የእለት ዜና

ለኢንተርፕራይዞች 200 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ የብርድ በጀት መያዙ ተገለጸ

የአነስተኛና መካካለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንስ ፕሮጀክት ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የብድር ድጋፍ የሚውልና በሦስት ዓመት የሚተገበር ተጨማሪ የ200 ሚሊዮን ዶላር በጀት መኖሩን አስታወቀ።
ፕሮጀክቱ በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ የሚገኙ አምራች ኢንተርፕራይዞችን በማሽን ሊዝ፣ በሥራ ማስኬጃና በንግድ ልማት አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ነው የገለጸው። ይህም የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞችን ውጤታማነት ለማሳደግ በፋይናንስ፣ በመሰረተ ልማትና በጥሬ ዕቃ ግብዓት አቅርቦት፣ በኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት እንዲሁም በገበያ ትስስር እንዲደገፉ የሚደረግ ስራ አካል ነው ተብሏል።

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ የመንዝወርቅ ግረፌ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ቀደም ብሎ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የተሰጠው ብድር በቂ ባለመሆኑ እንዲሁም በኮቪድ ምክንያት የተጎዱ አንዳንድ ኢንተርፕራይዞች በመኖራቸው እነሱን ለመደገፍ ታልሞ ነው ብለዋል። የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የብድር ፍላጎት ከዚህ ቀደም ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ እድገት ማሳየቱ ለተጨማሪ ብድር በጀቱ መዘጋጀት ሌላ ምክንያት ነው ተብሏል።

ብድሩ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ ሆነው፣ በአነስተኛና መካከለኛ ምድብ ውስጥ ለሚገኙ ለኹሉም ኢንተርፕራይዞች የሚሰጥም መሆኑን ነው የገለጹት። የሚሰጠው ብድር ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሊዝ፣ እንዲሁም ለስራ ማስኬጃ በሚል ከባንኮችና ከማይክሮ ፋይናንሶች መሆኑንም አስተባባሪዋ ተናግረዋል።

ብዙ ጊዜ ኢንተርፕራይዞች በዋስትና ምክንያት ከባንኮች ብድር አያገኙም ያሉት የመንዝወርቅ፣ በዚህ ፕሮጀክት ግን በሰበሰቡት ፕሮፎርማ አዋጭነታቸው ተጠንቶ መሳሪያ በኪራይ ይወስዳሉ፣ በኋላም የመሳሪያውን ባለቤትነት ደብተር ከባንኩ እንደሚያገኙ አስረድተዋል።
ኢንተርፕራይዞች የስራ ማስኬጃ የሚሆነውን ብደር ከባንኮችና ከማይክሮፋይናንሶች የሚያገኙ ሲሆን፣ ባንኮችም ይህን ገንዘብ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ተበድረው ያቀርባሉ ነው ያሉት። ይህም ብድር በኢንተርፕራይዞች በኩል የሚታየውን የብድር አቅርቦት እጥረት ይቀርፋል ተብሏል።

ባንኮችና ማይክሮፋይናንሶች በራሳቸው የማበደሪያ ወለድ እንደሚያበድሩና የኢትዮጵያ ልማት ባንክም 11 በመቶ በሚሆን የብድር መጠን ለኢንተርፕራይዞች የሚያቀርብ መሆኑንም አመላክተዋል። የድጋፍ ብድሩ በመላ አገሪቱ ለሚገኙ ኢንተርፕራይዞች የቀረበ ሲሆን፣ በገንዘብ ተቋማቱ ኹሉም ቅርንጫፎች ብድሩ የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ተቋሙ በ2009 ሥራ ሲጀምር ከሰባት ሺሕ የማይበልጡ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች እንደነበሩ የተገለጸ ሲሆን፣ አሁን ላይ በሚሰጣቸው ድጋፎች ቁጥራቸው ከ21 ሺሕ በላይ ደርሷል ነው የተባለው። ይህ የፋይናንስ ፕሮጀክትም ከልማት ባንክ ጋር በመተሳሰር የኢንተርፕራይዞችን የፋይናንስና የንግድ ልማት አገልግሎት ችግር ለመፍታት ለተጨማሪ ሦስት ዓመት የትግበራ በጀት መፈቀዱ የዘርፉን የፋይናንስ ፍላጎት በተሻለ ሁኔታ ለመፍታትና ለመደገፍ መልካም ዕድል እንደሚፈጥር ተመላክቷል።

ስለሆነም ድጋፉን በተገቢው ሁኔታ በመጠቀም የኢንተርፕራይዞችን ውጤታማነት ማሳደግና በሂደትም ዘርፉ ለአገር በቀል ኢኮኖሚው ግንባታ የሚኖረውን ድርሻ እንዲወጣ ለማስቻል መስራት ያስፈልጋል ተብሏል።
በመጨረሻም ፕሮጀክቱ ከጥቃቅን የተሸጋገሩ ሴት አምራቶችን ለመደገፍና ለኢንተርፕራይዞች የገበያ መረጃ በማቅረብና ለምርቶቻቸው የገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድ የተሻለ ዕድል ይዞ የመጣ መሆኑም ተነግሯል።


ቅጽ 4 ቁጥር 163 ታኅሣሥ 9 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!