የእለት ዜና

የእርሻ ሥራን የማዘመን ጉዞ

የኢትዮጵያ አርሶ አደር ወራትን እና ወቅትን ተከትሎ፣ ከተፈጥሮ ጋር ተናብቦ ዘር ይዘራል፤ ሰብሉ ለፍሬ ሲደርስ ያጭዳል፣ ይከምራል። አሁን የምንገኝበት ኅዳር ወር አብዛኛው አካባቢ የፍሬ ወቅት ነው፤ እህልም ተሰብስቦ፣ ተከምሮ የሚታይበት። በቀጣይ ወራ ደግሞ የተሰበሰበው እህል በተለያየ መንገድ ይወቃል። ምርቱን ወደ ገበያ ማቅረብ፣ ከተረፈው ለዘርና ለምግብ ማስቀረት ቀጣዩ የአርሶ አደሩ ተግባር ይሆናል።

በዚህ የእህል መውቃት ወይም የመፈልፈል ሒደት ታድያ አርሶ አደሩና መላው ቤተሰቡ ሥራ ይበዛበታል። በተለይም ሴቶችና ሕጻናት በዚህ ሥራ ላይ በስፋት ይሳተፋሉ። በበሬ በማስረገጥ፣ በጆንያ አድርጎ በዱላ መደብደብና የመሳሰለው ብዙ ጊዜ እህሉን ለመውቃት የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው። ታድያ አድካሚ ሥራ ነው፤ ብዙ ጊዜና ጉልበት ይወስዳል። ከዛም ባለፈ እህሉ ስለሚሰባበር ለዘር ለማስቀረት አይመችም፤ ከዛ ባለፈ ለገበያም ተመራጭ ላይሆን ይችላል።

በባለሙያዎችና አጥኚዎች አንደበት ይህ ኹነት ከእህል መሰብሰብ በኋላ የሚከሰት ብክነት (Post-harvest loss) ይሉታል። ኤፍሬም አሰፋ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በመቱ ፖሊቴክኒክ አሠልጣኝ ሆነው ያገለግላሉ። ይህን ከእህል መሰብሰብ በኋላ የሚከሰት ብክነትን ለመቀነስ የሚያስችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ለማስተዋወቅና ለማስፋፋት በሚደረግ ጥረት ውስጥ ተሳታፊ ናቸው። በዚህ ላይ ሐሳባቸውን ሲሰጡ፤ ‹‹ከሚሰበስቡት [አርሶ አደሮች] እህል ላይ ለመሸጥ ያሰቡት ግማሹ ሲሰበር ግማሹ ለዘር አይሆንም። ገበያ ለማቅረብ ካሰቡት ቀንሰው ለቤት አገልግሎት ያውሉታል። በዚህ የተነሳ ለዘር የሚሆንም እንደ አዲስ ሊገዙ ነው፤ ገንዘብ አውጥተው›› ብለዋል።

ኤፍሬምን ያገኘናቸው ‹ፊድ ዘ ፍዩቸር ኢትዮጵያ› የተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት ከካምስ ኢንጅነሪንግ ጋር በጋራ ባሳለፍነው ኅዳር 6/2014 ባዘጋጁት መድረክ ነው። መድረኩ በዋናነት ከግብርና ሥራ ጋር በተገናኘ የሚሠሩ ከአራት ክልል የተውጣጡ የመንግሥት ኃላፊዎችና የዩኒቨርሲቲና ኮሌጅ አባላት የታደሙበት ነበር።

መቅድም
ጥበቡ አሻግሬ በፊድ ዘ ፍዩቸር ኢትዮጵያ ውሰጥ እስካለፈው ወር መጀመሪያ ድረስ የመፈልፈያ ማሽንን በተመለከተ በተያዘው ፕሮጀክት ሒደት ላይ ተሳታፊ ባለሙያ ነበሩ። እህል ከተሰበሰበ በኋላ የሚደርስ ብክነት የተለያየ ደረጃ እንዳለው ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። ‹‹እህል ሲወቃ፣ ሲጓጓዝ፣ ሲከማች ወይም ለገበያ ሲቀርብ ብክነት ሊከሰት ይችላል። በዚህም መሠረት በአጠቃላይ ከ20 እስከ 30 በመቶ ብክነት ይፈጠራል›› ሲሉ ይናገራሉ።

ለዚህ መፍትሔ ይሆናል የተባለው የተለያዩ እህሎችን መፈልፈያ/መውቂያ ማሽን (Multi crop thresher) ነው። ይህም አንዱ የግብርና ቴክኖሎጂ ሲሆን፣ በዚህ ቴክኖሎጂ የሚባክነውን እህል ማትረፍና የብክነት መጠንን መቀነስ እንደሚቻል ይጠቁማሉ። ‹‹አርሶ አደሩ የሰበሰበውን እህል ለመውቃት የሚወስድበት ጊዜና ጉልበት ከፍተኛ ነው። 200 ኩንታል ለመውቃት እስከ 10 ቀን ሊወስድበት ይችላል። ቴክኖሎጂን በመጠቀም ግን በአጭር ሰዓት በጥራት ከተፈለፈለ በኋላ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ወደ ገበያ ይገባል። አርሶ አደሩም ወደ ሌላ ሥራ የመሄድ እድሉ ይጨምራል›› ብለዋል።

ካምስ ኢንጅነሪንግ ደግሞ ይህን ቴክኖሎጂ የማስተዋወቅና የማስፋፋት ግብ ይዞ፣ በግብርናው ውጤታማ ሥራ ሠርቶ መልከ ብዙ ጥቅም ማስገኘትን ግቡ ያደረገ ተቋም ነው። ዳዊት ጎበና የካምስ ኢንጅነሪንግ ምክትል ሥራ አስኪያጅ እና የመውቂያ/መፈልፈያ ማሽንና የግብርና ሜካናይዜሽን ክፍል አስተዳዳሪ ናቸው።

እንደ ዳዊት ገለጻ፣ ካምስ ኢንጅነሪነግ እህል ከተሰበሰበ በኋላ የሚደርስን ብክነት ለመቀነስ ወሳኙ መላ የግብርና ሜካናይዜሽን ነው ብሎ ያምናል። ለዚህም ላለፉት ሦስት ዓመታት በጉዳዩ ላይ ሲሠራ የቆየ ሲሆን፣ በተለየ በዚህ የእህል መውቂያ/መፈልፈያ መሣሪያ ላይ ከዓመት ተኩል በፊት ጀምሮ ወደ ማምረት ለመግባት ሲሠራ እንደቆየ ያወሳሉ።

መሣሪያው የምዕራብ አፍሪካዊቷ ጋና ቴክኖሎጂ ነው። ከዛ ተወስዶና በጋራ ሥልጠናና ልምድ ልውውጥ ሒደት አልፎ ወደሌሎች የአፍሪካ አገራት እየተሰራጨም ይገኛል። ‹‹እያደገና እየተሻሻለ ያለ ቴክኖሎጂ ነው። እኛ አገርም ከጤፍ በቀር ስንዴ፣ ገብስ፣ ሩዝና አኩሪ አተር ተሞክሮበታል፤ በቆሎ በዋናነት ተሞክሮም ውጤታማ ሆኗል። ከኢትዮጵያ ውጪ ሰባት የአፍሪካ አገራት ተሰራጭቷል›› ሲሉ ዳዊት ተናግረዋል።

ምን ታሰበ?
ካምስ ኢንጅነሪንግ ይህን አዲስ የግብርና ሥራን የሚያግዝ ቴክኖሎጂ ወደ ሥራ በማስገባት ሒደት ላይ አዲስ የንግድ ሥራ አካሄድን አምጥቻለሁ ይላል። ይህም ከአገልግሎት ሰጪዎች ጋር የሚደረግ ጥምረት ነው።
ጉዳዩ እንዲህ ነው፤ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ እና ጋምቤላ ክልል የሚገኙ ወጣቶች በዚህ የመውቂያ/መፈልፈያ ማሽን ጋር በሚገባ እንዲተዋወቁ ተደርጓል። እነዚህም ወጣቶች በአካባቢው ያለውን የግብርና ሥራ በቅርበት የሚያውቁ ሲሆኑ፣ በተጓዳኝ የቀለምን ትምህርት የቀሰሙ ናቸው።

ዳዊት እንዳስረዱን፣ ወጣቶቹ ባገኙት ሥልጠና የመውቂያ/መፈልፈያ ማሽኑን እንዴት ማንቀሳቀስና መጠገን እንደሚችሉ ቢያውቁም፣ በመሣሪያው አገልግሎት በመስጠት ገቢ ለማግኘት እንዲያስችላቸው መሣሪያውን የመግዛት አቅም ላይኖራቸው ይችላል። በብድር እንግዛ ቢሉም የዋስትና ጉዳይ እንቅፋት መሆኑ አይቀርም። ስለዚህም ተደራጅተውና ማሽኑን ተረክበው ከባለንብረቱ ድርጅት ጋር በጋራ ይሠራሉ። የመውቂያ/መፈልፈያ ወቅት በሚደርስ ጊዜ ከቦታ ቦታ ማሽኑን ይዘው በመንቀሳቀስ አገልግሎት ለአርሶ አደሮች ይሰጣሉ።

በዚህ መሠረት አሁን ላይ በካምስ ኢንጅነሪንግ 55 የመውቂያ/መፈልፈያ መሣሪያዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከ18 እስከ 20 የሚደርሱት ለአገልግሎት ሰጪዎች ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ለመስጠት የታቀደው ግን 30 መሆኑን ያነሱት ዳዊት፣ ነገር ግን ግብረ-ንድፍ (ፕሮፖዛል) አቅርበው ተመዝኖ ያለፉት 20 የሚደርሱ በመሆናቸው ቅድሚያ እንዳገኙ ገልጸዋል። ከዛ ባሻገር 48 ማሽኖች ወደ አገር ውስጥ ገብተው ለመገጣጠም እየተጠበቁ ነው።
ከላይ እንደተጠቀሰው በዚህ ሥራ ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ ወጣቶች ሥልጠና ወስደው የማሽኖቹን መምጣት በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

የቴክኖሎጂው ቅቡልነት
በኢትዮጵያ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በቶሎ የመቀበል ባህል እምብዛም የለም። ማኅበረሰቡ አሰላስሎ፣ ተመልክቶና ጊዜ ሰጥቶ፣ ጥቅም ጉዳቱን በየራሱ ሚዛን ለክቶና በብዙ መስፈርት ሠፍሮ ነው ለጥቅም ለማዋል የሚስማማው። የካምስ ኢንጅነሪንግ ምክትል ሥራ አስኪያጁ ዳዊትም፣ ይህ ቴክኖሎጂን በፍጥነት ያለመቀበል ባህል እንዳለ ይስማማሉ። ‹‹የተለመደ ነው! አዲስ ነገር ማስለመድ ይከብዳል›› አሉ።

ይህ የመውቂያ/መፈልፈያ ማሽን ለበቆሎ በአንድ ቀን ወይም በዐስር ሰዓታት ውስጥ እስከ 3 ኩንታል በቆሎ ሊፈለፍል ይችላል። ለስንዴ፣ ገብስ፣ አኩሪ አተርና ለመሳሰሉት ደግሞ ከዛ ባነሰ መጠን፣ በሰዓት አምስት ወይም ዐስር ኪሎ መውቃትና መፈልፈል የሚችል ነው። በየአንዳንዱ ማሽንም በትንሹ አምስት፣ ቢበዛ ሰባት ባለሙያዎች በየሥራው ላይ ወሳኝ የሥራ ድርሻ ይኖራቸዋል።

ይህ የታሰበው ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ አርሶ አደር ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ እስኪሠራ አንድ ወይም ኹለት ዓመት ሊወስድ እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል። ‹‹የመውቂያና መፈልፈያ ወቅት አራት ወር ገደማ ስለሆነ፣ አንድ ዓመት ስንል አራት ወር አካባቢ ማለታችን ነው። በቀረው ስምንት ወር አካባቢ ደግሞ ወጣቶቹ የማስታወቂያ ሥራ ይሠራሉ፤ ገበያ ይፈጥራሉ። ያንን ማድረግ ማሽኑ ተቀባይነት እንዲያገኝ የሚፈጀውን ጊዜ ይቀንሰዋል ብለን እናምናለን›› ብለዋል፤ ዳዊት።

በመቱ ፖሊ ቴክኒክ አሠልጣኝ የሆኑት ኤፍሬም በዚህ ላይ ዕይታቸውን ሲያካፍሉ፣ አርሶ አደሮች አንድን ቴክኖሎጂ ተቀብለው ወደ ሥራ ማዋል ላይ ይቸገራሉ ይላሉ። ‹‹ያለማመን ነገር አለ። በዚህም የተነሳ ቴክኖሎጂው በሰዓቱ ወደ ማኅበረሰቡ ገብቶ የሚያመጣው ውጤት እንዳይታይ ያደርጋል። ያንን ለመቅረፍ ግን ግንዛቤ መስጠት ላይ እናተኩራለን›› ብለዋል።

አያይዘውም በቴክኖሎጂ አቅራቢዎች በኩል ያለውን ክፈተት አንስተዋል። በተለይም አርሶ አደሩን ሳያማክሩና ችግሩ ምን እንደሆነ ሳያውቁ ቀጥታ አዲስ ቴክኖሎጂን ‹እንካችሁ!› ማለት ለአርሶ አደሩ እንግዳ እንደሚሆንበትና የተባለው በቶሎ ያለመቀበልን ግፊት ሊፈጥር እንደሚችል ጠቅሰዋል። በአንጻሩ ከመሠረቱ ጀምሮ አርሶ አደሩን በማናገርና ፍላጎቱን መሠረት በማድረግ፣ ጥቅሙንም በሚመለከት ግንዛቤ በመስጠት ከተሠራ በቶሎ ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል ተናግረዋል። አሁን ላይም በዛ መልክ መሠራቱን ነው አክለው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።

በአገር ውስጥ ስለማምረት
ዳዊት ጎበና ይህን የእህል መውቂያ/መፈልፈያ ማሽን ማምረትና ወደ አገልግሎት በማስገባት ሒደት ውስጥ የሚፈጠረውን የሥራ ዕድል በኹለት ወገን ማየት እንደሚቻል ያመላክታሉ። አንደኛው የከተማ የሥራ ዕድል ፈጠራ ሲሆን፣ ይህም ማሽኖቹን በማምረት ዘርፍ ላይ በመሠማራት የሚፈጠር የሥራ ዕድል ነው። ኹለተኛው ደግሞ በገጠር በቋሚነት ለወጣቶች የሚፈጠረው የሥራ ዕድል ነው። ድርጅቱ አገኘሁት ባለው ጥናት መሠረት በኢትዮጵያ ቢያንስ 20 ሺሕ የመውቂያ/መፈልፈያ ማሽኖች ያስፈልጋሉ።

ይህን ማሽን በአገር ውስጥ ለማምረት ታስቦ እንደነበር ዳዊት አስታውሰዋል። ነገር ግን በኮቪድ 19 ምክንያት ግብዓቶችን እንደልብ ከውጪ ማስመጣት ስላልተቻለ ማሽኖቹ ከቻይና ተዘጋጅተው እንዲመጡና በኢትዮጵያ የመገጣጠም ሥራ ብቻ እንዲሠራ ተወሰነ። ነገር ግን በዚህ እንደማይዘልቅና በአገር ውስጥ ማምረት እንዲቻል ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እንዲሁም ከአነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ጋር በመሆን ባለሙያዎችን ማፍራት በዕቅድ ተይዟል።

‹‹በአገር ውስጥ የብረታ ብረት አቅርቦት ካለ፣ በአምራች ደረጃ አቅም እንዲኖረን ባለሙያዎችን ለማሠልጠን ከኮሌጆች ጋር እየተነጋገርን ነው። በቂ ሥልጠና እንዲሰጥልን ለማድረግ መንገድ ላይ ነን፤ ግንኙነቶችን እየፈጠርን ነው። ያ ችግሩን ይፈታል ብለን እናስባለን›› ሲሉ ነው ዳዊት የገለጹት።

ከዚህ ባለፈ ከተለያዩ የመንግሥት ባለድርሻ አካላት በጎ ምላሽ ማግኘታቸውን ዳዊት ተናግረዋል። ከዛም ባለፈ ወጣቱ ዘንድ ያለው የሥራ ተነሳሽነትም ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ በግብርና ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ግንዛቤ እንዳለ ያመላከተ ነው ብለዋል። ባስተላለፉት መልዕክትም ይህን አሉ፤

‹‹የኢትዮጵያ ወጣት ግብርናው ከዘመነለት ወደ ከተማ ያለውን ፍልሰት ትቶ፣ በግብር ሥራ መሳተፍ እንደሚፈልግ እያየን ነው። እና ኢንቨስትመንቱ በትክክል ወጣቱን ያማከለ ከሆነና የግብርና ቴክኖሎጂዎች ግብርናን እንዲያዘምኑ ተደርገው ተቀርጸው ከመጡ፣ ሥራ አጥ የምንለው ወጣት፣ ከከተማ ሳይቀር ወደ ገጠር ገብቶ ለመሥራት የሚችልበት ሁኔታ አለ። ስለዚህ የኢንቨስትመንት ትኩረት ግብርናውን ወደማዘመን ማተኮር አለበት።››


ቅጽ 4 ቁጥር 159 ሕዳር 11 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com