የእለት ዜና

የሰሜን ወሎ ወጣቶች “ባርነት ይብቃን” በማለት ይፋዊ ትግል መጀመራቸው ተነገረ

የሰሜን ወሎ ወጣቶች በራሳቸው ተነሳሽነት ተደራጅተው አካባቢያቸውን ለመጠበቅ እንቅስቃሴ መጀመራቸው ተገለጸ። ከባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ጀምሮ የራያ፣ የቆቦ ፣የዞብል እና ሌሎች የሰሜን ወሎ ከተማ ወጣቶች በህወሓት የተያዙ ቦታዎችን ለማስለቀቅ መደራጀት መጀመራቸውን የቆቦ ከተማ ከንቲባ ተናግረዋል። በዞብል ከተማ ላይ ከ10 ሺሕ በላይ ወጣቶች ተደራጅተው በርካታ ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙም አዲስ ማለዳ ሰምታለች።

የቆቦ ከተማ ከንቲባ አዲሱ ወዳጆ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 48 ያሉ የከተማው ነዋሪዎች በፈቃደኝነት ይሄንን አደረጃጀት በመቀላቀል፣ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛሉ።

የመደራጀት ሥራው የተጀመረው ጭፍራን ማዕከል በማድረግ ነበር። ይሁን እንጂ፣ ጭፍራ፣ኡዋ እና አውራ ከተሞች በጠላት እጅ ስለነበሩ፣ ወደ ዞብል በማዞር ሥራውን በስፋት በመሥራት ላይ እንደሆኑ ተጠቁሟል። ዞብል ከተማ ውስጥ ማዕከል ያደረገው ይህ ስብስብ፣ ወደጫካ መግባት ሲያስፈልግ በመግባት፣ ከህወሓት ጣጣቂዎች ጋርም በመፋለም ቦታዎችን እያስለቀቀ እንደሚገኝ ታውቋል።

በተጨማሪም፣ የወጣቶቹ ስብስብ ከህወሓት ቡድን የማረከውን መሣሪያ እና የተለያዩ ቁሳቁሶች በመጠቀም በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል ተብሏል። እንደከንቲባው አገላለጽ ፣ እስካሁን በአካባቢው በ 9 ግንባሮች ጦርነት ተከፍቶ፣ በከፍተኛ ተጋድሎ በአመርቂ ሁኔታ ወጣቶቹ ተከላክለዋል። ወጣቶቹ፣ በቂ ትጥቅ ባላገኙበት ሁኔታ፣ ከህወሓት በተማረኩ ወታደሮች መሣሪያ አካባቢያቸውን ከጠላት በማጽዳት ላይ ይገኛሉ ብለዋል። የዚህን አደረጃጀት ዓላማ የተገነዘቡ የአማራ ክልል ወጣቶች፣ በተለይ ከደብረ ብርሃን በ13/3/2014 የመጡ ከ120 በላይ ወጣቶች ወደዞብል በማምራት ትግሉን በይፋ ተቀላቅለዋል ሲሉ ተናግረዋል።

እነዚህ ወጣቶች፣ የጠላት መሣሪያዎችን ከየቦታው በማንሳት፣ ሎጂስቲክ በማቅረብ፣ አስከሬን በማንሳት፣ ምሽጎችን በመቆፈር፣ ለቆሰሉ ወገኖች የመጀመሪያ ዕርዳታ በመስጠት እና ሌሎችንም ሥራዎች በመሥራት ትግሉ በቀላሉ እንዲሳለጥ የድርሻቸውን አስተዋጽዖ በማድረግ ላይ ይገኛሉ ተብሏል። ሥራቸውን የሚያከናውኑት በመቄት፣ ጋሸና እና በራያ ግንባር ለኹለት ተክፍለው ነው የተባለ ሲሆን፣ በሽምቅ ገብቶ የህወሓትን አሰላለፍ የሚያጠና ቡድን ፣ ንብረት የት የት አካባቢ እንዳለ የሚያጠና አካል፣ እንዲሁም ከደሴና ከኮምቦልቻ የተሰረቁ ንብረቶች የተቀመጡበትን ቦታ በማጥናት መረጃ ለወገን ጦር በማድረስ ንብረት እንዲመለስ በማድረግ ቡድኑ ከፍተኛ አስተዋጾ እያደረገ ይገኛል።

ይሁን እንጂ እነዚህ በጎ ፈቃደኞች ፣ ህወሓትን ከአካባቢው ጠርጎ ለማስወጣት በሚያደርጉት የሞት ሽረት ትግል ፣ የክልሉ መንግሥት በቂ ድጋፍ እያደረገላቸው እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ሲገልጹ መቆየታቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ወጣቶቹ “ባርነት ይብቃ” በሚል ይህንን አደረጃጀት ካቋቋሙ ጀምሮ፣ የሎጂስቲክ፣ የትጥቅ፣ የተለያዩ የጦር ግንባር ቁሳቁሶችን ፣ በምርኮ ከማግኘት በዘለለ፣ መንግሥት ዕርዳታ እየሰጣቸው እንዳልሆነ ገልጸዋል። የመንግሥትን ሥራ በማቃለል፣ ወደ ድል የሚደረገውን ሩጫ ከማፋጠን አንጻር ከፍተኛ አሰተዋጽኦ እያደረጉ እንደሆነ ወጣቶቹ ይገልጻሉ። ነገር ግን፣ እንደ ዲሽቃ የመሳሰሉ የቡድን መሣሪያዎች ከመንግሥት ቢሰጥ፣ በአጭር ጊዜ ለድል እንደሚበቁ ይናገራሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የቆቦ ከተማ ከንቲባ የወጣቶቹን እንቅስቃሴ በመመልከት፣ ለክልሉ መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግ በመጠየቁ፣ በአሁኑ ሰአት፣ የራሽን፣ የሎጂሰቲክ እና የጦር መሣሪያ ድጋፍ መደረግ መጀመሩን ጠቁመዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 160 ሕዳር 18 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!