የእለት ዜና

ሕብረት ኢንሹራንስ ሸሪዓ መር የሆነውን ተካፉል መድኅን ሊጀምር መሆኑ ታወቀ

ሕብረት ኢንሺራንስ ኢስላማዊ አስተምህሮን መርህ ያደረገ የተካፉል መድኅን (ኢንሹራንስ) ተግባራዊ ሊያደርግ እንደሆነ አስታወቀ።
ሕብረት ኢንሹራንስ የሙስሊሙን ማኅበረሰብ አካታች የሆነ አገልግሎት መስጠትን ታላሚ አድርጎ እየሠራ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ እንደ ኢንሹራንሱ የቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ዳይሬክተር ጥላሁን ታደሰ የተካፉል አገልግሎትን ለመጀመር በኩባንያው የአዋጭነት ጥናት እንደተከናወነ በተለይም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ አማካይነት አገልግሎቱ ለኢትዮጵያ ቢተዋወቅም፣ የዚህን ኢስላሚዊ የመድኅን አገልግሎት አዋጭነት ጥናት የሚያካሂደው አገር በቀሉ አልፋ የተሰኘ የፉይናንስ አማካሪ መሆኑን ጥላሁን ደስታ ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል።
ከባለፈው 2012 በጀት ዓመት በፊት በአገሪቱ ውስጥ ካሉ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አንድ ሦስተኛ እንኳን የሚሆኑት የተካፉል መድኅን ዋስትና የሚሰጡ አልነበረም። ስማቸው መጠቀሱን ያልፈለጉት በዚሁ የፉይናንስ ማማከር ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያ ለአዲስ ማለዳ እንዳስረዱት፣ ተካፉል (ኢስላሚክ የመድኅን ዋስትና) የመጣው- ካፋላ ከሚለው የአረቢኛ ቃል ሲሆን፣ ፍችውም “የእርስ በርስ ዋስትና ወይም የጋራ ዋስትና” ማለት ነው። ጽንሰ ሐሳቡ በማኅበረሰቡ ውስጥ አደጋዎች በሚገጥሙበት ወቅት ካሳ እና ተጠያቂነቶችን በመደጋገፍ በጋራ የሚደራረሱበት ሒደት ነው ተብሏል።

ተካፉል በኢስላሚክ ኢንሹራንስ (ተካፉል) ውስጥ የፖሊሲው ባለቤቶች ጥምር ኢንቬስትሮች ሲሆኑ፣ የፖሊሲው ባለቤቶች የኢንቨስትመንቱ ትርፍና ኪሳራ ይጋራሉ። በሕግ የተረጋገጠ ትርፉ የለውም። ምክንያቱም እንደ መደበኛው የኢንሹራንስ ድርጅቶች ቀድሞ የተረጋገጠ ትርፉ መሰረት አድርጎ የፖሊሲ ባለቤት የሚያደርግ አካሄድ መከተል ከወለድ ጋር ተመሳሳይነት ያለው በመሆኑ በሸሪዓው ተቀባይነት የለውም ተብሏል። በጋራነት እና በትብብር መርሆዎች፣ ማለትም የጋራ ኃላፊነት፣ የጋራ ተጠቃሚነት፣ የጋራ ፍላጎት እና ትስስር መርሆች ላይ የተመሠረተ እንደሆነም ባለሙያው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ጅማሬውም በኢስላማዊ ልኂቃን ምክር ቤት ከሸሪዓ ሕግጋት ጋር በተጣጣመ መልኩ የጸደቀ መሆኑ ተጠቁሟል። ይህ ተካፉል ኢስላማዊ የመድኅን አገልግሎት በአገራችን በቀዳሚነት የተጀመረው በ23 መስራች አባላት እና በ3.75 ሚሊዮን ብር ካፒታል በተቋቋመው ግሎባል ኢንሹራንስ ኩባንያ በ2013 መስከረም ወር ላይ ሲሆን፣ ድርጅቱ ባደረገው የአዋጭነት ጥናትም 1.3 ትሪሊዮን ብር በላይ ይንቀሳቀስበታል ተብሎ የተገመተ ነበር።

በተጨማሪ አዋሽ ኢንሹራንስ በ10 ቅርንጫፎች አገልግሎቱን በማስጀመር የተከተለው ሲሆን፣ ኒያላ ኢንሹራንስ ኩባንያም በመቀጠል ኢስላማዊ የመድኅን አገልግሎት ወደመስጠት መግባቱ የሚታወስ ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ የመድኅን ወይንም የኢንሹራንስ ጽንሰ ሐሳብ እምብዛም የሚታወቅ አይደለም። በተያያዘም 62 በመቶ የሚሆን በገጠር የሚኖረው ማኅበረሰብ ስለኢንሹራንስ ሰምቶ እንደማያውቅ ጥናቶች ይጠቁማሉ። በአሁኑ ጊዜ የመድኅን ዋስትና ብለን የምንጠራው ጽንሰ ሐሳብ ከ 1400 ዓመታት በላይ በተለያየ መንገድ
ይተገበር የነበረ ቢሆንም፣ የተካፉል መድኅን አገልግሎት ግን 1970 በ አገረ ሱዳን እንደተጀመረ ይነገራል።

አገልግሎቱን አሁን የጀመረው ሕብረት ኢንሹራንስ የተመሠረው በ1994 በ87 ባለድርሻዎች፣ በስምንት ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል እና በ25 ሚሊዮን ብር አጠቃላይ ካፒታል ነበር።
የኩባንያውን የተከፈለ ካፒታል ግማሽ ቢሊዮን ብር ለማድረስ የተወሰነውን ውሳኔ ተከትሎ ባሳለፍነው የበጀት ዓመት የኢንሹራንሱ ጠቅላላ የተከፈለ ካፒታል ብር 473.4 ሚሊዮን ከ501 ባለአክሲዮኖች ማድረስ መቻሉ ታውቋል። በአሁኑ ሰዓት የኩባንያው ሀብት 1.8 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ለማወቅ ተችሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 159 ሕዳር 11 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com