የእለት ዜና

የኮቪድ 19 መድኃኒት ዝግጅትና ክትባት የመስጠቱ ሒደት

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ኹለት ዓመት ሊደፍን ቀናት ቢቀሩትም እስካሁን ከበሽታው የሚያድን መድኃኒት አልተገኘም። መድኃኒቱን ለማግኘት ከሚደረግ ርብርብ ጎን ለጎን ክትባቱንም ለማዘጋጀት በነበረ ጥድፊያ ከበርካታ ወራት በኋላ ውጤታማ መሆን ተችሎ ነበር። በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ክትባቱ በብዙ አገራት ተቀባይነት አግኝቶ የሥርጭቱን መጠን በአንጻራዊነት እንደቀነሰው ይነገራል።

ከምዕራባውን አገራት ዜጎች መካከል በአማካኝ ከግማሽ ያህሉ በላይ ተከትበው የተቀሩትም እየተጠባበቁ ይገኛሉ። የተወሰኑት ግን በተለያየ ምክንያት ላለመከተብ ወስነው ከመንግሥት ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ይገኛሉ። “ካልተከተባችሁ አገልግሎት ማግኘት አትችሉም” ከሚል መገደቢያ ጀምሮ፣ “ከሥራ ገበታችሁ ትነሳላችሁ” የሚሉ ማስጠንቀቂያ አዘል ዕርምጃዎች ይወሰዳሉ ቢባልም፣ ጥቂት የሚባሉ ዜጎቻቸው ‹‹አሻፈረን አንወስድም›› ብለው ምክንያት ያሉትን ደጋግመው በማስተጋባት ሒደቱን ተቃውመውታል።

አፍሪካን በተመለከተ፣ በተለይ ከሰሐራ በታች ያሉ አገራት 5 በመቶ የማይሞሉ ዜጎቻቸውን ብቻ ማስከተብ የቻሉ ሲሆን፣ ይህ የሆነው ከአመለካከት መለያየት ሳይሆን ከአቅም ዕጥረት እንደሆነ ባለሙያዎች ይስማሙበታል። አገራቱ የለጋሽ አገራትንና ተቋማትን እጅ ከመጠበቅ ውጭ እኩል አምርተው ወይም ገዝተው ዜጎቻቸውን ለመከተብ አለመቻላቸው ለተከታቢው ቁጥር ማነስ በዋና ምክንያትነት ይጠቀሳል። ይህ እውነታ ቢኖርም፣ የአፍሪካውያንን ቁጥር ለመቀነስ በማሰብ ምዕራባውያኑ የሠሩት የሕዝብ ቁጥር መቀነሻ አሻጥራቸው ነው በማለት ክትባቱን የሚቃወሙት አሉ።

ያም ተባለ ይህ፣ ሀብታም አገራቱ ዜጎቻቸውን ለመከተብና ኹሉንም በተቻለ መጠን ለማዳረስ ሲሞክሩ፣ ድሃዎቹ አገራትም የተወሰነውን የሕብረተሰብ ክፍል በመለየት ክትባቱን ቅድሚያ እንዲያገኙ እያደረጉ መሆኑ ይታወቃል። ኢትዮጵያም የዚሁ የመከተብ ዓላማን ለማሳካት በዘመቻ መልክ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿን ከኅዳር 13 ጀምሮ ባሉት 10 ቀናት በዘመቻ መልክ ለመከተብ ዕቅድ አውጥታ እየተንቀሳቀሰች ነው።

የኮቪድ መድኃኒትና ሕክምናው
አስከአሁን የኮቪድ-19 ቫይረስን ለመከላከል የሚሰጥ ክትባት እንጂ፣ የተያዘ ሰው ከበሽታው እንዲድን የሚሰጠው ሕክምና አልነበረም። ታማሚዎች ሆስፒታል ገብተው በተፈጥሮ ሒደት እንዲያገግሙ አጋዥ ከመሆን ባለፈ፣ በሽተኛውን ሙሉ በሙሉ የሚያድን የሕክምና ዘዴ ይፋ አልሆነም።

የቻይና ተመራማሪዎች ይህን ክፍተት ለመሙላት ምርምር ማድረግ ከጀመሩ የከረሙ ቢሆንም፣ ከሰሞኑ ተስፋ የሚሰጥ መረጃን ይፋ አድርገዋል። ግሎባል ታይምስ ላይ በወጣው መረጃ መሠረት ቻይናውያኑ በቀጣይ የፈረንጆቹ ዓመት ወደ ገበያ ይቀርባል ያሉትን የሕክምና ዘዴ ፈቃዱን ለማግኘት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደሚገኙ አሳውቀዋል። ከወር በኋላ ፈቃድ የማግኘት ሒደቱ ይከናወናል ብለው የተናገሩት ተመራማሪዎቹ፣ በቀጣዩ የፈረንጆቹ ዓመት ግልጋሎት ላይ እንዲውል መታቀዱን ጠቁመዋል። የምርምር ሒደቱ ወደ ውጤት እየተቃረበ እንደሆነ ቀደም ብለው አሳውቀው የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ለተግባራዊነቱ እየተቃረበ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ሕክምናው ክትባት የመስጠት ሒደቱን አስቀርቶ ሙሉ በሙሉ የሚተካው አለመሆኑን የተናገሩ ሲሆን፣ ከክትባቱ ጋር ጎን ለጎን የሚሰጥ የቴራፒ መንገድ ነው ብለዋል። መድኃኒቱ የሚዘጋጀው ከክትባቱ ውስጥ ከሚገኝ ንጥረ ነገርና የሰውነት የመከላከል አቅምን በሚገነቡ ንጥረ ነገሮች ቅንጅት ነው የተባለ ሲሆን፣ ታማሚው በቶሎ እንዲሻለውና ቫይረሱ በሰውነቱ ውስጥ የሚቆይበትን ጊዜ የሚያሳጥር ነው ተብሎለታል።

ሕክምናው የሚሰጠው ለኹሉም ሳይሆን፣ በጥቂቱና በመካከለኛ ደረጃ ለተጎዱ ብቻ ነው የተባለ ሲሆን፣ ክፉኛ ለተጎዱት ስለማገልገሉ ግን የተረጋገጠ ነገር የለም ብለዋል። የአስቸኳይ ጊዜ ፈቃድ ያገኛል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ የመጀመሪያ ነው የተባለ ሕክምና፣ በቻናይናና አሜሪካ መቀመጫውን ባደረገ የሕክምና ኩባንያና በሺንዜኑ ዢንዋ ዩኒቨርስቲ ትብብር እንደተሠራ ተነግሯል።

ሦስት ዙር ሙከራን አልፏል የተባለው ይህ መድኃኒት፣ በቴራፒ መልክ በተሰጣቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ አገር ዜጎች ላይ ውጤታማ መሆኑ ተነግሯል። ለተለመደው የኮቪድ ዝርያ ብቻ ሳይሆን ዴልታ ለተሰኘውና ለሌሎችም አዳዲስ ዝርያዎችም ያገለግላል ሲሉ ተመራማሪዎቹ አሳውቀዋል።

የክትባት አስፈላጊነት
በኮቪድ 19 ቫይረስ የተጠቁ ሕመምተኞችን ለማከም መድኃኒት ቢገኝም እንኳን፣ አስቀድሞ መከላከያው ክትባት አስፈላጊ መሆኑ አያጠራጥርም። የክትባቱ ዓይነትም ሆነ ጥራት ራሱን የቻለ መሥፈርት ቢኖረውም፣ ችግር የማያስከትል መሆኑ እስከተረጋገጠ ድረስ ሕብረተሰቡ ክትባቱን ቢጠቀም ተጠቃሚ እንደሚሆን ባለሙያዎች ይናገራሉ። አለመከተብ በበሽታው የመሞት ዕድልን በ15 ዕጥፍ ገደማ ይጨምራል ብለው ባለሙያዎች በጥናት ማረጋገጣቸውን በባለፈው ዕትማችን በወጣ ጽሑፍ አስነብበን ነበር።

አገራት ዜጎቻቸው እንዲከተቡ ከቅስቀሳ ጀምሮ የተለያዩ የማበረታቻ እንዲሁም የማስፈራሪያ ተግባራትን ሲያከናውኑ ቆይተዋል። መንግሥታት ተከተቡ እያሉ የሚቀሰቅሱትን ያህል ባይሆንም፣ ግለሰቦችና ቡድኖች “አትከተቡ የሴራ ውጤት ነው” እያሉ ሕብረተሰቡን በሐሳብ ያዋዥቁታል። በኹለቱ ተቃራኒ ሐሳቦች መካከል የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ውሳኔ ላይ ለመድረስ እንደሚቸገሩ ይነገራል። አንከተብም ብለው የወሰኑ የተለያየ ምክንያት በማቅረብ አስገዳጅ መመሪያዎችንም ሆነ ሕጎችን ለመቋቋም ሲሞክሩ ይሰማል።

አንዳንድ አገራት ነዋሪዎቻቸው ምግብ ቤትን የመሳሰለ አገልግሎት ሰጪዎች ጋር ገብተው ለመጠቀም ስለመከተባቸው የሚያረጋግጥ ሠርተፍኬት እንዲያሳዩ ያዛሉ። ይህ መንገድ አዋጭነቱ ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ አገልግሎት ላለማጣት ሲሉ የሚከተቡ እንደሚኖሩ ግን ይገመታል። በሌላ በኩል፣ ይህን ዓይነት ክልከላ ፈርተው ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሰዎች በመራቃቸው ተቋማቱ ገቢያቸው እንደቀነሰባቸው እየተነገረ ነው። ሰው ሠርተፍኬት ይዞ የማሳየቱ አዝማሚያ ዝቅተኛ በመሆኑ፣ ተጠቃሚያቸውን ከግማሽ በላይ ሊቀንስ እንደሚችል አንድ በስኮትላንድ የተካሄደ ጥናት ጠቁሟል። እንደጥናቱ ከሆነ በእንደዚህ ዓይነት አሠራር በወራት ውስጥ 75 በመቶ የሚሆኑ የግል አገልግሎት ሰጪዎች ምንም ድጋፍ የማያገኙ ከሆነ እንደሚዘጉ ያመላክታል።

የክትባቱ ተቃዋሚዎች
በኹሉም አገራት ማለት በሚቻል መልኩ ክትባቱን የሚቃወሙ፣ መከተብም የማይፈልጉ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉ ይታወቃል። በግድ አንከተብም ያሉትን እነዚህን ግለሰቦች ለማስገደድና ኹሉም እንዲከተብ ለማድረግ የሚሞከሩ ጥረቶችን በመቃወም በርካቶች አደባባይ ሲወጡ ይሰማል።

ከአውሮፓ አገራት ብዙ ያልተከተበ ዜጋ ያላት ኦስትሪያ ስትሆን፣ 35 በመቶው ያልተከተበ ነው። ይህንን ለመቀነስ በማሰብ ባለሥልጣናቷ ያልተከተበ፣ ምግብ ለመግዛት ወይ መሥራትን ለመሳሰለ ዓላማ ግድ ሆኖበት ካልሆነ በስተቀር፣ ከቤቱ ወጥቶ ከተያዘ እንደሚቀጣ ደንግጋለች። አንከተብም ያሉ ከተፈቀደላቸው ዓላማ ውጭ በየመንገድ ላይ ሲጓዙ ከተያዙ፣ እንዲሁም ካፌ ገብተው ከተገኙ ለቅጣት ያዳረጋሉ። እነዚህ ገደብ የተጣለባቸው ዜጎች ውሳኔውን ይቃወሙታል። አለመከተብ መብታችን ነው በማለት። እንደኹለተኛ ዜጋ መታየታችን ብቻ ሳይሆን እንደሕዝብ ጠላት ተደርገን እንድንታይ መደረጉ ተገቢ አይደለም ሲሉ ሒደቱን ይቃወሙታል።

ክትባት ዘመናዊ ሕክምና ከመጣ ወዲህ ትልቁ የዘርፉ ዕመርታ ቢሆንም፣ እንደ ኮቪድ ክትባት በርካታ ተቃውሞ ያገጠመው እንደሌለ የሚናገሩ አሉ። ሰዎች ክትባቱን ለምን እንደፈሩት የተለያየ ምክንያትን ያስቀምጣሉ። ለሕበረተሰቡ ተቃውሞ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የነበራቸው አስተዋጽዖ ከፍተኛ እንደሆነ በእንግሊዝ በተካሄደ አንድ ጥናት መረጋገጡን ፊውቸር የተሰኘው ድረ-ገጽ ዘግቧል። ክትባቱን በተመለከተ በተካሄዱ የዳሰሳ ጥናቶች የተቀባይነቱ መጠን ከቦታ ቦታ ይለያያል።

ክትባቱን ላለመከተብ የሚሰጡ ምክንያቶችም እንዲሁ ከአካባቢ አካባቢ ይለያያሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ክትባቱ የጎንዮሽ ጉዳት ያስከትላል በሚል የምዕራባውያን አገራት ዜጎች ሥጋታቸውን ሲያስተጋቡ፣ የዓለም ሕዝብን በተለይ የድሃውን ቁጥር ለመቀነስ ታስቦ የተዘጋጀ ነው የሚሉ ደግሞ በድሃ አገራት ውስጥ ይበረክታሉ።

ክትባቱን የማይከተቡ አብዛኞቹ ሰዎች ምንም ዓይነት ሳይንሳዊ ማስረጃ ሳይኖራቸው የሚያንገራግሩ መሆናቸው በጥናቱ ታውቋል። ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ምክንያትም ሳይኖራቸው ለመከተብ የሚፈሩት ቀዳሚውን ቦታ ይይዛሉ። የተከተበም ይያዛል የሚሉ የመኖራቸውን ያህል፣ መከተብ ሙሉ በሙሉ ከመያዝ ባያድንም በከፍተኘና መጠን ተጎድተው እንዳይሞቱ ያደርጋል መባሉን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆናቸው ይነገራል።

አብዛኛው ክትባቱን የማይፈልግ ሰው ኃላፊነት እንደማይሰማው ተደርጎ መወሰድ የለበትም የሚሉት እነዚህ የክትባቱ ተቃዋሚዎች፣ በፍላጎት ላይ የተመሠረተ እስከሆነ ድረስ መገለል የለብንም ብለው ያምናሉ። አብዛኞቹ የማይከተቡት በሽታው የለም ወይም አይዘንም ብለው ሳይሆን፣ ስለክትባቱ ያላቸው ጥርጣሬ ስለገዘፈባቸው እንደሆነ በተለያዩ አገራት የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚጠቁሙ ዶቼ ቬሌና ቢቢሲን የመሳሰሉ የሚዲያ ተቋማት እስካሁን የተካሄዱ ጥናቶችን ዋቢ አድርገው አስነብበዋል።

በአገራችን ኢትዮጵያም 10 ሚሊየን ሰዎችን ለመከተብ በታቀደበት ዘመቻ ፈቃደኛ የሆነ እንዲከተብ ጥሪ ቀርቧል። ለበሽታው ተጋላጭ ናቸው የተባሉ ከዚህ ቀደምም ቅድሚያ እንዲከተቡ ተደርገው ነበር። የአሁኑ የክትባት መጠን ከፈላጊው ብዛት ጋር ስለመመጣጠኑ በሒደት የሚታይ ቢሆንም፣ ያለው የክትባት መጠን ውስን በመሆኑ18 ዓመት የሞላቸው ዜጎች በየአቅራቢያቸው ባለ የሕክምና ተቋም ተገኝተው ክትባቱን እንዲወስዱ መንግሥትና ግብረ-ሠናይ ተቋማት በትብብር እየሠሩ ይገኛሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 159 ሕዳር 11 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com