የእለት ዜና

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና “ኢግል ላየን ቴክኖሎጂ” በደንበኞች ሆቴል አገልግሎት ክፍያ በጋራ ለመሥራት ተስማሙ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢግል ላየን ቴክኖሎጂ የተሰኘ በዲጂታል ንግድ መፍትሄዎች ማበልጸግ ላይ የተሠማራ የግል ኩባንያ፣ በደንበኞች ሆቴል አገልግሎት ክፍያ ላይ በጋራ ለመሥራት መስማማታቸው ታውቋል።
ድርጅቶቹ በሦስት የ‹ዲጂታል› መተግበሪያ ላይ ሥምምነት መፈጸማቸው የታወቀ ሲሆን፣ እነዚህም ‹ጌት ሩም፣ ጌት ፊ እና ሆቴል ቤዲንግ› የተሰኙ መሆናቸው ተገልጿል። መተግበሪያው አገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ ያሉ መንገደኞችን የሆቴል እና የማረፊያ አገልግሎት የእጅ ስልክን በመጠቀም እና በድረ-ገጽ አማካይነት በተቀላጠፈ መንገድ ማሟላት የሚቻል ሲሆን፣ ክፍያንም በመተግበሪያው አማከይነት መፈጸም እንደሚቻል ለመረዳት ተችሏል።

መተግበሪያውን ያበለጸገው ኢግል ላየንስ ቴክኖሎጂስ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት በእርሱፍቃድ ጌታቸው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት፣ መተግበሪያውን ለማበልጸግ ከአንድ ዓመት በላይ እንደወሰደ እና ከንግድ ባንክ ጋር ጥምረቱን ለማድረግ ከ3 ወራት በላይ የፈጀባቸው መሆኑን ነው። ሦስቱን ዲጂታል መተግበሪያዎች ለማበልጸግ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጋቸውንም ሥራ አስኪያጅ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

‹ጌት ሩም› የተሰኘው መተግበሪያ ከየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ያለ ተጓዥ ኪሱን ያገናዘበ ማረፊያ ማግኘት የሚችልበትን ሁኔታ ታሳቢ ተደርጎ እንደበለጸገ ሥራ አስኪያጅ ገልጸው፣ ከውጪ የሚመጡ ተጓዦች ከአሉበት አገር ሆነው በ‹ማስተር፣ ቪዛ እና ዩኒየን› ካርዶቻቸውን ተጠቅመው፣ በፈለጉት ሆቴል ለሚፈልጉት ቀናት ክፍያ ፈጽመው ያለ ሥጋት ወደ ኢትዮጵያ መግባት እንደሚችሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዳጂታል ዘርፍ ሥራ ክፍል አባል የሆኑ ስማቸው መጠቀሱን ያልፈለጉ ባልደረባ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ የዓለም አቀፍ የባንክ ሥርዓት ወደ ዲጂታል እና የካርድ አገልግሎት በመቀየሩ በአሁኑ ሰዓት ባንኩ በአለም ዓቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደረገውን የዲጂታል ሥርዓት ወደ ገበያው የማምጣት ሥራ ላይ መጠመዱን ነው የገለጹት።

በተጨማሪም፣ በጥሬ ገንዘብ የተለመደው የንግድ ሥርዓትን ወደ ኤሌክትሮኒክ ገበያ ለመቀየር ኢግል ላየን ቴክኖሎጂ ያመጣው መፍትሄ የአንበሳውን ድርሻ ሊጫወት እንደሚችል ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። በጥሬ ገንዘብ የሚደረግ ንግድ የወረቀት ኖቶችን ቶሎ እንዲያረጁ ከማድረጉ በተጨማሪ፣ መንግሥትን አዳዲስ ኖቶችን ለማሳተም የውጭ ምንዛሬ እንዲያወጣ ያስገድደዋል። ይህ ደግሞ ለኑሮ ውድነትና ዋጋ ግሽበት አስተዋጽዖ ያደርጋል ብለዋል።

መተግበሪያዎቹ ከፋይናንስ ደኅንነት እና ለ‹ሳይበር› ጥቃት ተጋላጭነት አንጻር፣ ጥብቅ ምዘና እና የማጣራት ሥራ በባንኩ በኩል እንደተሠራ የባንኩ ምንጭ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። የሆቴል ክፍያ አገልግሎትን ያቀላጥፋል የተባለው ቴክኖሎጂ፣ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንንት ኤጀንሲ የፋይናንስ ደኅንነት ማረጋገጫ ተስጥቶታል ተብሏል።

የቴክኖሎጅ መፍትሔዎቹ ከ400 በላይ ባለ ኮኮብ ሆቴሎች ባላት አገር፣ ለአገር ውስጥም ሆነ ከውጪ ለሚመጡ እንግዶች በ‹ጌት ሩም› የሚያርፉበትን ሆቴል እንዲመርጡ ከማስቻሉ በተጨማሪ፣ ማረፊያ ክፍል ሲይዙ የዋጋ ማረጋገጫ (ኢንቮይስ) ይደርሳቸዋል። ይህም ለተጓዡ ግብይቱ የተቀላጠፋና ዘመናዊ እንዲሆን ያደርግለታል ተብሏል።

ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ሆኑ የመንግሥት ተቋማት፣ በቡድን የሚመጡ እንግዶች ሲኖሯቸው እና የኮንፈረንስ ቱሪስቶች በሚጋብዙበት ጊዜ፣ ጨረታ በማውጣት እና በማስተዋወቅ፣ እንዲሁም ዋጋ ማቅረቢያ በመሰብሰብ የሚያጠፉትን ጊዜ እና ገንዘብ አስቀርቶ፣ ኹሉን በአንድ በያዘው የ‹ሆቴል ቢዲንግ› መተግበሪያ አማካይነት በአጭር ግዜ አገልግሎት መፈጸም ያስችላቸዋል ሲሉ በእርሱፍቃድ ገልጸዋል።

ሆቴሎች ከደንበኞና ተቋማት ያልተከፈለ ሂሳብ ለመሰብሰብ የሚወስድባቸውን ኃይል ከግማሽ በመቶ በላይ የሚያስቀር በመሆኑ፣ ለሆቴል መስኩ ይበል የሚያስብል መፍትሔ ነው ሲሉ የሆቴል ባለሙያ የሆኑት እና በማማከር ሥራ ላይ የተሠማሩት ኤርሚያስ አለሙ ጠቁመዋል።

የኢግል ላየንስ ቴክኖሎጂስ፣ ከወራት በፊት ከ22 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ባሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ለሕዳሴው ግድቡ በውጪ አገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ገቢ ማሰባሰቢያ “ኢትስ ማይ ዳም” የተሰኘ መተግበሪያ በማበርከት ከ166 ሺሕ ዶላር በላይ ማሰባሰብ እንዲቻል አስተዋጽዖ አድርጓል።


ቅጽ 4 ቁጥር 160 ሕዳር 18 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!