ንግድ ባንክ ከአንድ ሺሕ በላይ ቅርንጫፎቹ ላይ ክለሳ አካሔደ

0
655

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በየሦስት ዓመቱ በሚያካሒደው የቅርንጫፎች አቅም እና ደረጃ ክለሳ መሰረት በተገባደደው የበጀት ዓመት አንድ ሺሕ 164 ቅርንጫፎች ላይ ክለሳ ማከናወኑ ታወቀ። በክለሳው ውጤት መሰረትም 4 ቅርንጫፎችን ወደ ልዩ ቅርንጫፍነት፣ 28 ቅርንጫፎችን ወደ ደረጃ አራት፣ 150 ቅርጫፎችን ወደ ደረጃ ሦስት፣ 225ቱን ወደ ደረጃ ኹለት ያሳደገ ሲሆን 11 ቅርንጫፎች ደግሞ ከነበሩበት ዝቅ ተደርገዋል።

ለደረጃ አወጣጡ እንደመለኪያ የተወሰዱት የቅርንጫፉ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን፣ የተጠቃሚዎች ቁጥር፣ የአገልግሎት ዓይነት ብዛት፣ የውጪ ምንዛሬ ግኝት እንዲሁም ቅርንጫፉ ካበደረው ገንዘብ ውስጥ የተበላሹ ብድሮች መጠን ለደረጃ አሰጣጡ መሰረት ናቸው።

በእነዚህ መሰረትም በ2011 በጀት ዓመቱ መገባደጃ ላይ በተጠናቀቀው የደረጃ ማሻሻል ወቅት ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ቅርንጫፎች ከአንድ ደረጃ በላይ አድገዋል። በክለሳው መሰረት ቅርንጫፎቹ የሚያስፈልጋቸውን ሥራ አስኪያጆች ለመተካትም ከዚህ በፊት በምደባ አማካኝነት የነበረውን አሰራር በመቀየር በቦታዎቹ ላይ ማስታወቂያ እንዲወጣ ተደርጓል።

ባንኩ ባወጣው ከ400 በላይ የውስጥ የሥራ ማስታወቂያ የቅርንጫፎቹ ሥራ አስኪያጆች መሳተፍ የሚችሉ ቢሆንም ቀድመው በነበሩበት ቅርንጫፍ ላይ ግን መወዳደር እንደማይቸሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በባንኩ አሰራር መሰረትም አንድ ሠራተኛም በአንድ ጊዜ ከአንድ ደረጃ በላይ ሊያድግ አይችልም።

የአዲስ ማለዳ ምንጭ አክለው እንደተናገሩት አንድ ሥራ አስኪያጅ የሥራ እርከኑ ደረጃ 12 ላይ ሆኖ የሚያስተዳድረው ቅርንጫፍ ከደረጃ አንድ ወደ ሦስት ካደገ ለቅርንጫፉ የሚያስፈልገው የሥራ አስኪያጅ እርከን 14 ላይ ያለ ቢሆን በአንድ ጊዜ ከአንድ ደረጃ በላይ ወደ ላይ ማደግ ስለማይቻል ሥራ አስኪያጁን ይዞ መቀጠል አይቻልም ብለው ያስረዳሉ። ከዚህ ቀደም እንዲህ ዓይነት ክፍተት በሚያጋጥምበት ወቅት በሰው ኀይል ክፍል አቅራቢነት የባንኩ ማኔጅመንት ሥራ አስኪያጆቹን የሚሾም ሲሆን አሁን ግን የሥራ ማስታወቂያ መውጣቱ ከዚህ ቀደም ይሠራበት ከነበረው የተለየ ነው ይላሉ።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው አንድ የባንኩ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ግን ባንኩ አሁን ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት ባሳደግነው ቅርንጫፍ ላይ እንዳንወዳደር ከመደረጉ ባሻገር ደረጃ ማስተካከሉ በዚህ ዓመት ቢሠራም ላለፉት ዓመታት በብቃት ያስተዳደረ ሥራ አስኪያጅ ከቦታው ማንሳት አግባብ አይደለም ይላሉ።

ለአዲስ ማለዳ ቅሬታውን ያቀረቡት ሠራተኞች እንዳሉት ማስታወቂያው ከደረጃ 11 በላይ ያለ ማንኛውም ሠራተኛ ለቦታው ማመልከት እንደሚችል የሚጠቅስ ሲሆን በዚህም መሰረት አንድ ሥራ አስኪያጅ የነበረን ሰው ዝቅ ሊደርግ ይችላል ብለው እንደሚገምቱ ተናግረዋል። ይህም አንድ ሰው ከሥራ ደረጃው በዲሲፕሊን ጥፋት ካልሆነ በቀር ዝቅ መደረጉ አግባብ አይደለም ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

“ከዚህ ቀደም ለምሳሌ 4 ኪሎ ቅርንጫፍ ከደረጃ 3 ወደ 4 ከፍ ቢል ወይ ሥራ አስኪያጁ አብሮ ያድጋል ወይ ደረጃ ሦስትን ሲስተዳድሩ ከነበሩ ሥራ አስኪጆች መካከል ተወዳድሮ ይሾማል እንጂ እንዲህ ዓይነት ሁሉም ቅርንጫፍ ላይ ማስታወቂያ ማውጣት ያልተለመደ እና ሌላ ቀውስ የሚፈጥር ነው” ሲሉ ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ ሠራተኛ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የሚያድግ ቅርጫፍ ሲኖር ሥራ አስኪያጁም አብሮ ያድግ የነበረ ሲሆን ምናልባት የአቅም ችግር ቢኖር እንኳን አቅማቸውን የማሳደግ እንጂ ከሥራ ድርሻቸው ላይ የማንሳት ድርጊት ተፈጽሞ እንደማያውቅ ተናግዋል።

አዲስ ማለዳ ሐምሌ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here