የእለት ዜና

ከአጎዋ መታገድ የሚያስከተለው የኢኮኖሚ ጫና ምን ያህል ነው?

ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተባባሰ በመጣው ጦርነት ሳቢያ በተለይ ከምዕራቡ ዓለም የሚደርስባት ጫና የበረታ ነው ሲሉ ብዙዎች ይናገራሉ። በዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል በሚል አሜሪካም እንዲሁ በተለያዩ ጊዜያት ማስጠንቀቂያዎችን ስትሰጥ ቆይታለች።
ይህ ከእውነተኛ የሰብዓዊ መብት ተቆሪቋሪነት የመነጨ ሳይሆን፣ አውሮፓውያኑም ይሁን አሜሪካ ፍላጎታቸው እና ጥረታቸው ህወሓትን ለመታደግ ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው። ምክንያቱ ደግሞ ከፍተኛ ሥራ አጥነት፣ መፈናቀል፣ ግጭቶች እንዲሁም ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች በተጋረጡባት ኢትዮጵያ ላይ ሌላ ማዕቀብ መጫን ዜጎችን በጦርነቱ ከሚደርስባቸው የማይተናነስ ሌላ ሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ እንደሚከታቸው ጫና ለሚያደርጉ አገራት ግልጽ በመሆኑ ነው።

ይህም ሆኖ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ የጦር መሣሪያ ግዥ እንዳትፈጽም ከመከልከሏ በተጨማሪ፣ በኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ ያሳዳራል ተብሎ ሥጋት ፈጥሮ የነበረው ከአጎዋ መታገድም ተፈጻሚ የሚሆን ከሆነ ተግባራዊ ለመሆን ቀናት ይቀሩታል።

አጎዋ (African Growth and Opportunity Act) የአፍሪካ አገሮች ከተረጅነት ወጥተው በራሳቸው ምርት ተወዳዳሪ በመሆን ተጠቃሚ እንዲሆኑና ራሳቸውን እንዲችሉ በሚል ከአፍሪካ የሚላኩ ምርትና አገልግሎቶች አሜሪካ ከቀረጥና ከታሪፍ ነጻ እንዲገቡ በሚል ነበር በግንቦት ወር 1992 የተጀመረው። በዚህም ከሰሐራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት እስከ መስከረም ወር 2018 ድረስ በአንድ ወገን ፍላጎት ላይ ብቻ የተመሠረተ የዚህ ነጻ ገበያ ተጠቃሚ ሆነው እንደሚቆዩ ይጠበቃል።

ይህን የንግድ ሥራ ዕድል ተጠቅመው በርከት ያሉ የአፍሪካ አገራት ኢኮኖሚያቸውን ሲያሻሽሉ፣ ኢትዮጵያም ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር በተጨማሪ ባለፈው ዓመት ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አግኝታለች ተብሏል። ይህን ተጠቅማም 4 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት መሳብ የቻለች መሆኗም እንዲሁ የሚታወቅ ነው።

ሆኖም አሜሪካ፣ ኢትዮጵያ ከአጎዋ ገበያ ተጠቃሚነት ልትሰርዛት ትችላለች የሚለው ሥጋት ዕውን ሆኖ የነጻ ገበያ ተጠቃሚነቷን ካጣች በርካታ ዜጎች ሥራ አጥ እንደሚሆኑ ይነገራል። የምታጣው ገቢም እንዳለ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ከአጎዋ ገበያ መታገድ በዋናነት የሚፈጥረው ጫና በዜጎች ላይ የሚያስከትለው ሥራ አጥነት እና አገሪቱ ታገኝ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ እንድታጣ ማድረግ ቢሆንም፣ ታስቦበት ከተሠራ ግን የሚያስከትለው ጫና በጣም አናሳ መሆኑን እና ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ መልካም ጎን እንዳለውም ምሁራን ይናገራሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር የሆኑት አለማየሁ ገዳ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ሐሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ አጋርተዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ በአጎዋ በኩል የሚላኩ ምርትና አገልግሎት ላይ ጥራታቸውን ማሻሻል ወይም ቀድሞ ይሸጡ በነበረበት ዋጋ መሸጥ ከተቻለ ኢትዮጵያ ጉዳት አይደርስባትም ብለዋል። አጎዋ ማለት በገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን በአማካይ 15 በመቶ የሚያግዝ ነው። ይህም በአጭሩ የአጎዋ አባል ያልሆነች አገር አንድን ዕቃ በ115 ዶላር የምትሸጥ ከሆነ፣ የአጎዋ ገበያ አባል የሆነች አገር ያንኑ ዕቃ በ100 ብር መሸጥ ትችላለች። ይህም በቀላሉ ገዥ እንድታገኝ ያስችላታል።

ኢትዮጵያም ከአጎዋ ከተሰረዘች የምታጣው ይህችን 15 በመቶ የገበያ ዕድል በመሆኑ፣ ምርት ጥራት ላይ ከተሠራ፣ አምራቾች ትርፋቸውን የተወሰነ መቀነስ ከቻሉ፣ መንግሥትም የተወሰነ ድጎማ ካደረገላቸው እና ሌላ የገበያ አማራጭም ማየት ከተቻለ ተፅዕኖውን በመጋራት ማስወገድ ይቻላል ባይ ናቸው። ከአጎዋ መታገድ በዋናነት የሚያስከትለው የኢኮኖሚ ሳይሆን የፕሮፖጋንዳ ጫና ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ፣ ይህን ታሳቢ በማድረግ ከልብ ከተሠራ በአጎዋ በኩል የኢትዮጵያን ምርት የሚቀበሉ ደንበኞች እንኳን ሌላ ደንበኛ መልመድ ስለማይፈልጉ በዚያው ሊቀጥሉ ይችላሉ ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በአጎዋ በኩል ለአሜሪካ ገበያ የምትልከው ከዘጠና በመቶ በላይ ጨርቃ ጨርቅ መሆኑን ገልጸው፣ በአጠቃላይ ከውጭ ንግድ ከምታገኘው ገቢ በጨርቃ ጨርቅ የምታገኘው ደግሞ ስድስት በመቶ ብቻ ነው ብለዋል። በአጎዋ በኩል በዋናነት ጨርቃ ጨርቅ እንዲሁም የቆዳ ውጤቶች፣ ጥራጥሬና ቡና ተልኮ በአንድ ዓመት የተገኘው ገቢ 260 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ነው። ይህም አገሪቱ በዓመት በአማካይ ከውጭ ገበያ ከምታገኘው 3 ቢሊዮን ዶላር ገድማ 260 ሚሊዮን ዶላር ያን ያህል ጥቅም ነው ብሎ መናገር ስለማይቻል፣ ከአጎዋ ገበያ የሚቀርባት ገቢ ብዙም እንዳልሆነ ነው ያስረዱት። ከዚህ ይልቅ ከሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የቡና፣ ሰሊጥ እና ጫት ንግድ ቢቆም ነው የበለጠ ጉዳት የሚያደርሰው ይላሉ።

በሌላ በኩል፣ አሜሪካ በአጎዋ ስም ለዜጎቿ የአፍሪካን ጥሬ ዕቃና ምርት በርካሽ ዋጋ እንዲያገኙ በማድረግ ከኢትዮጵያ የበለጠ የምትጠቀመው ራሷ ስለሆነች እገዳው ተፈጻሚ ላይሆን ይችላል የሚሉ አሉ። ፕሮፌሰር አለማየሁ ይህን አስመልክተው ሐሳብ ሲሰጡ፣ 20 ትሪሊዮን ዶላር ዓመታዊ ካፒታል ያላት አገር፣ ከኢትዮጵያ የ260 ሚሊዮን ዶላር ምርትና ጥሬ ዕቃ ማግኘት ትርጉም የለውም። ከዚያ ይልቅ አጎዋ ለአሜሪካ ትልቅ የውጭ ፖሊስ ዋና ማስፈጸሚያዋ ስለሆነ እገዳውን ተፈጻሚ ላታደርገው ትችላለች ብሎ ማስብ ይሻላል ሲሉ ገልጸዋል።
ከአጎዋ መሠረዝ ምክንያት ከ60 እስከ 65 ሺሕ የሚደርሱ ዜጎች ሥራ አጥ ይሆናሉ ብለው የሚገምቱት የኢኮኖሚክስ ምሁሩ፣ ከአጎዋ መሠረዝ የሚያስከትለው ትልቁና ዋናው ጊዚያዊ ጫናም ይህ ነው ብለዋል። ነገር ግን፣ ከላይ በተገለጸው መሠረት የአገር ውስጥና የአህጉር ገበያን መጠቀም ከተቻለ፣ ምርትና አግልግሎቶች ላይም ጥራታቸው ላይ በመሥራት ከአጎዋ ውጭ በገበያው ላይ ተወዳዳሪ መሆን ከተቻለ፣ ሠራተኞቹን መታደግ ይቻላል የሚል ዕምነት አላቸው። በሠራተኞች ላይ የሚያደረስው ጫናም በኮሮና ምክንያት ከደረሰው ጫና የከፋ እንደማይሆን ነው የተናገሩት።

ይልቅ ይላሉ ፕሮፌሰሩ፣ አሜሪካም ሆኑ ምዕራባውያን ኢኮኖሚዋን ጫና ውስጥ በማስገባት ኢትዮጵያን መጉዳት ከፈለጉ ማድረግ የሚችሉትና በተጨባጭም ከፍተኛ ጉዳት ማድረስ የሚችሉበት ሌላ ዕቀባ አለ። ይህም ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክና ከአይ.ኤም.ኤፍ. የዕርዳታ ብድር እንዳታገኘ ካደረጉ ነው። ከዚህ አንጻር ባላሰብነውና ባልተዘጋጀንበት ጊዜ ስለተፈጠረ እንጂ ከአጎዋ መሠረዛችን የሚያስከትለው ጫና በጣም አናሳ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

ይህን ሐሳባቸውን ሲያብራሩ፣ ኢትዮጵያ በዓመት ወደ አገር ውስጥ የምታስገባው ምርትና አገልግሎት በአማካኝ ወደ 17 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል። ወደ ውጭ ገበያ ምርትና አገልግሎት በመላክ የምታገኘው ገቢ ደግሞ በአንጻሩ በአማካኝ 3 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነው። ስለሆነም የሚያስፈልጋትን ሸቀጣ ሸቀጥ ከውጭ ገበያ ለመሸመት ቀሪውን ወደ 14 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የሚሆነውን ገንዘብ የምታገኘው በዕርዳታና ብድር ነው ባይ ናቸው። ከ14 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋውን በውጭ አገር ከሚኖሩ ሐበሾች፣ 1.5 ቢሊዮን ዶላር የሚደርሰው ደግሞ ከተለያዩ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች በሚገኝ ዕርዳታ ይሸፈናል። ቀሪ ወደ 7.5 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነው 30 በመቶው ከቻይና 12 በመቶው ደግሞ ከዓለም ባንክና ከአይ.ኤም.ኤፍ. በሚገኝ የዕርዳታ ብድር የሚሸፈን መሆኑን አመላክተዋል። በዚህም ትልቁ አገራዊ የኢኮኖሚ ቀውስ የሚፈጠረው የአጎዋ መታገድ ሳይሆን ይህ ቢታገድ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም፣ ኢትዮጵያ ትልቁን እና ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነውን የንግድ ልውውጥ የምታደርገው ከእስያና ከጎረቤት የአፍሪካ አገራት ጋር ነው ያሉት አለማየሁ፣ ልውውጣችን 12 በመቶ ገደማ የሆነው የአሜሪካ ገበያ የሚያስከትልብን ጫና ቀላል ነው ብለውታል።
አውሮፓም ልክ እንደ አጎዋ ያለ የገበያ ሥርዓት ያላቸው መሆኑን ጠቁመው፣ ኢትዮጵያ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነውንና ኹለተኛውን ትልቅ የንግድ ልውውጥ የምታደርገው ከአውሮፓ ጋር በመሆኑ ይልቅስ እዚህ ላይ በደንብ መሥራት ያስፈልጋል ነው የሚሉት።

ፕሮፌሰር አለማየሁ በማጠቃለያቸው፣ አሜሪካ በዚህ ሥም በማስፈራራት ደካማ እና በጥቅም ላይ የተመሠረተ የውጭ ፖሊሲዋን የሚያስጠብቅላት መንግሥት መፍጠር ነው የምትፈልገው። የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ ወጣቱ ለአሜሪካ የተጋነነ መልካም ስሜት ነበር የነበረው፣ አሁን ግን ጥቅም እንጂ ወዳጅ የማትፈልግ አገር መሆኗን አውቆ አሁን ካልተማረ ዕድሜ ልኩን አይማርም። በቀጣይም ልክ እንደ አጎዋ ባልጠበቅነው መልኩ አንድ ነገር ፈጥረው ሊያስፈራሩንና ሊያስጨንቁን ይችላሉ። ስለዚህም ከአሁኑ በመማር ፖሊሲ ስናወጣም በደንብ እንድናጤንና ተጋላጭነትን እያሰብን እንድናዘጋጅ ይረዳናል። ከገባን ባለመታገዳችን ከምናገኘው ገቢ ይልቅ፣ በመታገዳችን በመማር የምናተርፈው ትርፍ የበለጠ ነው ብለዋል።

የጂጂ ሱተር ጋርመንት ባለቤትና ማኔጂግ ዳይሬክተር የሆኑት፣ በተለይ ከኮሮና ቫይረስ መከሰት በፊት በስፋት ጨርቃ ጨርቅ ለውጭ ገበያ ሲያቀርቡ እንደነበር የገለጹት ጌታቸው ቢራቱ፣ የአጎዋ ነጻ ገበያ ከተጀመረ ጀምሮ ጉዳቱ እንጂ ጥቅሙ እንደማያመዝን ስለማውቅ በአገረ ውስጥም ይሁን በአገር ውጭ በሚካሄዱ ስብሰባዎች ላይ አላስፈላጊ መሆኑን ስናገር ነው የቆየሁት በማለት ሐሳበቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ምርቶቻችን አገር ውስጥ እና ሌላ አገር ገበያ ላይ ከሚሸጡበት ዋጋ ወርደው በአጎዋ ገበያ እንደሚሸጡ በተጨባጭ አውቃለሁ ያሉት ጌታቸው፣ እስካሁን ያንን ምርት ለአፍሪካ ገበያ ብናቀርበው ኖሮ በእርግጠኝነት ከዚያ የበለጠ ገቢ እናገኝ ነበር ሲሉ ገልጸዋል።
በአጎዋ ገበያ አህጉራችን ውስጥ ከተራነት ተነስተው ባለጸጋ የሆኑትም አፍሪካውያን ሳይሆኑ የእነሱ(የውጮቹ) ኩባንያዎች ናቸው፣ ለዚሁም የአፍሪካ መሪዎች በየጊዜው እያለቀሱ ሲለምኑ እያየሁ ስቃወም ነው የኖርኩት ብለዋል። የምርት መጠናችን አነስተኛ መሆኑ እንጂ የምርት ጥራታችን የታወቀ ነው፤ ምርቶቻችንን ወደ አፍሪካ በመላክ ከፍተኛ ገቢ ማግኘት እንችላለን ነው ያሉት። ስለዚህም ግዙፍ የአፍሪካን ገበያ ለመመስረት የአሁኑ ትልቅ ትምህርት ይሰጣል ባይ ናቸው።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በጨርቃ ጨርቅ አምራችነት ትልቅ ድርሻ አላት ያሉት ጌታቸው፣ እንደ ሞሮኮና አልጀሪያ ያሉ አገራት በማዳበሪያ ምርት፣ ግብጽና ደቡብ አፍሪካ በመጠጥ ምርታቸው የሚታወቁ ስለሆነ በመተባበር የአፍሪካን ግዙፍ ገበያ መፍጠር ቢቻል ከስጋት ነጻ የሆነች አፍሪካ መፍጠር እንደሚቻል ነው የገለጹት። አሁን ላይ 1.8 ቢሊዮን የሚደርሰው የአፍሪካ ሕዝብ አብዛኛውን የግዥ ምርት የሚያስገባው ከእስያና ከመካከለኛው ምሥራቅ መሆኑንም ጠቅሰው፣ ወደ ውጭ ገበያ የሚላከው የኢትዮጵያ ምርት የተወሰነ ማሻሻያ እና የብራንድ ለውጥ ተደርጎበት ተመልሶ ወደ አፍሪካና ሌሎች አገራት እንደሚላክ አመላክተዋል። ለዚህም ኢትዮጵያ ከአጎዋ መታገድ የሚፈጥረው ጫና በሠራተኞች ላይ ነው፤ እሱንም መተባበርና የተለያዩ መፍትሔዎችን ማየት ከተቻለ የፓርኮች ሥራ ሳይስተጓጎል ጫናውን ማስወገድ ይቻላል ብለዋል። በአጎዋ በኩል ወደ ውጭ የሚላከው ምርታችን የዓለም አቀፉን የጥራት መሥፈርት ያሟላ በመሆኑ ወደ ሌላ የውጭ ገበያ በመላክ የምናገኘውን ምንዛሬ የማናስቀጥልበትና ሥራ አጥ የሚሆኑ ዜጎቻችንንም የማንታደግበት ምንም ምክንያት የለም በማለት ሐሳበቸውን አጋርተዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ የበለጠ የምዕራባውያን ማዕቀብ ቢደርስባት አሁን ያለው ኢኮኖሚዋ ጫናውን የመቋቋም አቅሙ ምን ያህል እንደሆነ ለመገመት ብዙ ነገሮችን በስፋት ማየት እና ማጥናት ስለሚጠይቅ ይህን መገመት አስቸጋሪ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ።
ሆኖም ግን፣ ጠንክረን ባለመሥራታችንና የደካማ ኢኮኖሚ ባለቤት በመሆናችን በቀላሉ ይህን ያህል ከተረበሽን፣ በመንግሥት ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው ህወሓት በአገሪቱ ላይ እንዲፈጠር የሚያደርገው ጫና በርትቶ፣ አሜሪካና ምዕራባውያኑ ከዚህ የበለጠ ዕቀባ ቢያደርጉ ምን ያህል አገሪቱ እየተዘጋጀች ነው ሲሉ በርካቶች በአጽንዖት ይጠይቃሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 159 ሕዳር 11 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com