የእለት ዜና

በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ገምዴል ወረዳ ከ60 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች ችግር ላይ ነን አሉ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ገምዴል ወረዳ የሚገኙ ከ60 ሺሕ በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች በሽብርተኝነት የተፈረጀው “ሸኔ” በሠነዘረው ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት ችግር ላይ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
አዲስ ማለዳ ከነዋሪዎቹ የሰማችው፣ ታጣቂ ቡድኑ ከኅዳር 8/2014 ጀምሮ ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት እንደከፈተባቸውና፣ በዚህም ከ60 ሺሕ በላይ የሚሆኑት የአካባቢው ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ነው።

ሸኔ ጥቃቱን ከሠነዘረበት ከኅዳር 8/2014 ጀምሮ የመጠለያ፣ የአልባሳትና የምግብ ችግር እንደገጠማቸው የተናገሩት ነዋሪዎቹ፣ ሁኔታውን ለወረዳው አስተዳደር ቢያሳውቁም ምላሽ ባለማግኘታቸው ችግር ላይ መሆናቸውን ነው ለአዲስ ማለዳ ያመላከቱት።
ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አያሌው ታደሰ የተባሉት ግለሰብ የተናገሩት፣ ታጣቂ ቡድኑ ወደ ባቦ ገምዴል ወረዳ ገብቶ ጥቃት ሲፈጽም፣ ከሚሊሻ ውጭ ከለላ ያደረገ የመከላከያም ሆነ የልዩ ኃይል አካል አለመኖሩን ነው።

አያይዘውም “ልዩ ኃይል በአካባቢው ቢኖርም ሲተኩስ የነበረው ወደ ሰማይ ነው፤ ይህ ደግሞ ኦነግ ሸኔ አካባቢውን ለመቆጣጠር አስችሎታል” በማለት ነው የዐይን እማኝነታቸውን የሰጡት።

አዛውንቶችን፣ እርጉዝ ሴቶችን፣ ሕፃናትንና የአካል ብቃት ችግር ያለባቸው ሰዎችን በጋሪ ጭነን በመውሰድ ነው ሕይወታቸውን ማትረፍ የቻልነው የሚሉት አያሌው፣ አሁን ላይ ተፈናቃዮቹ የውኃ፣ ምግብ፣ የመጠለያ እንዲሁም የአልባሳት ችግር አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል።
በጉዞና በስደት ላይ ሆነው የሚወልዱ በርካታ እናቶች እንዳሉ የተናገሩት የአካባቢው ነዋሪ፣ ከኹሉም በላይ እናቶችና ሕፃናት ኹኔታውን መቋቋም እንዳልቻሉ ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።

ከሚሠነዘረው ጥቃት ሕይወታቸውን ለማትረፍ ወደ አሶሳ ከተማ ሲጓዙ የነበሩ ኹለት መኪናዎች 90 ሰዎችን እንዳሳፈሩ፣ “በመንዲ እና አርዩ” አካባቢ መታገታቸውን አያሌው አክለው ተናግረዋል።

አስተያየት ሰጭው አክለውም፣ በሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ የተሳፈሩ 70 ሰዎችና፣ በአነስተኛና መለስተኛ መጓጓዧ የተሳፈሩ 20 ሰዎች ከታገቱበት ቀን ጀምሮ አድራሻቸው አልታወቀም ብለዋል።
አዲስ ማለዳ ከነዋሪዎቹ እንደተረዳችው ከሆነ፣ ከ60 ሺሕ በላይ የሚሆኑት የባቦ ገምዴል ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸውን ትተው የተሰደዱት በአካባቢው ለደኅንነታቸው ከለላ የሚያደርግ ኃይል ባለመኖሩ ነው።

ይህን በተመለከተም ታደሰ ይመር የተባሉት የአካባቢው ሚሊሻ፣ “የምን መከላከያ ነው? በአካባቢው ያለው የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ነው፤ እርሱም ነዋሪዎቹን በማስፈራራት አካባቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ ነው ያደረጉት” ሲሉ ነው የተመለከቱትን የተናገሩት።
ታጣቂ ቡድኑ በዘመናዊ መሣሪያ የታገዘና የተደራጀ ነው የሚሉት ታደሰ ይመር፣ በወቅቱ ከለላ ለማድረግ ሞክረው የነበሩት 15 ሚሊሻዎች ብቻ ናቸው ብለዋል። አያይዘውም በአካባቢው የነበረው ልዩ ኃይል፣ “ምንም አልተዋጋም፤ በዚህም ምክንያት ጥቃቱን መመከት አልተቻለም” ሲሉ ነው የተመለከቱትን የገለጹት።

በወረዳው የነበሩ በርካታ ቤቶች መቃጠላቸው፣ ነዋሪዎቹ ንብረታቸውን ማውጣት አለመቻላቸው፣ እንዲሁም አዝመራቸውን በሚሰበስቡበት ወቅት ለመፈናቀል መገደዳቸው ተገልጿል።
ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉት ዜጎች ከ60 ሺሕ በላይ ናቸው የሚሉት ታደሰ ይመር፣ ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ የወረዳው አስተዳደር ድጋፍ እንዳላደረገላቸው ጠቁመዋል።

ሌላኛው መለሰ ታዬ የተባሉት የአካባቢው ነዋሪ ከተፈናቀሉት መካከል መሆናቸውን ገልጸው፣ ታጣቂ ቡድኑ ጉርባ ኢቡ፣ ቦኒ እና ጊርባ አንድ በሚባሉ አካባቢዎች የነበሩ በርካታ የአማራ ተወላጆችን ቤት ንብረት ማቃጠሉን ገልጸዋል።
ግለሰቡ አክለውም፣ ከለላ ሲያደርጉ የነበሩ ኹለት ሚሊሻዎችና አንድ ገበሬ መቁሰላቸውን ያብራሩ ሲሆን፣ በወቅቱ የአንቡላንስ አገልግሎት ባለመገኘቱ ገበሬው ሠላም ወዳለበት አካባቢ የሄዱት በአህያ ተጭነው ነው ሲሉ ነው የተናገሩት።

ቤቶች ብቻ ሳይሆኑ በርካታ የግለሰብ ሱቆች ተቃጥለዋል የሚሉት መለሰ ታዬ፣ ነዋሪዎቹ ከአካባቢያቸው ለመውጣት ትራንስፖርት ከማጣታቸውም በተጨማሪ፣ ለተገኘውም ከዕጥፍ በላይ እንደከፈሉ ነው የጠቆሙት።
አያይዘውም፣ ከባቦ ወደ ነጆ ለመጓጓዝ ከዚህ በፊት ታሪፉ 30 ብር፣ እንዲሁም ከነጆ አሶሳ 120 ብር የነበረ ሲሆን፣ በተፈናቀሉበት ወቅት ለ30 ብር ታሪፉ 300 ብር፣ ለ120 ብር ታሪፉ ደግሞ 350 ብር እንደከፈሉ ነው ያመላከቱት።

ነዋሪዎቹ በመጨረሻም፣ ብርና አቅም ሳይኖራቸው ቀርቶ ጥቃቱ ከሚፈጸምበት ቦታ መውጣት ላልቻሉ ሰዎችና ለተፈናቃዮች የሚመለከተው አካል መፍትሔ እንዲሰጣቸው አሳስበዋል።

አዲስ ማለዳ ለደረሰው ችግር መፍትሔ ለማምጣት ምን እየተሠራ እንደሆነ ለመጠየቅ ወደ ባቦ ወረዳ አስተዳደር ጌጡ ገለቱ ስልክ ብትደውልም፣ ስለ ጉዳዩ ሲጠየቁ ስልክ በመዝጋታቸውና በድጋሚ ሲደወል ለማንሳት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ምላሻቸውን ማካተት አልቻለችም።


ቅጽ 4 ቁጥር 160 ሕዳር 18 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!