የእለት ዜና

ዓባይ ኢንሹራንስ የተከፈለ ካፒታሉን ከ300 ወደ 500 ሚሊዮን ብር ሊያሳድግ ነው

ዓባይ ኢንሹራንስ ኩባንያ አሁን ያለውን 300 ሚሊዮን ብር የተከፈለ የካፒታል መጠን በሚመጡት ኹለት ዓመታት ወደ 500 ሚሊዮን ብር እንደሚያሳድግ ገለጸ።
ዓባይ ኢንሹራንስ ኩባንያ አ.ማ. ባሳለፍነው ታኅሳስ 2/2014 ባደረገው 11ኛ መደበኛና ድንገተኛ የባለአክሲዮኖች ስብሰባ፣ በቀጣዮቹ ኹለት ዓመታት ውስጥ ካፒታሉን እንደሚያሳድግ ገልጾ በጠቅላላ ጉባኤው ማጽደቁን አዲስ ማለዳ መረዳት ችላለች።
ኢንሹራንሱ በመጭዎቹ ኹለት ዓመታት 300 ሚሊዮን ብር ካፒታል ወደ 500 ሚሊዮን ብር ለማሳደግ ያቀረበው ሐሳብ በጠቅላላ ጉባኤው እንደጸደቀ የዓባይ ኢንሹራንስ የማርኬቲንግና ኮርፖሬት ፕላኒንግ መምሪያ ኃላፊ ቢኒያም አየለ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የኢንሹራንሱን የካፒታል ዕድገት ዕቅድ ስምምነት ለመድረስ የተቻለው፣ ኢንሹራንሱ ያለውን ገቢ ከፍ በማድረግ ከሌሎች አክሲዮን ማኅበሮች በተሸለ በገበያው ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማድረግ ታልሞ መሆኑንም ኃላፊው አብራርተዋል።

በመጭዎቹ ኹለት ዓመታት ውስጥ 300 ሚሊዮን ብር ካፒታሉን ወደ ግማሽ ሚሊዮን ብር ለማሳደግ ያቀደው ዓባይ ኢንሹራንስ ኩባንያ አ.ማ፣ በ2014 በጀት ዓመት ማጠቃለያ 387.44 ሚሊዮን ብር የተጣራ ሀብት እንዳስመዘገበ እና 663.5 ሚሊዮን ብር ደግሞ የኩባንያው የተመዘገበ አጠቃላይ ዕዳ መሆኑ ተመላክቷል።

ኢንሹራንሱ በበጀት ዓመቱ ከተመዘገበው የአረቦን መጠን 362 ሚሊዮን ብር ወይም 2.6 በመቶ የሚሆነውን የገበያ ድረሻ መያዙ የተመላከተ ሲሆን፣ ይህም ከባለፈው 2013 ከተመዘገበው 270 ሚሊዮን ብር ወይም 2.4 በመቶ የገበያ ድርሻ ጋር ሲነጻጸር የ34 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ ችሏል ነው የተባለው።

ይህ የዕድገት ለውጥ መታየትም በቀጣዮቹ ዓመታት ካፒታሉን የማሳደግ ውሳኔውን እውን ለማድረግ የሚያስችል ማሳያ በመሆኑ ነው ጠቅላላ ጉባኤው ዕቅዱን ያጸደቀው ተብሏል።

ምንም እንኳ በውጭ ምንዛሬ ዕጥረት፣ በፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የኮቪድ ሥርጭት እንዲሁም የዋጋ ግሽበት ኢንሹራንሱን በፈለገው ልክ እንይጓዝ መሰናክል ቢሆኑትም፣ በቀጣዮቹ ኹለት ዓመታት ያቀደውን የካፒታል መጠን መጨመር ዕውን ለማድረግ የሚያስችሉት መንገዶች አሉ ተብሏል።

ከእነዚህም መካከል በአገሪቱ ውስጥ የሚስፋፋው የውጭ ኢንቨስትመንት፣ የሕብረተሰቡ የመድኅን ዋስትና ግንዛቤ መጨመር፣ የከተሞች መስፋፋት ብሎም ሌሎች ምክንያቶች ካፒታሉን ለማሳደግ በር ከፋቺ እንደሆኑ ነው የተገለጸው።
በ2014 በጀት ዓመት ኢንሹራንሱ 13.9 ቢሊዮን የአረቦን ገቢ በማስመዝገብ 24.8 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት ያሳየ ሲሆን፣ ለዚህ ገቢም የኢትዮጵያ መድኅን ድርጅት 43.8 በመቶ የሚሆነውን ከፍ ያለ ድርሻ መያዙን ነው መረዳት የተቻለው።

ኢንሹራንሱ በበጀት ዓመቱ ካገኘው አጠቃላይ የአረቦን ገቢ መካከል ከተሸከርካሪ መድኅን ዋስትና 44 በመቶ፣ ገንዘብ ነክ ከሆነው መድኅን ዋስትና 23.8 በመቶ፣ እንዲሁም ከኢንጅነሪንግ 12 በመቶ የያዙ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ላለፉት ዐስር ዓመታት በአማካይ 35.1 በመቶ የአረቦን ዕድገት አስመዝግቧል።

በኩባንያው በ2020/21 በጀት ዓመት፣ 350 ሚሊዮን 153 ሺሕ 890 ብር ከጠቅላላ መድኅን ድርሻ የተገኘ ሲሆን፣ ቀሪው 11 ሚሊዮን 867 ሺሕ 115 ብር ከሕይወት መድን ድርጅት የተገኘ መሆኑ ታውቋል።
ይህ አፈጻጸምም ከዕቅዱ 325 ሚሊዮን 543 ሺሕ 289 ብር ጋር ሲነጻጸር 14 በመቶ ብልጫ እንዳሳየና ይህም ከባለፈው ተመሳሳይ ዓመት 270 ሚሊዮን 546 ሺሕ 775 ብር ጋር ሲነጻጸር 33.8 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ነው መረዳት የተቻለው።

ዓባይ ኢንሹራንስ በ2020/21 የበጀት ዓመት አጠቃላይ የመድኅን ድርጅት ብቻ ከታክስ በፊት 75 ሚሊዮን 564 ሺሕ 130 ብር ማስመዝገቡ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት 68 ሚሊዮን 175 ሺሕ 884 ብር ጋር ሲነጻጸር 10.8 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ተብሏል።

በበጀት ዓመቱ እስከ ሰኔ 30/2014 በአጠቃላይ 280 ሚሊዮን 512 ሺሕ ብር ሲሆን፣ ከባለፈው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነጻጸር 19.7 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተመላክቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 163 ታኅሣሥ 9 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!