የእለት ዜና

የኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የተከፈለ ካፒታሉን ወደ አንድ ቢሊዮን ብር ሊያሳድግ ነው

የኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ አ.ማ. ታኅሳስ 1/2014 ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔው፣ የተከፈለ ካፒታሉን ከግማሽ ቢሊዮን ብር ወደ አንድ ቢለዮን ብር ለማሳደግ መወሰኑን አስታወቀ።
የኢንሹራንስ ኩባንያው የተከፈለ ካፒታሉን በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ወደ አንድ ቢለዮን ብር ለማሳደግ ውሳኔ ላይ መድረሱን ለማወቅ ተችሏል።

የኦሮሚያ ኢንሹራንሱ ኩባንያ ካፒታሉን ለማሳደግ የወሰነው እየጨመረ በመጣው የኢንሹራንስ ገበያው ውድድር ውስጥ ብቃት ያለውና ተወዳደሪ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ ስለታሰበ ነው ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ የኩባንያው ከፍተኛ የተከፈለ ካፒታል ሙሉ ለሙሉ ተከፍሎ በማለቁ እና የካፒታል ጥንካሬ መፍጠር በማስፈለጉ፣ የኩባንያውን የተከፈለ የካፒታል መጠን ማሳደግ አስፈላጊ ሆኗል ሲሉ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጸሚ ትዕግስቱ ሽፈራው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በተያያዘም፣ የኩባንያውን “ካፒታል ማሳደጉ ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ በሦስት ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፈውን ባለ 32 ፎቅ የኩባንያውን ዋና መሥሪያ ቤት ግንባታ ለማካሄድ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል” ሲሉ ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።
በ2013 የቻይናው ‹ጂያንግዚ ኮንስትራክሽን ኩባንያ› የኢንሹራንስ ኩባንያው ዋና መሥሪያ ቤት በ1.1 ቢሊዮን ብር ለመሥራት ጨረታ ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

የኢንሹራንስ ኩባንያው ባሳለፍነው 2013 በጀት ዓመት 141 ሚሊዮን ብር ያገኘ ሲሆን፣ ከ 2012 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸርም የ92.73 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል። በዚህ መሠረትም ብር 1000 ዋጋ ያለው እያንዳንዱ አክሲዮን 290 ብር ትርፍ ያስመዘግባል ማለት እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል።

በተያያዘ ኩባንያው ቅርንጫፎቹን 51 ከማድረሱ ጋር ተያይዞ፣ አጠቃላይ አስተዳዳራዊ ወጪው ከአምና ወይንም ከ2013 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ18.4 በመቶ ብልጫ ያሳየ ሲሆን፣ አጠቃላይ አስተዳዳራዊ ወጪው 162.6 ሚሊዮን ብር ሆኖ መመዝገቡን ለማወቅ ተችሏል።

ሥራ አስፈጻሚው ለአዲስ ማለደ እንደገለጹት ከሆነ፣ የኢንሹራንስ ኩባንያው በያዝነው ዓመት የማይክሮ ኢንሹራንስን ተደራሽ ለማድረግ በተለየ መልኩ ይሠራል።
ይህ ማይክሮ ኢንሹራንስ፣ በግብርና ዘርፉ በተለይም ከብት በማርባት እና የንግድ ሰብል በማምረት የሚተዳደረው የማኅበረሰብ ክፍል ሊገጥመው ከሚችለው ያልታሰበ ተፈጥሯዊ አደጋ ለመታደግ የሚያገለግል ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በቦረና በተከሰተው ደርቅ የተጎዱ አርብቶ አደር እና አርሶ አደር የኢንሹራንስ ኩባንያው ደንበኞችን ለመታደግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

ኢንሹራንሱ በ2020/21 በጀት ዓመት፣ ሕይወት ነክ ያልሆኑ ኢንሹራንስ እና ማይክሮ ኢንሹራንስን ጨምሮ፣ ከባለፈው 2019/20 በጀት ዓመት በ35.4 በመቶ የተሻለ ወይንም አጠቃላይ 671 ሚሊዮን አረቦን ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ በሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ አርባ በመቶ ዕድገት አሳይቶ አምና ከሰበሰበው 9.5 ሚለዮን አረቦን፣ ሰኔ 30/2013 በተገባደደው የበጄት ዓመት ወደ 13.3 ሚሊዮን ብር ማደጉን አዲስ ማለዳ ለመረዳት ችላለች። ኢንሹራንሱ ሰኔ 30 እስከተጠናቀቀው በጀት ዓመት ድረስ 192.4 ሚሊዮን ብር ሕይወት ነክ ላልሆነ ኢንሹራነስ የከፈለ ሲሆን፣ 5.1 ሚሊዮን ብር ለሕይወት ካሳ መክፈሉን ለማወቅ ተችሏል።

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ከ12 ዓመት በፊት በ25 ሚሊዮን ብር እና በ540 ባለድርሻዎች የተቋቋመ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት የ500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል እና የ694.2 ሚሊዮን ብር በጊዜ ገደብ ተቀማጭ ኢንቨስትመንት ማድረጉን ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 163 ታኅሣሥ 9 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!