የእለት ዜና

ሕገ-ወጥ የዱር እንስሳት ንግድ በድንበር አካባቢዎች እየጨመረ ነው ተባለ

ኢትዮጵያ ሕገ-ወጥ የዓለም አቀፍ የዱር እንስሳት ንግድ መተላለፊያ መስመር (ኮሪደር) እየሆነች መምጣቷ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑ ተገለጸ።
በኢትዮጵያ የድንበር አካባቢዎች፣ በተለይም የሱማሌ ክልል ቶጎ ውጫሌ፣ ከፍተኛ ሕገ-ወጥ የዱር እንስሳት ንግድ መናኽሪያ እየሆነ መምጣቱን በዘርፉ ጥናት የደረጉ ባለሙያዎች እየገለጹ ነው። የዱር እንስሳት ሕገ-ወጥ ንግዱ ሰንሠለት፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ አፍሪካ አገራት ድረስ የተዘረጋ እንደሆነ በዘርፉ ጥናት ያካሄዱት መስፍን ወ/ሰማያት (ዶ/ር) ይናገራሉ።

ለዱር እንስሳት የተለየ ትኩረት ሠጥታ ከምትሠራው ኬንያ ጨምሮ፣ ከተለያዩ አገራት የሚመጡ የዱር እንስሳት፣ አዕዋፋት፣ የዝሆን ጥርስ እና የተለያዩ እንስሳት ቆዳዎች በሕገ-ወጥ መንገድ ለገበያ እንደሚቀርቡ መስፍን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
እንስሳቶቹ፣ በተለይም የአቦሸማኔ ግልገሎች፣ ምቹ ባልሆነ መልኩ በሕገ-ወጥ መንገድ በባህር ተጉዘው ወደ የመን፣ ከዚያም ወደ ተለያዩ አገራት ይወሰዳሉ። በዚህ የባህር ጉዞ በሕገ-ወጥ መንገድ ከሚዘዋወሩት ከ4ቱ እንስሳት አንዱ ብቻ ወደ ታለመለት ቦታ እንደሚደርስ የዱር እንስሳት ክብካቤ ባለሙያው መስፍን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የዱር እንስሳትን ለቤት ውስጥ አገልግሎት ማዋል በዓለም አቀፍ ሕጎች ጭምር የተከለከለ ሲሆን፣ ከ1975 ጀምሮ ዓለም አቀፍ የአቦሸማኔ ንግድ ታግዷል። ነገር ግን፣ ከ2010 እስከ 2019 ከሦስት ሺሕ 600 በላይ በሕይወት ያሉ አቦሸማኔዎች በሕገ ወጥ መንገድ የተሸጡ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ 10 በመቶው ብቻ ናቸው በሕግ አስከባሪዎች ቁጥጥር ሥር መዋል የቻሉ።

የዓለም እንስሳት ጥበቃ (ዎርልድ አኒማል ፕሮቴክሽን) የተሰኘ ድርጅት በጥናት ደረስኩበት ባለው መደምደሚያ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሕገ-ወጥ የዱር አንስሳት ንግድ እንዲያሻቅብ የአንበሳውን ሚና እየተጫወተ እንደሆነ ጠቁሟል።
ድርጅቱ በሪፖርቱ፣ መነሻቸውን መካከለኛው እና ምዕራብ አፍሪካ ያደረጉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አጥቢ እና ተሳቢ የዱር እንስሳት፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጓጉዘውና መዳረሻቸውን ወደ ተለያዩ አገሮች፣ በተለይም ወደ መካከለኛው ምስራቅ፣ አድርገው ለቤት እንስሳነት እየዋሉ ነው ሲል ያትታል።

ድርጅቱ ባስነበበው ሪፖርት እንደገለጸው ከሆነ፣ ከመካከለኛው ምስራቅ አገሮች በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዱር እንስሳቱን ወደ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ታይላንድ፣ ሆንግ ኮንግ፣ ኦማን፣ ማሌዥያ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን እና ዩናይትድ ኪንግደም እንደሚያጓጉዝ ለማወቅ ተችሏል።

በድርጅቱ ጥናት መሠረት፣ ብዙ ጊዜ በአየር መንገዱ ከተጓጓዙ የዱር እንስሳት መካከል እንሽላሊት፣ ኤሊ፣ የእባብ እና የጊንጥ ዝርያዎች ተጠቃሾች ናቸው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ፣ “እንደ ዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር(አያታ) አባልነቴ፣ በሕይወት ያሉ እንስሳትን የማጓጉዘው የእንስሳቱን ደኅንነት በጠበቀ እና ሕጋዊ በሆነ መልኩ ነው” ሲል የቀረበበትን ክስ በይፋዊ ገጹ አስተባብሏል።
በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ባለሥልጣን፣ የሕገ-ወጥ እንስሳት ዝውውር ዳይሬክቶሬት ዘርፍ ባልደረባ፣ በአየር መንገዱ ላይ የተሠነዘረው ክስ ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ይህ ተቋም ደረስኩበት ብሎ የሠነዘረው ውንጀላ፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ ከተከፈተው የምዕራባውያን የሥም ማጥፋት ዘመቻ እንዱ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

አማኑኤል ተፈራ የቶጎ ውጫሌ ነዋሪ ሲሆኑ፣ “በአካባቢያችን የሚኖሩ የጉምሩክ አባላት ጉቦ ተቀብለው የዱር እንስሳቱ ወደ ሱማሌ ላንድ በሕገ-ወጥ መንገድ እንዲወጡ ያግዛሉ” ሲሉ ዕማኝነታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል::
አያይዘውም፣ በየወሩ ቢያንስ አራት አቦሸማኔዎች ወደ ዐረብ አገሮች ከኢትዮጵያ ተነስተው በሱማሌ ላንድ በኩል አድርገው በኮንትሮባንድ ይወጣሉ ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

በሳዑዲ ዐረቢያና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የዱር እንስሳት ገበያው ደርቷል። በተለይ ቱጃር አረቦች የዱር እንስሳትን ልክ እንደ ቤት እንስሳት የማርባት ልማዳቸው ጨምሯል የሚሉት፣ በዱር እንስሳት ክብካቤ ጥበቃ ላይ የተሠማሩና አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ባለሙያ ናቸው። እንደባለሙያው አባባል በአሁኑ ወቅት “አንድ አቦሸማኔ እስከ 10 ሺሕ ዶላር” ድረስ በመካከለኛው ምሥራቅ ባሉ የአረብ አገራት ይሸጣል።

ባለሙያው አያይዘውም፣ “የአቦሸማኔ ግልገሎቹን ይዘው ለሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች የሚያቀርቡት በአብዛኛው ኢትዮጵያዊያን ናቸው ያሉ ሲሆን፣ በአንድ ግልገልም ከ 10-15 ሺሕ የኢትዮጵያ ብር እንደሚከፈላቸው” ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
ነጁ ጃሚ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሱማሌ ላንድ ዜጋ ስትሆን፣ በዱር አራዊት ክብካቤ እና ጥበቃ ሥራ ላይ የተሠማራች ናት። ይች ወጣት የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል፣ አቦሸማኔን በመውሰድ ወደዐረብ አገራት ለሚያሻግሩ ሕገ-ወጦች ዋነኛ መስመር መሆኑን ትገልጻለች።
በአለም ላይ 7 ሺሕ 100 አቦሸማኔዎች ብቻ በዱር እንደሚገኙ የሚጠቅሰው የዓለም እንስሳት ጥበቃ (ዎርልድ አኒማል ፕሮቴክሽን) ድርጅት ዘገባ፣ ከነዚህም 90 በመቶ የሚሆኑት በአፍሪካ ውስጥ እንደሚገኙ ያትታል።


ቅጽ 4 ቁጥር 163 ታኅሣሥ 9 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!