የእለት ዜና

የብሔራዊ ውይይት ውጥን እና የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ

በኢትዮጵያ፣ በተለይ ከ2008 ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች ያጋጠመው የጸጥታ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ወደ ጦርነት ካመራ አንድ ዓመት አልፎታል። በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮች እልባት አለማግኘታቸውን ተከትሎ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ ሥልጣናቸውን መልቀቃቸው የሚታወስ ነው።

በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተከሠተው የጸጥታ ችግር ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የሥልጣን መልቀቅ ምክንያት መሆኑን ተከትሎ፣ በ2010 መጋቢት ወር ላይ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን መጥተዋል።
በወቅቱ ወደ ሥልጣን የመጡት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ያለውን የጸጥታ ችግር ይፈታሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸው ነበር። ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያዊነትን የሚያንጸባርቁ ሐሳቦችን በማራመድ ተቀባይነት አግኝተዋል።

ይሁን እንጂ፣ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካበቢዎች የሚታዩ የጸጥታ ችግሮች በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ መሪነት መምጣት ሊቀረፉ አልቻሉም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ አስካሁን ድረስ እልባት ካላገኙ የጸጥታ ችግሮች መካከል በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ካማሺና መተከል ዞኖች፣ በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅና በምዕራብ ወለጋ ዞኖች በየጊዜው የሚከሰቱት ችግሮች ተጠቃሽ ናቸው።

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩት የጸጥታ ችግሮች ዋና ምክንያታቸው ሥር የሠደደ የብሔር ፖለቲካ መሆኑን ብዙዎች ይገልጻሉ። ይህ በእንዲህ እንዳለ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚታየው የጸጥታ ችግር መነሻው ኢትዮጵያን በበላይነት ለ27 ዓመታት የገዛው አሁን በሽብርተኝንት የተፈረጀው ህወሓት የፈጠረው የተበላሸ የፖለቲካ ምህዳር መሆኑን ከመንግሥት እስከ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ያምናሉ።

እዚህም እዚያም የሚታየው የጸጥታ ችግር እልባት ሳያገኝ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ፣ ህወሓት ቀስ በቀስ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ቅራኔ ውስጥ መግባቱ የሚታወስ ነው።
በተለያዩ አካባቢዎች የሚታየውን የጸጥታ ችግር እልባት ለመስጠት ብሔራዊ ውይይትና መግባባት እንደሚያስፈልግ የሚገልጹ እንደ ‹ማይንድ ኢትዮጵያ› ያሉ ድርጅቶች ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ሲሠሩ ነበር።

የፌዴራል መንግሥት እና የህወሓት ተቃርኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሠፋ መምጣቱን ተከትሎ፣ ጥቅምት 24/2013 ላይ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ጦርነት ተቀስቀቅሶ እስካሁን እንደቀጠለ ነው። በተለየዩ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶችን ለመቅረፍና የፖለቲካ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የታሰበው ውጥን በኅዳር ወር ይጀመራል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ የጦርነቱ መቀስቀስ ሒደቱ ሳይጀመር እንዲቀር አድርጎታል።

አገር አቀፍ ብሔራዊ ወይይትና መግባባት ከመንግሥት እስከ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የታመነበት ጉዳይ እየሆነ ቢመጣም እስካሁን እውን ሊሆን አልቻለም። ለዚህ ደግሞ አሁን ያለንበት ወቅታዊ ሁኔታ እንደ አንድ ምክንያት ይወሰዳል።
በማይንድ ኢትዮጵያ በኩል የተጀመረው የብሔራዊው ውይይት ጉዳይ በመንግሥት በኩል ተቀባይነት ማግኘቱን ተከትሎ፣ ኹሉን አካታች ብሔራዊ ውይይት እንደሚካሄድ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አዲስ መንግሥት በተመሠረተበት ማግስትና በጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓለ ሲመት ወቅት መግለጹ የሚታወስ ነው።

ይህንነኑ ተከትሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ታኅሳስ 1/2014 ባካሄደው ኹለተኛ መደበኛ ስብሰባው፣ በኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ ዐዋጅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ ረቂቅ ዐዋጅ የተዘጋጀው፣ መንግሥት በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ይሁንታ አግኝቶ ሲመረጥ ቃል ከገባባቸው አገራዊ ጉዳዮች መካከል፣ ኹሉን አካታች የሆነ አገራዊ ምክክርና ውይይት በማካሄድ አገራዊ መግባባት እና በአገር ጉዳይ የጋራ አቋም እንዲኖር የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራት መወሰኑን ተከትሎ ነው ተብሏል።

የጠቃላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ስለውሳኔው ባወጣው መረጃ፣ መሠረታዊ በሚባሉ አገራዊ ጉዳዮች በተለያየ ጎራ የተሰለፉ የፖለቲካ ልኂቃንም ሆኑ ምልዓተ-ሕዝቡ ተቀራራቢና በአገራዊ አንድነት ገንቢ አቋም እንዲይዙ ለማድረግ፣ አካታች አገራዊ ምክክሩን ተግባራዊ ለማድረግ በገለልተኝነት ለመምራትና ለማስተባበር የሚችል ቅቡልነት ያለው ተቋም ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ጠቅሷል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ ረቂቅ ዐዋጅ ላይ ተወያይቶ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲያጸድቀው ማስተላለፉ የሚታወስ ነው። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔን መሠረት አድርጎ ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታኅሳስ 7/2014 ባካሄደው አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሦስተኛ መደበኛ ስብሰባ፣ በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ ረቂቅ ዐዋጅ ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

ማይንድ ኢትዮጵያ የጀመረው የብሔራዊ ውይይት ውጥን ባሳለፍነው ኅዳር ወር ይጀመራል ተብሎ የነበረ ቢሆንም እስካሁን አልተካሄደም። ማይንድ ኢትዮጵያ ቅድመ ብሔራዊ የውይይት መድረክ ማካሔዱ የሚታወስ ሲሆን፣ ቅድመ ውይይቱ በአጠቃላዩ ብሔራዊ ውይይቱ ኹኔታ ላይ ያተኮረ ነበር።

ብሔራዊ የውይይት መድረኩ ሲጀመር የሰላም ሚኒስቴር፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ የብዙኃን መገናኛዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ መገለጹ የሚታወስ ነው።
አሁን ላይ በመንግሥት እና በማይንድ ኢትዮጵያ የተወጠነው ብሔራዊ የውይይት መድረክ በኢትዮጵያ ላለው ችግር የመፍትሔ አካል እንደሚሆን ብዙዎች ይገልጻሉ። በሌላ በኩል ደግሞ አሁን ያለው ወቅታዊ ኹኔታ ብሔራዊ የውይይት መድረክ ለማካሄድ የሚያስችል አይደለም የሚሉ አሉ።

ብሔራዊ የውይይት መድረክ ለማካሄድ አሁን ላይ ያለው ጦርነት እልባት ማግኘት እንዳለበት ስማቸው እንዲገለጽ የማይፈልጉ የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ ጠቁመዋል።
የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ ያለው ችግር የሚፈታው በብሔራዊ ውይይትና መግባባት መሆኑን ያምናሉ፣ ይሁን እንጅ ብሔራዊ መግባባቱ ውጤት በሚያመጣ ኹኔታ በአግባቡ ካልተካሄደ የሚፈለገውን ውጤት ላያመጣ እንደሚችል ሥጋት አላቸው።
“መንግሥት ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማሳተፍ ያደረገው ሙከራ መልካም ጅምር ነው” የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ፣ መንግሥት ያሉትን ችግሮች ለመፍታት በሚያደርጋቸው ሙከራዎች ላይ እንቅፋት የሚሆኑ እና ወደ ኋላ የሚጎትቱ የቀደሙ ችግሮች እንደሚገጥሙት ይገልጻሉ።

በመሆኑም፣ መንግሥት ወደፊት በሚያካሂደው ብሔራዊ የውይይት መድረክ ላይ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ችግሮችን ከወዲሁ ለይቶ ማቃለልና መንገድ መጥረግ እንዳበት ጠቁመዋል። መምህሩ እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ ያለው ችግር በአጭር ጊዜ የሚፈታ ባይሆንም ብሔራዊ ውይይቱን ለማድረግ አስቻይ ኹኔታዎችን በመፍጠር ውይይቱን በዚህ ዓመት መጀመር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ያሉት ችግሮች ያለ ውይይት ይፈታሉ ብዬ አላስብም የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ፣ ከፖለቲካ እስከ ሕገ-መንግሥት ድረስ ያሉ ችግሮች በውይይት መሻሸል እንደሚገባቸው ጠቁመዋል። የብሔራዊ ውይይት ሒደቱን ሊያስፈጽም የሚችል ተቋም ለማቋቋም በመንግሥት በኩል የተጀመረው ሥራ ወሳኝ መሆኑም ተመላክቷል።

በብሔራዊ ውይይቱ የተለያዩ ሐሳቦች መንጸባረቅ አለባቸው የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ፣ ውይይቱ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት በሚፈጥር ኹኔታ ተቀርጾ መመራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ትልቅ ችግር እየሆነ የመጣውን ጥላቻ ላይ የተመሠረተ መገዳደልና የበቀል ፖለቲካ፣ በብሔራዊ ዕርቅ እስካልተፈታ ድረስ ወደ ፊት መጓዝ እንደማይቻል መምህሩ ጠቁመዋል። በመሆኑም፣ እስካሁን የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ጥላቻና በቀልን በሚያስቀር ኹኔታ በብሔራዊ ዕርቅ መቋጨት አለባቸው ብለዋል።

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በጦርነት ጉዳት ያስተናገደውን የማኅበረሰብ ክፍል መልሶ ማቋቋም ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠርና ግጭቶችን ለማስቀረት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በጦርነቱ የተጎዳውን የማኅበረሰብ ክፍል በተገቢ ሁኔታ መልሶ ማቋቋም ካልተቻለ ብሔራዊ መግባባቱን ወደ ኋላ የሚጎትት ችግር ሊሆን እንደሚችል ተመላክቷል።

ብሔራዊ ውይይት በአንድ አገር ውስጥ ችግር በሚያጋጥምበት ወቅት በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ለመፈለግና ችግሩን ለማስቀረት የሚጠቅም የጋራ መድረክ መሆኑን ብዙዎች ይገልጻሉ። ብሔራዊ ውይይት ለዘላቂ የግጭት አፈታት፣ ለፖለቲካዊ ለውጥና ኹሉን አሳታፊ ለሆነ የፖለቲካዊ ሥርዓት ግንባታ ተመራጭ መንገድ መሆኑ ይገለጻል።

ብሔራዊ ውይይትና መግባባት በኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ታሪካዊ ጉዳዮች ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት እና ችግሮችን ወደ ኋላ በመተው አዲስ ምዕራፍ ለመጀመር በር ከፋች መፍትሔ እንደሆነም ይነገርለታል።


ቅጽ 4 ቁጥር 163 ታኅሣሥ 9 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!