የእለት ዜና

ዩኒቨርስቲው ቤተሰቦቻቸው የተፈናቀሉና ጦርነት ቀጠና ውስጥ በሚገኙ አካባቢዎች ያሉ ተማሪዎችን ከግቢ በማስወጣቱ ተማሪዎቹ መቸገራቸውን ተናገሩ

ባህር ዳር የኒቨርስቲ ተማሪዎቹን ከሰሞኑ ከግቢ ማስወጣቱን ተከትሎ፣ ቤተሰቦቻቸው ጦርነት ባሉባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ እና በጦርነቱ የተፈናቀሉ ቤተሰቦች ያሏቸው ተማሪዎች ማረፊያ በማጣታቸው ችግር ላይ መውደቃቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጸዋል።
በዩኒቨርስቲው ሲማሩ የነበሩ ተማሪዎች ከዩኒቨርስቲው የመውጫ ፈቃድ እየወሰዱ ግቢውን መልቀቃቸውን አዲስ ማለዳ ከግቢው ከወጡ ተማሪዎች ሰምታለች። ዩኒቨርሰቲው ተማሪዎች ከግቢ እንዲወጡ መፍቀዱን ተከትሎ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው መውጣታቸው ታውቋል። በጦርነት ቀጠና ውስጥ ያሉና በጦርነቱ የተፈናቀሉ ቤተሰቦች ያሏቸው ተማሪዎች፣ በዩኒቨርስቲው ውሳኔ ከግቢ ወጥተው የሚርያፉበት በማጣታቸው መቸገራቸውን ገልጸዋል።

ተማሪዎቹ ከግቢ እንዲወጡ የተደረገው በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ኅብረት ውሳኔ መሆኑን የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ገልጸዋል። አዲስ ማለዳም የጉዳዩን አሳሳቢነት በመመልከት የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ቢዝነስ ግቢ የተማሪዎች ተወካይ የሆኑትን ተማሪ መልካሙ ታደሰን ያነጋገረች ሲሆን፣ ጥያቄው የተነሳው በተማሪዎች መሆኑን በማንሳት የተማሪዎቹ ኅብረት የ7ቱም ግቢ (ካምፓስ) ተማሪዎትን በባህር ዳር የባህል አዳራሽ በመሰብሰብ በጉዳዩ ላይ እንዳወያየ አስታውሰዋል።

በውይይቱም አገር ሕልውናዋን ለማስጠበቅ የልጆቿን ድጋፍ ከበፊቱ በላቀ ሁኔታ በምትፈልግበት ሰዓት የተማሪዎቹ በትምህርት ገበታ ላይ መገኘት ፋይዳ እንደሌለው ተማሪዎቹ አንስተው፣ ትምህርታቸውን ከአገር ደኅንነት በኋላ መቀጠል እንዳለባቸው ተስማምተዋል ብለዋል። በተጨማሪም፣ ተማሪዎቹ አገራቸውን ከመበተን ለማዳን በሚችሉት አቅም ሁሉ ለመሰለፍ ቃል ገብተው ይህንን ስምምነታቸውን ለዩኒቨርስቲው ሴኔት ለማስገባት ስምምነት ላይ መደረሱ ተጠቁሟል።

በዚህም የዩኒቨርስው የተማሪዎች ኅብረት ተወካዮች በስምምነቱ መሠረት ውሳኔውን ለዩኒቨርሲቲው ሴኔት አቅርበው፣ የዩኒቨርስቲው አስተዳደር እና አካዳሚክ ኃላፊዎች ተሰብስበው የተማሪዎቹን ውሳኔ በመሉ ድምጽ እንዳጸደቁት ተማሪ መልካሙ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። ይህን ውሳኔ ተከትሎም ጥቅምት 29 እና 30/214 ተማሪዎቹ ከሚማሩበት ጊቢ ለቀው ወጥተዋል።

የተማሪ ኅብረት ተወካዮቹ በዩኒቨርስቲው የሚማሩ አካል ጉዳተኛ እና አቅመ ደካማ ተማሪዎች ዕጣ ፈንታቸው ምን ይሁን በሚለው ላይ ከዩኒቨርስቲው ሴኔት ጋር በመወያየት፣ እዛው ጊቢ ውስጥ እንዲቆዩ እና የምግብና የመኝታ አገልግሎት የሚያገኙበትን ሁኔታ እንዲመቻችላቸው ተደርጓል ተብሏል። አገር ፈተና ውስጥ እንደሆነች ኹሉም ኢትዮጵያዊ ሊያውቅ ይገባል ያሉት ተማሪ መልካሙ፣ የፈተናውን ገፈት እያንዳንዱ ዜጋ ሊቀምስ የግድ ነው። ስለሆነም ተማሪዎች ወደየቤታቸው ሲሄዱ የተለያየ ችግር ሊደርስባቸው እንደሚችል የሚጠበቅ ነው ብለዋል። የተማሪ ኅብረት ተወካዮ አክለውም ከተለያዩ አቅም ካላቸው ባለሀብቶች ገንዘብ በማሰባሰብ መሳፈሪያ የሌላቸው ተማሪዎች ወደየቤታቸው እንዲሄዱ ተደርጓል በማለት ችግሩን በተቻለ መጠን ለመፍታት መሞከራቸውን ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጅ፣ ከጊቢው ከወጡ ተማሪዎች ወስጥ የተወሰኑት በባህር ዳር ከተማ በየቤተክርስቲያኑ እና በየመስጊዱ ተጠልለው ለችግር እንደተዳረጉ እንደሚገኝ ለጊዜው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ተማሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የኅብረቱ ተወካይ በበኩላቸው፣ ይህ መረጃ እነሱ ጋር እንዳልደረሳቸው በመግለጽ፣ ይሁን እንጂ ጉዳዩን አጣርተው አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚሰጡ ጠቁመዋል።

በሰባቱም የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ግቢዎች ከ16 ሺሕ በላይ ተማሪዎች እንደሚማሩ ከዩኒቨርስቲው የተገኘው መረጃ ያሳያል። ከአካል ጉዳተኞች እና ከአቅመ ደካማ ተማሪዎች ውጪ ኹሉም በአሁን ሰዓት ከጊቢዎቹ በመውጣት ወደየትውልድ መንደራቸው መመለሳቸውን የኅብረቱ ተወካይ ጠቁመው፣ በቀጣይ የአገርን ድኅንነት በማስጠበቅ ረገድ የራሳቸውን አስተዋጽዖ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆኑ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡

በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ምላሽ ለማግኘት አዲስ ማለዳ ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ስልክ ብትደውልም ስልካቸውን ሊያነሱ ባለመቻላቸው ምላሻቸውን ማካተት አልቻለችም።


ቅጽ 4 ቁጥር 159 ሕዳር 11 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com