የእለት ዜና

ከአራት ዓመት በፊት የተዘጋጀው የወተት ምርት የጥራትና የግብይት ረቂቅ ዐዋጅ አልጸደቀም

በወተት ምርት ላይ የሚስተዋለውን የጥራትና የግብይት ችግር ይፈታል ተብሎ ከአራት ዓመት በፊት የተዘጋጀው ረቂቅ ዐዋጅ እስካሁን አለመጽደቁንና ተግባራዊ አለመደረጉን የኢትዮጵያ ሥጋና ወትት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
በኢትዮጵያ በአጠቃላይ በዓመት በሚመረተው የወተት ምርት ላይ ከማለብ ጀምሮ እስከ ማቀነባበር ያለውን ከፍተኛ የጥራት ጉድለት እና የግብይት ችግር ለመፍታት እና ሕጋዊ የንግድ ሥርዓት ለማበጀት ተብሎ የተዘጋጀው ዐዋጁ፣ በተያዘው በ2014 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ለሚንስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ አስተያየት ከተሰጠበት በኋላ ለፓርላማ ይቀርባል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ እስካሁን ግን እንዳልቀረበ የኢትዮጵያ ሥጋና ወትት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ደበሌ ለማ ተናግረዋል።

ይህ የሆነበትም ምክንያት፣ በአዲሱ መንግሥት ምስረታ በተደረገው የተቋማት ሽግሽግ መጓትት በመፈጠሩ ነው ተብሏል። የኢትዮጵያ ሥጋና ወትት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ቀድሞ ተጠሪነቱ ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን ወደ ግብርና ሚኒስቴር መዞሩ ዐዋጁን ለማጸደቅ እንቅፋት እንደፈጠረም አስረድተዋል። በቀጣይም ቢሆን አገሪቱ ካለችበት ኹኔታ አንጻር፣ ዐዋጁ ፓርላማ ከቀረበ በኋላ ለሕግ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቶና ጸድቆ ተግባራዊ እስከሚሆን ለወራት ሊዘገይ እንደሚችል ጠቁመዋል።

እስካሁን በወተት ምርት ላይ የነበረው ከፍተኛ የጥራት እና የግብይት ችግር የተከሰተው፣ ደላላውን ከመሀል በማስወጣት አምራችና ተጠቃሚውን በቀጥታ የሚያገናኝ ሕግ ባለመኖሩ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣ በቀጣይ ግን ዐዋጁ አምራችና ተጠቃሚን በቀጥታ የማገናኘት ኃይል ስለሚኖረው ችግሩን ይቀርፋል የሚል ዕምነት እንዳለቸው ተናግረዋል።

የተዘጋጀው ረቂቅ ዐዋጅ ላለፉት አራት ዓመታት ከወተት አምራቶች፣ ከወተት አቀናባሪዎች፣ ከክልሎችና ሌሎች ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ሲደረግበት ቆይቷል ተብሏል። ዐዋጁን ያዘጋጀውም የኢትዮጵያ ሥጋና ወትት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ከበፊቱ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ሲሆን፣ ግብርና ሚኒስቴርም ከረቂቁ ያዘጋጀው ክፍል መኖሩ ተጠቁሟል።

ዐዋጁ ከማለብ ጀምሮ እስከ ማቀነባበሪያ ድረስ በማን እንዲሚጓጓዝ፣ መያዣ ዕቃው ምን ዓይነት መሆን እንደሚገባው፣ የግብይት ቦታው የት እንደሆነ፣ ተሳታፊዎቹ እነማን እንደሆኑ ይደነግጋል ነው የተባለው። በተጨማሪም ዐዋጁ የዋጋ ተመንን ያስቀምጣል፤ በየደረጃውም የወተቱ ይዘት ይፈተሻል። በዚህም ውኃ እና ሌሎች አላስፈላጊ ነገሮችን ከወተት ጋር የቀላቀሉ፣ በየመንደሩ በጀሪካን ይዘው የሚሸጡ እና በጥቅሉ ደንቡን ተላልፈው በተገኙ አካላት ላይ ዐዋጁ ቅጣት ያስቀመጠ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የዐዋጁ መዘጋጀት በዋናነት የጥራትና የግብይት ችግሩን ይፈታዋል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ዐዋጁ ኹሉንም አካላት ተጠያቂ የሚያደርግ በመሆኑ በመሀል ገብተው እንደፈለጉ የሚሠሩትን አካላት ሕጋዊ መስመር ተከትለው እንዲሠሩ ወይም ከገበያው እንዲወጡ ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም በኢትዮጵያ የወትት ምርት ጥራትና ግብይት ችግሮችን ከመፍታት በተጨማሪ የምርት መጠኑን ማሳደግ እንደሚገባም ጠቁመዋል። እንደ አገር በዓመት ማምረት የሚገባንን የወትት ምርት እያመረትን አይደለም ሲሉም ገልጸዋል። ይህን ተከትሎም በዚህ ወቅት አንድ ሊትር ዋጋ ከ50 እስከ 60 ብር እንደሚሸጥና ካለው የጥራት ጉድለትና የመጠን ማነስ አንጻር የማይመጥን ዋጋ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጨምረው አብራርተዋል። ከአርብቶ አደሮች፣ ከከፊል አርብቶ አደሮች፣ ከአርሶ አደሮችና በግላቸው ወትት ምርት ላይ ከተሠማሩ አካላት የሚገኘው እና እስካሁን በጥናት የተረጋገጠው የኢትዮጵያ ዓመታዊ የወትት ምርት መጠን 4.2 ቢሊዮን ሊትር ወተት ሲሆን፣ ለ120 ሚሊዮን ሕዝብ ሲካፈል አንድ ሰው በዓመት በአማካኝ የሚጠቀመው ከ20 እስከ 30 ሊትር ወተት እጅግ በጣም ዝቅተኛ መሆኑንም ገልጸዋል።

ይህን ለመፍታት የላሞችን ዝርያ በመቀየር እና የውጭ ዲቃላዎችን በማብዛት ከኹለት ሊትር በላይ የሚታለቡ ላሞችን ማበራከት እንደሚያስፈልግ ነው ያመላከቱት። በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ለሱማሌ እና ለጅቡቲ የግመል ወትት የምትልክ ሲሆን፣ በአንጻሩ በአገር ውስጥ ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት እና ዝቅተኛ የወተት ምርት አቅርቦት ለማመጣጠን በየዓመቱ በሚሊዮን ቶን የሚቆጠር የዱቄት ወተት ከውጭ አገር እንደምታስገባ ተመላክቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 159 ሕዳር 11 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com