የእለት ዜና

የግዥና ንብረት አስተዳደር ረቂቅ ዐዋጅ ላይ ማሻሻያ ሊደረግ ነው

ከ2001 ጀምሮ እስካሁን ሲሠራበት በነበረው የግዥና ንብረት አስተዳደር ዐዋጅ ላይ ማሻሻያ ሊደረግ መሆኑን የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

ባለሥልጣኑ በሥራ ላይ ያለው የግዥ አፈጻጸምና ንብረት አስተዳደር ሥርዓት የበለጠ ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆን ከማድረግ፣ እንዲሁም ለመንግሥት ገንዘብ ተመጣጣኙን ፋይዳ ከማስገኘት አንጻር ያለበትን ክፍተት በመለየትና የዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በማካተት፣ ባለፉት ዓመታት የግዥና ንብረት አስተዳደር ዐዋጅ ማሻሻያ ሥራዎችን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን፣ አሁን ላይ ረቂቅ የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ዐዋጅ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገልጿል።

የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬከተር ሰጠኝ ገላን ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ የማሻሻያ ሥራው የተጀመረው ከ2006 ጀምሮ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን ዐዋጁ ሳይጸድቅ ቆይቷል ነው ያሉት። አሁን ላይ ተሻሽሎ በተዘጋጀው ረቂቅ የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ዐዋጁ ላይ ከባለድርሻ አከላት (የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች)፣ ከግሉ ዘርፍ ማኅበራት እና ከግል ድርጅቶች፣ እንዲሁም ከሲቪል ማኅበራት ጋር ውይይት ተደርጎ፣ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በኩል ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል ሲሉ ተናግረዋል።

ዐዋጁ ባለፈው ዓመት ይጸድቃል ተብሎ ታስቦ ነበር ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲቀርብ የሚቀየሩና የሚሻሻሉ ነገሮች መኖራቸውን ጠቁመው፣ አሁንም ውሳኔው የእኛ ሳይሆን የበላይ አካል በመሆኑ የተሻሻለው የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ዐዋጅ መች እንደሚጸድቅ አይታወቅም ብለዋል።

የተሻሻለው የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ዐዋጅ በዋናነት፣ መጀመሪያ ሲዘጋጅ የነበረውን የብር የመግዛት አቅምና አሁን ያለውን የገንዘብ የመግዛት አቅም ልዩነት ያስተካክላል ተብሏል። ስለሆነም ላለፉት ዓመታት የተደረገውን የብር ምንዛሪ ማሻሻያ እና ያለው የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት በግዥ አፈጻጸም ላይ እያሳደረ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለማስቀረት አሁን ሥራ ላይ ባለው የግዥ ገንዘብ ጣሪያ ላይ ማሻሻያ ተደርጓል። ለአብነትም የግዥ ዘዴው ብሔራዊ ግልጽ ጨረታ ሆኖ የግዥ ዓይነቱ የግንባታ ሥራ ግዥ ከሆነ፣ በሥራ ላይ ያለው የገንዘብ ጣሪያ ብር 150 ሚሊዮን ወደ 600 ሚሊዮን ከፍ እንዲል ተደርጓል። በተመሳሳይ የግዥ ዘዴ፣ የግዥ ዓይነቱ የዕቃ ግዥ ሲሆን ደግሞ፣ በሥራ ላይ ያለው የገንዘብ ጣሪያ ከብር 50 ሚሊዮን ወደ 200 ሚሊዮን ተሻሽሎ ቀርቧል።

በውሱን ጨረታ የግዥ ዘዴ ለሚደረግ የዕቃ ግዥ ዓይነት እንዲሁ ቀድሞ ከነበረው 1.5 ሚሊዮን ብር ወደ 3.75 ሚሊዮን ብር ማሻሻያ ተደርጎበታል። የመንግሥት ንብረት ሽያጭ የጨረታ ማስታወቂያን በጋዜጣ ለማውጣት አሁን ያለው 10 ሺሕ ብር የገንዘብ ጣሪያ በማሻሻያው ወደ 50 ሺሕ ብር ከፍ ብሏል። በዚህ መንገድ የገንዘብ ጣሪያ ማሻሻያ የተደረገባቸው ሌሎች የግዥ ዓይነቶች መኖራቸውንም ባለሥልጣኑ ለአዲስ ማለዳ ከላከው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

በተጨማሪም፣ እስካሁን በሥራ ላይ ያለው ዐዋጅ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ያካትት እንዳልነበርና የተሻሻለው ዐዋጅ ግን የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በማካተት እንደ አገር አንድ የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ዐዋጅ እንዲኖር ያደርጋል ነው የተባለው። ይህን ተከትሎም ኢትዮ ቴሌኮም፣ የመንግሥት ባንኮች፣ የመንግሥት ኢንሹራንስ ድርጅቶች፣ ስኳር ኮርፖሬሽኖች እና ሌሎችም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ ሆነው፣ በባለሥልጣኑ በኩል የንብረት ግዥ አገልግሎት እንደሚያገኙ ተመላክቷል።
እንዲሁም፣ ባለው ዐዋጅ የሐራጅ ጨረታ የነበረው ለሽያጭ ሲሆን፣ በተደረገው ማሻሻያ ንብረትን ለመግዛት የሚያስችል ግልጽ የሐራጅ ጨረታ እንደተቀመጠም ተገልጿል።


ቅጽ 4 ቁጥር 159 ሕዳር 11 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com