የእለት ዜና

ከገበያ ታግዶ የነበረውን “ሲረስ 100 ፐርሰንት አፕል” ጭማቂን መጠቀም እንደሚቻል ተገለጸ

ከገበያ ታግዶ የነበረውን “ሲረስ 100 ፐርሰንት አፕል” የተሰኘ ጭማቂ መጠቀም እንደሚቻል የኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

ባሳለፍነው ጥቅምት ወር መጀመሪያ የኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን “ሲረስ 100 ፐርሰንት አፕል” የተሰኘ የታሸገ ጭማቂ፣ በውስጡ ለሰው ልጅ ጤና አደገኛ የሆነ ንጥረ ነገር ይዞ በመገኘቱ ከገበያ ላይ ማገዱ እና የትኛውም የማኅበረሰብ ክፍል ይህንን ምርት እንዳይጠቀም በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ማሳሰቡ የሚታወስ ነው። ይህን ተከትሎም በደቡብ አፍሪካ የሚመረተው ሲረስ የተባለው የታሸገ ጭማቂ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰባት አፍሪካ አገራት ገበያ መታገዱ ይታወሳል።

የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የምግብ ጥራት ፍተሻ ዳይሬክተር በትረ ጌታሁን ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ የምርት እገዳው የተላለፈው “ሲረስ አፕል 100 ፐርሰንት” ለተሰኘው ምርት ብቻ እንደሆነ ገልጸው የአፕል ጭማቂ ምርቱ ገበያ ውስጥ ሳይሠራጭ በፊት ማስወገድ መቻሉን ገልጸዋል።

በመጀመሪያ ጥቆማው የመጣው ከደቡብ አፍሪካው የሲረስ ጭማቂ አምራች ድርጅት መሆኑን በትረ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። እንደ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ገለጻ፣ የአጠቃላይ ምርት ዕገዳ የተላለፈው ችግሩ የታየበት ምርት ገበያ ላይ ከዋለው ጋር ለመለየት እና ጥብቅ ጥንቃቄ ለመድረግ ታስቦ መሆኑ ተመላክቷል። “ምርመራው እንደቀጠለ ሆኖ ሕብረተሰቡ እንዲረዳው የሚፈለገው መርዛማው ንጥረ ነገር የተገኘበት በሰኔ ወር ላይ ተመርቶ ለገበያ የዋለው የአፕል ምርት ብቻ መሆኑ ነው” ሲሉ ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ከሰኔ ምርቱ ውጪ ተመሳሳይ ግድፈት ያለበት ምርት አለመኖሩ ታምኖበት በቀሪ የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤት ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ዕገዳው ሙሉ ለሙሉ እንደሚነሳ ለማወቅ ተችሏል። ዕገዳው የተነሳው ምርቱ ላይ የተገኘው መርዛማ ንጥረ ነገር ባሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ በተመረተው ላይ ብቻ በመሆኑ እና አሁን ላይ መርዛማ ንጥረ ነግር ያለበት ጭማቂ ከገበያ ውጭ በመሆኑ ነው ተብሏል።

አዲስ ማለዳ ምን ያህል ምርት ወደ አገር ውስጥ እንደገባ እና ሙሉ ለሙሉ ስለመወገዱ፣ እንዲሁም በኮንትሮባንድ እንዳይሠራጭ ምን አርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ ከጉምሩክ ኮሚሽን ለማጣራት ያደረገችው ተደጋጋሚ ሙከራ ሊሳካ አልቻለም።

ከ30 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው እና መቀመጫውን በደቡብ አፍሪካ ኬፕ ታውን ያደረገው የሲረስ ኩባንያ ከ40 በላይ የሚደርሱ ጣዕም ያላቸው የጭማቂ ምርቶች ያሉት ሲሆን፣ ምርቶቹ በመካከለኛው ምስራቅ እና አውሮፓ ገበያ ላይ ይገኛሉ። ሲረስ የአፕል ጭማቂ በመበስበስና በመሻገት የሚከሰተው “ፓቱሊን” የተባለው ጎጂ ንጥረ ነገር የተገኘበት ሲሆን፣ በፍራፍሬዎች ላይ የሚከሰት ከሻጋታ በሚመነጭ “ማይክሮቶክሲን” በጭማቂው ላይ በተደረገ የቤተ ሙከራ ፍተሻ መታየቱ ከተረጋገጠ በኋላ ነው ከገበያ እንዲሰበሰብ የተወሰነው።

ይህ ማይክሮቶክሲን በውስጡ ፖቱሊን የሚባል በአፕል እና በአፕል ምርቶቹ ውስጥ ከሚከሰት ሻጋታ የሚፈጠር መርዛማ ንጥረ ነገር ስለሆነ፣ በሌሎች የሲረስ ምርቶች ላይ ሳይሆን በአፕል ምርቱ ላይ ብቻ የተገኘ ነው። በአንድ ሊትር ውስጥ እንዲኖረው ከተፈቀደው 50 ማይክሮ ግራም ከፍ ያለ መጠን መገኘቱን ተከትሎ ዕርምጃው መወሰዱን አዲስ ማለዳ ከዳይሬክተሩ ለመረዳት ችላለች።

የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ የንግድ ቀጠና (ኮሜሳ) የንግድ ውድድር ኮሚሽን በኬንያ፣ በዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ በዛምቢያ፣ ዚምብብዌ፣ ኡጋንዳ፣ ሲሸልስ እና ሞሪሺየስ ገበያዎች ውስጥ ተሰራጭቶ የሚገኘውን ምርት ተሰብስቦ ወደ አምራች ኩባንያው እንዲመለስ ማሳሰቡ ይታወሳል።


ቅጽ 4 ቁጥር 159 ሕዳር 11 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com