴ ነው። ይህ ክትባት እንደሚታወቀው በብዙ አገሮች እየተሠጠ ያለ የመከላከያ ክትባት ነው። ክትባቱ እንደየአገሮቹና የክትባቱ ዓይነት ይለያያል። ነገር ግን፣ ከ18 ዓመት በላይ የሆነ ማንም ግለሰብ ይህንን የኮቪድ ክትባትን መውሰድ ይችላል።

አገራችን ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት ባገኘችው ዕርዳታ የተለያዩ ክትባቶችን ለመስጠት እንዲያስችል የተዘጋጀ ዘመቻ ነው ከኅዳር 13 ጀምሮ የሚሰጠው። ዘመቻ ያልንበት ምክንያት አንደኛ፣ ክትባቱ አጭር የአገልግሎት ጊዜ ስላለው ማለትም የቆይታ ጊዜው አጠር ያለ ስለሆነ ቶሎ ተደራሽ ለሚሆኑ የማኅበረሰቡ ክፍሎች ማዳረስ ስላስፈለገ ነው በዘመቻ መልክ እንዲሰጥ ማድረግ ያስፈለገው።

የት የት ነው ክትባቱን ለመስጠት የታሰበው?
ክትባት ዘመቻው አገር አቀፍ ነው። ከተወሰኑ የደኅንነት ችግር ካለባቸው አካባቢዎች ውጭ በኹሉም ቦታዎች ክትባቱ ይሰጣል። ጤና ጣቢያ፣ ሆስፒታሎችና መደበኛ የክትባት ጣቢያዎች፣ እንዲሁም በጊዜያዊነት በሚቋቋሙ የክትባት ጣቢያዎች ውስጥ ይሰጣል።

በምን ያህል ጊዜ ይጠናቀቃል ብላችሁ ትገምታላችሁ?
የክትባት ዘመቻው ለ10 ቀን ነው የሚቆየው። በብሔራዊ ደረጃ ዘመቻው የሚጀመረው ከሰኞ ኅዳር 13 ጀምሮ ቢሆንም፣ አስቀድመው የጀመሩ አንዳንድ ከተሞች አሉ። አዲስ አበባና ድሬዳዋ ቀድመው ጀምረዋል። ሥርጭቱ ለኹሉም ክልሎች እኩል የደረሰ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ቀን አብዛኞቹ እንዲጀምሩ ታቅዷል። በኹሉም ክልሎች በተመሳሳይ ቀን ያልቃል ተብሎ ይጠበቃል።

እስከዛሬ ሲሠጥ ከነበረው ተለይቶ በዘመቻ መልክ እንዲሰጥ የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው?
የአሁኑን ልዩ የሚያደርገው አገራችን ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገሮች በቁጥር ሻል ያለ የክትባት መጠን ስላገኘች፣ አሁን ለኹሉም ማዳረስ አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘነው ነው በዘመቻ መልክ ለማድረግ የተወሰነው። የአገልግሎት ጊዜያቸውም አጭር በመሆኑም ነው ውሳኔው የተላለፈው። በመደበኛነት የማናደርገው ክትባቱ ለአገራችን አዲስ እንደመሆኑ የማኅበረሰቡም ግንዛቤ አናሳ ስለሆነ በዘመቻ መልክ አድርገን የግንዛቤ ማስጨበጫውንም በዛው መልክ ብናስኬደው ውጤታማ ይሆናል ብለን ስላመንን ነው። ኹለተኛ፣ በመደበኛነት የምንሠራቸው በርካታ ሥራዎች ስላሉ እነሱን እንዳይጋፋ ቶሎ ብሎ ክትባቶቹን ሰጥቶ ወደሌሎቹ የጤና አገልግሎቶች መሄድ ስላለብን ነው።

ክትባቶቹ ምን ምን ዓይነት ናቸው?
አብዛኞቹ ከዚህ ቀደም ሲሰጡ የነበሩ የክትባት ዓይነቶች ናቸው አሁን የሚሰጡት። ለምሳሌ አስትራዜኒካ፣ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን፣ ሲኖፋርም አሉ፤ አሁን ደግሞ ፋይዘርም ተጨምሯል። እነዚህ ናቸው አሁን በዋነኝነት የሚሰጡት። እነዚህ ኹሉም ክትባቶች የመከላከል አቅማቸው ተመሳሳይ የሆነ፣ ነገር ግን በተለያዩ አገሮችና ፋብሪካዎች የተመረቱ ናቸው። ስማቸው ይለያይ እንጂ አገልግሎታቸውም ሆነ የመከላከል አቅማቸው ተመሳሳይ ነው።

በኹለት ዙርና በአንድ ዙር የሚሰጡትን እንዴት ነው የምታከፋፍሉት?
ካሉት ክትባቶች ውስጥ አንዱ ብቻ ነው በአንድ ዶዝ ብቻ የሚሰጠው። ይህም ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የሚባለው ነው። ሌሎቹ ሦስቱ በኹለት ዶዝ የሚሰጡ ናቸው። የየራሳቸው የጊዜ ሰሌዳ ስላላቸው አንደኛው ዙር ከተሰጣቸው በኋላ ለኹለተኛው ዙር የሚቀጠሩበት ጊዜ ይኖራል። በክትባት ቦታው ላይ አራቱም አይነት ክትባቶች ስለሚኖሩ ሕብረተሰቡ የፈለገውን አይነት መርጦ የመከተብ መብት አለው።

በኹለተኛው ዙር ለሚከተቡ የሚያስፈልጋቸው ክትባት ተቀማጭ ይደረጋል ወይስ ጊዜያቸው እስኪደርስ በዕርዳታ ለማግኘት ነው የሚሞከረው?
የታሰበው፣ ያሉትን ኹሉንም ክትባቶች አሁን ለመስጠት ነው። ይህ የታሰበበት ምክንያት በቀጣይ የሚያስፈልጉት ዶዞቹ በዕርዳታ እንደሚገኙ ስለሚረጋገጥ ነው። ምክንያቱም፣ አሁን ካሉት ለጋሽ አገራት፣ እንዲሁም ኮቫክስ የሚባለው ዓለም አቀፍ የክትባት እንቅስቃሴውን የሚከታተለውና የሚመራው ተቋም በኩልም ክትባቱ ተደራሽ እንዲሆንና በበቂ ሁኔታ እንዲገኝ ቃል ስለተገባ ነው ይህንን እየሰጠን ያለነው። ስለዚህ አሁን በእጃችን ያሉ ክትባቶች በሙሉ አንደኛ ዙር ለሚከተቡም ሆነ ከዚህ ቀደም የመጀመሪያውን ዙር ተከትበው ኹለተኛውን ለሚጠባበቁ የሚሰጥ ነው።

ባለፈው ዘግይቶ እንደነበረው ወይም የለም የሚባልበት አጋጣሚ እንዳኖር ምን ታስቧል?
ዕጥረት ይኖራል ብለን አንጠብቅም። ምክንያቱም ባለፉት ጊዜያት ክትባቱን ከሕንድ አንድ ተቋም ብቻ እንጠብቅ ስለነበረ፣ በሕንድ አገር የተፈጠረው የኹለተኛው ማዕበል ወረርሽኝ በፈጠረው ችግር ምክንያት ነበር የዘገየው። አሁን ግን ከተለያዩ አገራት ስለሆነ የምናገኘው እንዲህ አይነት ችግር ይከሰታል ብለን አንጠብቅም።

ጥያቄዎቹን ኹልጊዜ በተከታታይ ስለምናቀርብ ዕጥረቱ አይፈጠርም። እንዲህ አይነት ክትባቶች በዓለም ደረጃ ሲሰሩ አብሮ የየአገሩ ዕቅድ ስለሚቀርብ፣ በቀረቡ ዕቅዶች መሠረት ስለሚሠራ የክትባቱ እንቅስቃሴ ችግር ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም። የዓለም ጤና ድርጅትን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ስለሚሳተፉበትና እነሱም ከዕቅድ አወጣጡ ጀምሮ ስለሚያግዙ ችግር ይገጥማል ተብሎ አይጠበቅም።

ምን ያህል የሕብረተሰብ ክፍል ይከተባል ብላችሁ ትጠብቃላችሁ?
እውነት ለመናገር እንደክልሎቹ አቅምና ተደራሽ እንደሚያደርጓቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ነው የተከፋፈለው። እርግጠኛ ሆኜ ትክክለኛ ቁጥሩን አሁን መናገር ባልችልም፣ እያንዳንዱ ክልል የራሱ ዕቅድ ስላለው በዛ መሠረት ነው እየተሰጠ ያለው። እኔ እንዳለኝ መረጃ በኹለቱ ዙሮች በግምት ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ክትባት ለመስጠት ታቅዷል።

የተከታቢው መጠን የሚወሰነው በክልሎች የእንቅስቃሴ መጠን ነው። የቅስቀሳ ሥራው ይወስነዋል ማለት፣ የክልል ጤና ቢሮዎቹ ለክትባቱ የሚሆን አገር አቀፍና ክልል አቀፍ የሆኑ ግብረ ኃይሎች ተቋቁመዋል። እነሱ የተለያዩ ፕሮግራሞችን አቅደዋል። አንደኛው ማኅበረሰቡን አስተባብሮ ከማንቀሳቀስና ግንኙነት ከመፍጠር ጋር በተገናኘ የሚሠራው ነው። የማኅበረሰቡን አመለካከት ለመቀየርና ተነሳሽነት እንዲኖር የሚሠሩ ሥራዎች ናቸው። የጤና ቢሮውና ግብረ ኃይሉ ብቻ ሳይሆን፣ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችም አስተዋጽዖ ሊያደርጉ ይገባል። ለምሳሌ፣ የሚዲያ ተቋማት ማኅበረሰቡን በማንቃት ትልቅ ሥራ ይጠበቅባቸዋል። የኃይማኖት አባቶችም፣ እንዲሁም ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ለዘመቻው መሳካት መሥራት ይጠበቅባቸዋል። የተለያዩ ተቋማትና መሥሪያ ቤቶችም በሥራቸው ያሉ ሠራተኞች እንዲከተቡ በማድረግ የቅስቀሳ ሥራውን ማገዝ ይኖርባቸዋል። ዘርፈ ብዙ የቅስቀሳ ሥራዎችን ስንሠራ ብቻ ነው ዕቅዱን ልናሳካ የምንችለው። ጠንክሮ የሚሠራ ግብረ ኃይል አቋቁመን ከሠራን ነው በእርግጠኝነት ክትባቱን በታሰበለት ጊዜ እንደታሰበው ለመስጠት የሚቻለው።

ስለክትባቱ ሥልጠና የሚሠጠው ለማን ነው?
ከክትባት ሰጪ ባለሙያዎች ጀምሮ ዘመቻውን የሚመሩት የጤና አገልግሎት ሰጪዎች ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች፣ እንዲሁም ዘመቻውን እንዲያግዙ የሚደረጉ የተለያዩ አካላት ናቸው። የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት የኃይማኖት መሪዎችን ጨምሮ የሚዲያ ሰዎችም እንዲሰለጥኑ ተደርጓል። የፖለቲካ አመራሩም ግንዛቤ እንዲኖረውም ተደርጓል። ከነዚህ በተጨማሪም በየከተሞቹ እየተዞረም የሚቀሰቀስባቸው መልዕክቶችንም አዘጋጅተናል። ለሬዲዮና ቴሌቪዥን የሚሆኑ መቀስቀሻ መንገዶችም ተለይተዋል። በየከተማው የሚለጠፉ ትልልቅ ባነሮችንም አዘጋጅተናል። በእነዚህ አጠቃላይ ሥራዎች ነው የተሻለ ውጤት ይመጣል ብለን የምናስበው።

ክትባቱ የሚሠጠው በፈቃደኝነት ነው ወይስ አስገዳጅነት ባለው መልኩ?
በአሁን ሰዓት በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ነው። እያንዳንዱ ግለሰብ ከበሽታው ይጠብቀኛል ብሎ አምኖበት የሚከተበው ነው መሆን ያለበት። እንደሚታወቀው ሦስተኛው የወረርሽኙ ማዕበል አልፎ ወደ አራተኛው እየሄድን ነው። ወረርሽኙ ከፍ ዝቅ እያለ ብዙ ሰዎችን እያጠቃ እንደሆነ እናውቃለን። በቀጣይ ብዙ ሰዎችን ሊያሳጣን የሚችል ሆኖ ሊመጣ ስለሚችል ያንን ለመከላከል እንድንችል ኹሉም ማኅበረሰብ በፈቃደኝነት መከተብ ነው ያለበት።

ክትባን በተመለከተ በማኅረሰቡ የሚነሱ የተለያዩ ብዥታዎች አሉ። እነዚህ የተሳሳቱ መሆናቸውን በማወቅ ትክክለኛውን መረጃ ከተገቢው ምንጭ በማግኘት የሚያስፈልገንን ክትባት አምነን መከተቡ በጣም ወሳኝ ነገር ነው። ለምሳሌ ከሚነሱት ብዥታዎች መካከል፣ ያደጉ አገሮች የአፍሪካን ሕዝብ ለመቀነስ አስበው ነው ያዘጋጁት እያሉ የሚያነሱ አሉ። እነዚህ አገሮች ክትባቶቹን የሠሯቸው ለራሳቸው ሕዝቦች ነው። ለምሳሌ ቻይናን ብንወስድ፣ የሰራችው ሲኖፋርም ከ1.4 ቢሊዮን ዜጎቿ 1.1 ቢሊዮን የሚሆኑትን ከትባበታለች። እነአሜሪካም ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆኑ ዜጎቻቸውን በነዚሁ ክትባቶች ከትበዋል። እንደአገር የመከላከል ብቃታቸውን ያጎለበቱባቸውን ክትባቶች ነው እኛም የምንጠቀመው። በክትባት መከላከል የምንችላቸውን ወረርሽኞች መቆጣጠር የሚቻለው ቢያንስ ከዜጎች 80 በመቶውን መከተብ ከተቻለ እንደሆነ ይታመናል። እነሱ እዛ ደረጃ ሲደርሱ እኛ አንድ በመቶ የሚሆነውን ነዋሪ ባለመከተባችን ተጎጂ ነው የምንሆነው።

በክትባቱ ዙሪያ ላይ ጥያቄ ያላቸውም ሆኑ መረጃን የሚፈልጉ የነፃ የስልክ ቁጥር 952ን ተጠቅመው ማናቸውንም ነገር መጠየቅ ይችላሉ። በዚህም ካልሆነ አቅራቢያ ያለ የጤና ባለሙያን በመቅረብ መጠየቅ ይቻላል። በዚህ መንገድ ኹሉም በፈቃደኝነት እንዲከተብ ነው የምንሠራው።

በአፍሪካውያንና በምዕራባውያን ዘንድ ያለው ከፍተኛ የሆነ የተከታቢ ቁጥር ልዩነት በአቅም ማነስ ብቻ ነው የመጣው ወይስ ሌላም ምክንያት አለው?
ዋናው ነገር አቅም ነው። እነሱ አቅሙ ስላላቸው ማምረትም ሆነ መግዛት ችለዋል። ኹለተኛው ደግሞ እነሱ ጋር ያለው የማኅበረሰቡ የንቃተ ህሊና ደረጃ ነው። ስለ ሕክምና ያላቸው ዕውቀትም ሆነ አመለካከት ከአፍሪካ የተሻለ ነው። በሌላ በኩል፣ የሞት ዓይነቱንም እነሱ በደንብ አይተውታል። ብዙ ወገኖቻቸውንም ስለጨረሰባቸው የክትባቱን ጥቅም በደንብ የተረዱት ይመስለኛል። እነዚህ ዓይነት ምክንያቶች ተደራርበው ነው እነሱ ይህን ያህል ሊከተቡ የቻሉት። ወደእኛ ስንመጣ ግን ተግዳሮቶቹ ብዙ ናቸው። አሁን ክትባቱን በብዛት እያገኘንና ብዙ ሰው እየተከተበ በሔደ ቁጥር ሌላውም የማኅበረሰብ ክፍል ማይከተብበት ምክንያት አይኖርም።

ባለፈው መምህራን ካልተከተቡ ማስተማር አይችሉም ሲባል እንደነበረው፣ በእኛ አገር እንደምዕራባውያኑ አስገዳጅ መንገዶች ያዋጣሉ ይላሉ?
ክትባትን በግድ ውሰዱ ማለት ከኮቪድ በፊትም የተለመደ ዓይነት አሠራር ነው። ግሎባል ሔልዝ በሚባለው ጽንሰ ሐሳብ አገሮች የራሳቸውን ማኅበረሰብና አገራቸውን ለአጠቃላይ ጤና ያሰጋኛል የሚሏቸው ጉዳዮች ላይ በአስገዳጅነት ሌሎች ወደእነሱ ሲገቡም ሆነ ዜጎቻቸው ሲንቀሳቀሱ እንዲህ አይነት አስገዳጅ ውሳኔዎችን ሊያስተላልፉ ይችላሉ። ለምሳሌ፣ ቢጫ ወባ የምንለውን ለመከላከል ማንም ሰው ወደተለያየ አገር ሲሔድ ያንን መከተቡን ማረጋገጥ ይቻላል። ይህ የተለመደ አሠራር ነው። አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት ተብለው የሚቀመጡ ጉዳዮች ላይ ማስገደድ አሁን የጀመረ አይደለም።

ከብዙ ማኅበረሰብ ጋር ቀጥታ የሥራ ግንኙነት ያለው ሰው፣ የሥራ ባህሪው ከብዙ ሰው ጋር የሚያገናኘው፤ እንቅስቃሴው ሥጋት ውስጥ የሚጥለው የማኅበረሰብ ክፍል መከተቡ ጥሩ ነው። ነገር ግን፣ ወደፊት ወረርሽኙ አስቸጋሪ ሆኖ ከተገኘ አስገዳጅ ሕጎች መውጣታቸው የማይቀር ነው። ለምሳሌ፣ አንድ የጤና ባለሙያ የማይከተብ ከሆነ ሌላውን እንዴት ሊያክም ይችላል? የባንክ ባለሙያንም የመሳሰሉ ከብዙ ሰዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው በአስገዳጅነት ተከተቡ ሊባሉ ይችላሉ።

አንከተብም ብለው የወሰኑ፣ ለምሳሌ አጥቢ እናቶች ስለሆንን ልንገደድ አይገባም የሚሉ ፍላጎታቸው ግንዛቤ ውስጥ የሚገባበት አሠራር ይኖራል?
እያንዳንዱ ሰው የራሱ የሆኑ የጤና ደረጃዎች አሉት። ነፍሰጡርና የሚያጠቡ እናቶች እንዲሁም ሌላ ተጓዳኝ ሕመም ያለባቸው ሰዎች፣ አለርጂን የመሳሰለ ችግር ያለባቸውን ሰዎች የመሳሰሉትን በተመለከተ ክትባቱን የሚሰጡ ሰዎች ተገቢውን ስልጠና ስለወሰዱ እነሱን በማማከር መውሰድ ያለባቸውና የሌለባቸውን መለየት ይቻላል። ሰዎች ክትባቱን ከመውሰዳቸው በፊት ይህን የመሳሰሉ ጉዳዮች ከተጣሩ በኋላ ነው (ምርመራዎች ባይደረግላቸውም) ክትባቱ የሚሰጣቸው። ክትባቱ ከጡት ማጥባት ጋር የተያያዘ ነገር የለውም። ሌላ ጉዳይ ካልኖራቸው በስተቀር የሚያግዳቸው ነገር የለም።

የተለያዩ ሰዎች አንከተብም የሚሉበትን ምክንያት ለማወቅ ያካሄዳችሁት ጥናት አለ?
አዎ፣ የተለያዩ ጥናቶች ይካሄዳሉ፤ እየተካሄዱም ነው። ከማኅበረሰቡ ጋር በምናደርጋቸው ውይይቶችም የምንሰማቸው አሉ። አሉባልታዎችና የተሳሳቱ ምልከታዎችንም በተለያዩ አጋጣሚዎች አንሰማለን። የሕዝብ ቁጥርን ለመቀነስ ታስቦ ነው ከሚሉት ጀምሮ፣ ክትባቱ አስተማማኝነቱ በጥናት የተረጋገጠ አይደለም የሚሉ፣ የደም መርጋት ያስከትልብናል የሚሉ፣ ከዕምነት አንፃርም ይህ የሠይጣን ሥራ ነው፣ የእግዚአብሔር ቁጣ ነው፣ በጸሎት ነው የሚወገደው የሚሉ፤ እንዲሁም 666 ነው እና ከማይክሮ ቺፕ ጋር የተገናኘ ነው የሚሉን የመሳሰሉ በርካታ ነገሮች አሉ። እነዚህን በተለያዩ ሚዲያዎች በምናስተላልፋቸው መልዕክቶች ምላሽ ለመስጠት እየተሞከረ ነው።

በተለያዩ መድረኮችም ጉዳዩን በማንሳት ሐሳቦቹ ትክክል አለመሆናቸውንና እውነተኛውን መረጃ ለመስጠት እየተሞከረ ነው። ለምሳሌ፣ የደም መርጋት ያመጣል የሚባለውን ብንመለከት፣ ክትባቱ የሚያስከትለው የደም መርጋት አጋጣሚ በጣም አናሳ ነው። አስትራዘኒካ ተከትቦ የደም መርጋት የሚጋጥመው 0.0004 በመቶው ነው። አንድ ሰው ሳይከተብ ቀርቶ ኮቪድ ቢይዘው ግን በሽታው የሚያስከትለው የደም መርጋት ዕድሉ ግን 16 በመቶ አካባቢ ነው። ይህ መከተብ እጅግ በጣም አዋጭ መሆኑን ነው የሚያሳየው። ከማይክሮ ቺፕ ጋር በተገናኘ የሚነሳውም፣ ማይክሮ ቺፑ ጠጣር የሆነ ቆዳ ሥር የሚቀበር ነው። ክትባቱ ግን ፈሳሽ ነው። ለሕፃናት ሲሰጡ ከምናውቃቸው ክትባቶች የተለየ አይደለም። እስከዛሬ ልጆቻችንን ተመሳሳይ ክትባቶችን ስናስከትብ እንዲህ አይነት ጥያቄዎችን ጠይቀን አናውቅም።

ማንኛውም መድኃኒትና ክትባት ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት የራሱን ሒደቶች አልፎ፣ ጥናቶች ተካሂዶበት በዓለም አቀፍ ተቋማትና በአገራት ተፈትሾ ነው ወደ አገልግሎት የሚገባው። ይህ ማለት ግን ከአገር አገር አይለያዩም ማለት አይደለም። አምፒሲሊን እንኳን ስንገዛ የጀርመን፣ የሕንድ፣ የጃፓን ተብሎ ጥራቱ ይለያያል እንጂ ኹሉም መሥራቱ ተረጋግጦ ነው። ክትባትም እንዲሁ የታለመላቸውን የመከላከል ዓላማ ማሳካታቸው ተረጋግጦ ነው ሥራ ላይ እንዲውሉ የሚደረገው።

አንከተብም የሚሉን ብቻ ሳይሆን ሌላው እንዳይከተብ የሚቀሰቅሱትን ምን ለማድረግ ታስቧል?
እንዳትከተቡ ብለው የሚናገሩ ሰዎች ምን ዓላማ ይዘው ነው የሚለው መታየት አለበት። አንዳንዶች ጉዳዩን ከፖለቲካ ጋር የሚያይዙት አሉ። ሌሎች ደግሞ ከራሳቸው ግንዛቤ ተነስተው ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሰዎች ማሳመኛ ብለው የሚሰጡዋቸው ማስረጃዎች ምንድን ናቸው የሚለውን በደንብ መመልከት ያስፈልጋል። ማሳመኛዎቹ ምን ያህል ውሸት መሆናቸውን እያሳየን መሥራት አለብን። ማኅበረሰቡ ትክክለኛውን መረጃ ማግኘት እስከቻለ ድረስ እኛም የሚጠበቅብንን እስከሠራን ድረስ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ችግር ይፈጥራሉ ብዬ አላምንም። ይህ ቢሆንም ግን፣ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ለምን እንዲህ እንደሚደርጉ መነጋገሩ አስፈላጊ ነው። ሚዲያውም በዚህ ረገድ ያለውን ብዥታ በማጥራት ኃላፊነቱንም መወጣት ይችላል ብዬ አምናለሁ።

በመጨረሻ፣ ምርመራን በተመለከተ የሚመረመረው ቁጥር እያነሰ ነው ከመባሉ አኳያ፣ ለክትባቱ ምርመራ አስፈላጊ ነው?
ክትባቱን ለማግኘት ግድ መመርመር አያስፈልግም። ነገር ግን፣ አንድ ግለሰብ ሊከተብ በሚሄድበት ጊዜ ኮቪድና ኮቪድ መሰል ምልክቶች ካሉበት ይጣራል። ምልክቶቹ ካሉበት እንዲቆይ ይደረግና ሌሎች ምርመራዎችን እንዲያደርግ ይደረጋል። ከዛ ባለፈ ግን መመርመር የሚጠቅመው አንደኛ፣ ሕመሙ ራሳችን ጋር ካለ ለቀሪ ቤተሰባችን እንዳናስተላልፈው ነው። ራሳችንን አግልለን ሌላውን እንዳናጋልጥ ለመጠንቀቅ ነው። ሌላው በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን ኃላፊነት ያለብን እንደአገርም ማሰብ አለብን። በስተመጨረሻ፣ ሌላውን መጠበቅ ብቻም ሳይሆን፣ ለራሳችንም ተገቢውን ዕርዳታ እንድናገኝ ስለሚያስችለን መመርመሩ ጠቃሚ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 159 ሕዳር 11 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com