የእለት ዜና

በቆቦ ከተማ አንድ ኪሎ በርበሬ 950 ብር፣ አምስት ሊትር ዘይት 1ሺሕ 800 ብር እየተሸጠ ነው

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ፣ በጦርነቱ ምክንያት ለምግብነት የሚውሉ ጥሬ ዕቃዎች የአቅርቦት ዕጥረት በመከሰቱ፣ የአንድ ኪሎ በርበሬ ዋጋ 950 ብር፣ እንዲሁም አምስት ሊትር ዘይት አንድ ሺሕ 800 ብር እየተሸጠ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ባሳለፍነው ሳምንት ከራያ ቆቦ ወደ ሎጊያ ከተማ ያቀኑት የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ የገለጹት፣ የገበያ አገልግሎት ቢጀመርም የብር አቅርቦት ባለመኖሩ ለመገበያየት መቸገራቸውን ነው።

ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ሳራ መንገሻ የተባለችው ወጣት በራያ ቆቦ ከተማ የአንድ ኪሎ በርበሬ ዋጋ 950 ብር መድረሱን ለአዲስ ማለዳ አመላክታለች። በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት አካባቢውን ከመቆጣጠሩ በፊት የአንድ ኪሎ በርበሬ ዋጋ 380 ብር ነበር ያለችው ሳራ፣ አሁን 950 ከመሆኑም በተጨማሪ አቅርቦት ስለሌለ በዚህ ዋጋም ማግኘት እንዳልተቻለ ነው የገለጸችው።

ከዚህም በተጨማሪ በከተማው የዋጋ ንረት አሳይቷል የተባለው በርበሬ ብቻ ሳይሆን፣ የምግብ ዘይትም ጨምር መሆኑን ነው መረዳት የተቻለው። እንደ ሳራ ገለጻ ከሆነ፣ አካባቢው ሠላም በነበረበት ወቅት አምስት ሊትር ዘይት ሲገዛ የነበረው 500 ብር ሲሆን፣ አሁን ግን ከሦስት ዕጥፍ በላይ አድጎ ወደ አንድ ሺሕ 800 ብር ከፍ ብሏል ስትል ነው ለአዲስ ማለዳ ያመላከተችው።

መንገሻ አሸብር የተባሉ ግለሰብ በበኩላቸው፣ የአማራ ፋኖና ልዩ ኃይል በሚያደረገው ጥቃትን የመመከት ሥራ አርሶ አደሩ ሰብሉን እየሰበሰበ በመሆኑ የእህል ችግር ባይኖርም፣ ዘይትና በርበሬ ውድ መሆኑን መስክሯል።
በጦርነቱ ከሚሰነዘረው ጥቃት ባልተናነሰ፣ የአልባሳትና ለምግብ ፍጆታ የሚሆኑ ቁሳቁሶች ችግር እየገጠመን ነው የሚሉት መንገሻ፣ “ኮንጎ” ተብሎ የሚጠራው ጫማ ከ300 ብር እስከ 500 ድረስ እየተሸጠ መሆኑን በመገረም ተናግረዋል።

መንገሻ አያይዘውም “ኮንጎ” የተሰኘው ጫማ የእስከዛሬ ዋጋው 50 ብር እንደነበር አመላክተው፣ በዚህ ወቅት በውድ ዋጋም ለመግዛት ማግኘት እንዳልቻሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በከተማው ሱቆች የነበሩ አብዛኞቹ ቁሳቁሶች በህወሓት ኃይሎች መዘረፋቸው፣ በከተማ ለሚስተዋለው የቁሳቁስ የዋጋ መጨመርና የአቅርቦት ዕጥረት ምክንያቱን መሆኑን መንገሻ አሸብር ይናገራሉ።

አክለውም፣ በጦርነቱ ምክንያት ወደ ተለያዩ ቦታዎች ተፈናቅለው የነበሩ ሰዎች ወደ ከተማው መመለሳቸውን የጠቆሙ ሲሆን፣ ከቤታቸው ሳይፈናቀሉ የቆዩትን ጨምሮ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ሰሞኑን የቁሳቁስ ዋጋ ንረትና ዕጥረት እንዳጋጠማቸው አመላክተዋል።
ከራያ ቆቦ ከተማ ወደ ሎጊያ ያቀኑት ዳንኤል ሞላ የተባሉት ሌላኛው ወጣት፣ ከላይ የተዘረዘሩት ቁሳቁሶች ውድ መሆናቸውን መስክረው፣ በሎጊያ ከተማ ጫማ ገዝቶ ለመሄድ ቢፈልጉም የአንድ ሲሊፐር (ሸበጥ) ዋጋ 300 ብር እንደሆነባቸው ነው የገለጸው።
በጦርነቱ ምክንያት የተቸገሩ በርካታ ሰዎች ብር ለማውጣትና የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለመግዛት ወደ ሎጊያ ስለሚያቀኑ፣ በከተማዋም የቁሳቁሶች ዋጋ ውድ ሆኗል ሲሉ ነው ዳንኤል የተናገሩት።

በሌላ በኩል በከተማዋ የመብራት አገልግሎት በፈረቃ እየተሰጠ መሆኑንና የትራንስፖርት አገልግሎት መጀመሩንም ዳንኤል አክለው ገልጸዋል።

በአካባቢው የሚገኙት የህወሓት ታጣቂዎች እንደተመናመኑና አንጻራዊ መረጋጋት እንዳለ የተጠቆመ ሲሆን፣ ባሳለፍነው ኅዳር ስድስት 2014 የአማራ ፋኖና ሚሊሻ ህወሓትን ከዞብል ተራራ ቀጥሎ በሚገኘው “ጮሬ” ተብሎ በሚጠራው ቦታ ድል እንዳደረጉ ተመላክቷል።
በዚህም ወደ 43 የሚሆኑ የህወሓት ታጣቂዎች ተገለዋል የተባለ ሲሆን፣ ከፋኖ ና ከሚሊሻ 6 ሰዎች ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ ይህን ተከትሎም ህወሓት ከተማዋን ለቆ በመውጣቱ በከተማዋ አንጻራዊ መረጋጋት መኖሩ ተገልጿል።

ዳንኤል አክለውም፣ ጥቃት የሚሰነዝረውን የህወሓት ቡድን ሙሉ ለሙሉ ለማስወጣት ያልተቻለው የአካባቢው ታጣቂዎች የመገናኛ መሣሪያ ስለሌላቸውና በተለያየ ቦታ ያለው የአማራ ፋኖና ሚሊሻ መናበብ ስላልቻለ ነው ብለዋል።
በመጨረሻም፣ የሚመለከተው አካል የወታደራዊ የመገናኛ መሣሪያ ድጋፍ ቢያደርግላቸው ጥቃት የሚሰነዝረውን ቡድን ሙሉ ለሙሉ ማስወጣት እንደሚቻል ነው ዳንኤል የጠቆሙት።


ቅጽ 4 ቁጥር 160 ሕዳር 18 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!