የእለት ዜና

‹‹ከቤታችን ስድስት አስከሬን ወጥቷል›› ሙላቱ በየነ የመሃል ወንዝ ቀበሌ ነዋሪ

ዬጦርነት የሰው ልጆች ታሪክ ላይ በተደጋጋሚ ተጽፎ የሚገኝ ክስተት ነው። በየጦርነቱ ዕልፍ ሕይወቶች ተሰውተዋል፤ ቤተሰብ ተበትኗል፤ ማኅበረሰብ ፈርሷል፤ አገር ተናግቷል። እንደ ኢትዮጵያውያን የውስጥ ግጭትና ጦርነት ላይ እንደነዳጅ የሚርከፈከፍን የውጪ ተጽዕኖ እየታገሉ አገርን ለማዳን ኅብረት መፍጠር ያልቻሉ ዜጎች፣ በጦርነት የተነሳ አገራቸው ሲፈርስ የዐይን ዕማኝ ሆነዋል። እንዲህ እንደ ኢትዮጵያውያን ታድያ የአገርን ከባድ ወቅት ተጋግዞና ተደማምጦ፣ ሸክሙን ተቀብሎ ለማሻገር የሚከፈለው መስዋዕትነት ቀላል አይደለም።

ገንዘብ በሥራ ይገኛል፤ የፈረሰ ቤት በኅብረት ዳግም ይገነባል፤ የተቃጠለውም ይተካል። በማኅበረሰብ የሚደርሰው ሥነ-ልቦና በጊዜ ሒደት ያገግማል። በአንጻሩ መተኪያ የሌለው ግን አንድ ነገር አለ፤ የሰው ልጅ ሕይወት። ኢትዮጵያ በዚህ ጦርነት በገንዘብ ሊተካ የሚችል ንብረትን ከማጣቷ በላይ በርካታ ዜጎቿን ተነጥቃለች። ሳይሰስቱ ሕይወታቸውን ለአገር የከፈሉ ሰማዕት ሊባሉ የተገባ ልጆች እንዳሏት ዐይታለች።

በዚህ መካከል ጦርነት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ንጹኃን ዜጎችም ለአገር የመጣ ዱላ በላያቸው ላይ አርፎ ተሰዉተዋል። ልጆችና ሕፃናት በማያውቁት ተቃጥለዋል። ከቤተሰብ አባላት ብዙዎች አልቀዋል፡፡ የት ነሽ? የት ነህ? ሳይባባሉም የተጠፋፉና በሕይወት ይኑሩ አይኑሩ የማያውቁ ጥቂቶች አይደሉም።

ወደፊት ከጦርነቱ ማብቃትና ከነገሮች መስተካከል በኋላ ልንሠማቸው ከምንችል እጅግ በርካታ አሳዛኝ ታሪኮች መካከል አንዱን ልንነግራችሁ ነው። ታሪኩ ከአጣዬ ኻያ ኪሎሜትር አካባቢ ገባ ብላ በምትገኝ መሃል ወንዝ በምትባል የገጠር ቀበሌ ኅዳር 7 ቀን 2014 ለኅዳር 8 አጥቢያ የተከሠተ ነው። ባለታሪኩ እና ብዙ የቤተሰባቸውን አባል የተነጠቁት ሙላቱ በየነ ሐዘናቸውን ዋጥ አድርገው በእርሳቸውና በቤተሰባቸው የደረሰውን ነግረውናል። አዲስ ማለዳ ከእኚህ ባለታሪክ ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች።

በጊዜው የነበረውን ኹኔታ እንዴት ያስታውሱታል?
እነሱ (በአሸባሪነት የተፈረጀው ህወሓት ቡድን) ወደ እኛ ሲገቡ ለስለስ ብለው ነበር ሲቀርቡን የነበረው። ሲገቡ አይዟችሁ አንነካችሁም ብለውን ነው የገቡት። እኔን ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ይዘውኝ ነበር፤ መታወቂያ አግኝተውብኝ ነው። መታወቂያው አንዱ የሥራ ቦታ ነው፤ ሌላው ደግሞ የነዋሪነት ነበር።

ኹለቱን ሲመለከቱ፣ ‹አንተ ተላላኪ ነህ› ብለው አቆዩኝ። ከዛ 12፡30 ሲሆን ለቀቁኝና ቤትህን ዐሳይ ብለውኝ ወደ ቤት ወሰዱኝ። ቤቴን ሳሳያቸው ቤተሰቦችህ የት ሔደው ነው አሉኝ። እኔም ፈርተው ወደ ጫካ ሔደዋል አልኳቸው። አሁኑኑ ቤተሰቦችህን አምጣቸው አሉኝ። ‹ሰው ይገድላሉ የሚባለው የውሸት ወሬ ነውና ሔደህ አምጣቸው!› ሲሉኝ አመጣኋቸው።

ግቢ ውስጥ ሦስት ቤት ነው ያለን። በዛም 18 ነበርን፣ አባትና እናቴን ጨምሮ ወንድሞቼና የወንድሜ ልጆች፣ የእኔም ልጆች አሉ። ታድያ አጥራችን በእንጨት የተሠራ ነው። ምሽግ የሠሩት እኛው ጊቢ ጋር ነበር። 8 ኩንታል የሚጠጋ እህል ነበር፤ እሱንም አበላሹት። በመሣሪያ የነደደው እህል እጅግ ብዙ ነው። ደኅናውን በሬ መርጠው አረዱ። (ሲቃ ባዘለ ድምጽ) ቢያወሩትም ትርጉም የለውም! ቤተሰቦቼ ተርፈውልኝ ቢሆን ነበር ለእኔ የሚሻለኝ!

አንደኛውን የተመታውና ነገር ግን አሁን በሕይወት ያለውን ወንድሜን አንገላቱት። መሣሪያ አስረከብን ብለው። ወንድሜም መሣሪያውን ደብቆ ነበር፤ እንደውም አንተ ተዋግተኸናል እያሉ አውጥተው ሲያንገላቱት ነበር። ከዛም አንገላተው ሲለቁን የተረፍን መስሎን ነበር፤ ግን ልናጣ የማይገባውን ኹሉ አጣን። መቀመጫ ማረፊያችንን ኹሉ ነው ያጣነው።

ከዛ በኋላ ምንድን ነው የተፈጠረው?
ይህ ከሆነ በኋላ ነው ለኅዳር 8 አጥቢያ ሌሊት ማለትም ሊነጋ ሲል 11፡00 ሰዓት በላያችን ላይ ከባድ መሣሪያ ወደቀብን። አንዱ ቤቱ ላይ፣ ሌላው ከአጥር ውጪ ነበር ከባዱ መሣሪያ የወደቀው። መሣሪያው ምን እንደሆነም አላውቅም! ፍሙን ስላየሁት ነው። እና ቤቱ ላይ በወደቀው መሣሪያ ሦስቱም ቤት ፈረሰ፣ የአንደኛው ቤት ግማሽ ጎን ነው የተረፈው። ስድስት ሬሳ ከቤታችን ወጥቷል።

ቤት ውስጥ ከነበርነው መካከል ኹለቱ ደኅና ናቸው። አንደኛው እንደውም ሌሎችንም የቤተሰብ አባላት እያስታመመ ነው። ሌሎቹ የተጎዱት እንጀራ መጉረስ እንኳ አይችሉም እንጂ ተርፈዋል። ከዚህ በኋላ ከሞት ባይተርፉ እንኳ አሁን ለመቅበርም ሰው አይጠፋም።
ያኔ ስድስት ሬሳ ኹለት ሆነን ነው ያወጣነው፤ ደም እየተንጠፈጠፈ አዝለን ነው ያወጣናቸው። በደኅና የተረፍነው እኔና እናቴ ነን። እናቴ አባቴን (የአባቴን አስክሬን) ለማውጣት አገዘችኝ። ያንን ስታይ እሷም ራሷን ሥታ ወደቀች። ከዛም የእኔ ሦስት ልጆች ነበሩ፣ አንዷ ልጄ ደክማለች፤ ቅጠል ሸፍኛት ሔድኩኝ። ኹለቱን ልጆቼን ከዛ አወጣሁ። ስመለስ ኹለት የአክስቴ ልጆች ነበሩ አንደኛዋ ተርፋለች። አባቴን፣ ወንድሞቼን፣ የወንድሜን ልጅ አጥቻለሁ።

እያዘንኩ ወደ ቤተክርስትያን ወሰድኳቸው፤ ሰውም የለም ነበር። አሁን አንዷ ሕፃን ልጄ በጣም ደክማለች። የቆሰሉት ቤት ናቸው አሁንም። አምቡላንስ መጥቶ ወስዷቸው ነበር። ሲታዩ ብረት ስላለባቸው ምንም መፍትሔ አልተገኘም። የግል ሐኪሞች የሸሹ ስለነበሩ በያሉበት እየተፈለጉ እንዲያግዙን እየተደረገ ነበር።

እንዳሉን እህልም ተቃጥሏል፤ እና አሁን ምን እየበላችሁ ነው?
ያው የተዘራ እህል ነበረ የተረፈ፣ እሷ ታጨደች። እሷን አሽተን እየበላን ነው። አሁን የዕለት ምግባችን ያ ነው። አንዳንድ ጎረቤት ደግሞ የተጋገረ ደረቅ እንጀራ ያመጣልናል። ቤታችን ስለፈረሰ ድልድይ ሥር ነበር ያለነው፤ አስፋልት ላይ ማለት ነው። ከመሃል ሜዳ ወደ ደብረብርሃን መሄጃ መንገድ መገናኛ ላይ አንድ ሰፋ ያለ ድልድይ ነበር፣ እዛ ነበርን። ስንረጋጋ በ6ኛው ቀን ነው ከዛ የወጣነው። ያኔ ጎረቤት እያመጣ ያበላናል።
ሰዉም ቢሆን የሚበላ ነገር አሳጥቶን አያውቅም። ከተረጋገጠው እህል ውጪ ራቅ ያለ ቦታ ያለው ደኅና የሆነውና ያልተረጋገጠው እህል እየታጨደ ነው፤ እሷን እያሸን እየበላን ነው።

ምን መልዕክት ማስተላለፍ ይፈልጋሉ?
አሁን አለቀ! ጫፉ ላይ ደረስን! ከዚህ በኋላ ተገላግለናል። በቅድሚያ ሲጀመር ነበር፤ ኦነግ ሸኔ ትጥቅ ይፍታ ሲባል፣ ኦነግ ሸኔ ፈትቶ ገብቶ ቢሆን፣ ጁንታ ያኔ ሽምግልና ሲላክበት ወይ ሽምግልናውን መቀበል ነበረበት አልያም መንግሥት አንድ ዕርምጃ መውሰድ ነበረበት። አሁንም ቢሆን አለቀ፣ ወይም ፈርተው ሔዱ ወይም አመለጡ ወይም ገቡ ወደገራቸው ብሎ መተው ሳይሆን፣ ዳር ላይ የደረሰውን መቋጨት አለበት። እነርሱ ለእኛ መርዝ ናቸው። እስከመቼም አይተዉንም። ለእኛ መርዝ ናቸው። ሕዝብ መግዛትን ቢፈልጉና የአገር ፍቅር ቢኖራቸው የሰው ሕይወት እንዲህ መደረግ የለበትም ነበር፣ ንብረት ላይ እንዲህ ማድረግ የለባቸውም ነበር።

እናም አሁን መንግሥት ጫፍ ላይ መድረስ አለበት፤ በትክክል ዕርምጃ መውሰድ አለበት። እኔ አሁንም ቢሆን ማጣት የማይገባውን ነው ያጣሁት። አሁንም ቁስሌ ቁስሌ ነው። እኔ ከዚህ በኋላ ምንም ነገር የለኝም፤ ወደ ግንባርም ውትድርናም ባለበት ቦታ ብሰለፍ ደስተኛ ነኝ። ማጣት የማይገባኝም ያጣሁት በእነርሱ ምክንያት ነው። ከዚህ በኋላ ምንም አማራጭም የለኝም።


ቅጽ 4 ቁጥር 163 ታኅሣሥ 9 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!