ብሔር እሰከ መቃብር!

0
800

የብሔር እኩልነት ጥያቄ ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ተፈቷል መባሉን የማይቀበሉት ይነገር ጌታቸው፥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብሔርተኝነት የአገር ኅልውናን አደጋ ላይ መጣሉን በማስረጃነት ይጠቅሳሉ። ለዚህም ሕገ መንግሥቱ ከአገራዊ ማንነት ይልቅ ለብሔር ማንነት የሚያደላ በመሆኑ አንድ የፖለቲካ ምጣኔ ሀብታዊ ማኅበረሰብ የመፍጠር ግብን ሩቅ አድርጎታል የሚሉት ይናገር፥ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት የፖለቲካ ምስቅልቅል መፍትሔው ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል እና ፌደራሊዝሙን ላላ ማድረግ ነው ሲሉ መከራከሪያ ሐሳብ አቅርበዋል።

ሄንግልስ የተባለው ፈላስፋ አገራት ያለፉባቸው አሰቃቂ ጦርነቶች መሰረታዊ መነሻቸው ሀብትና ነዋይ ሳይሆን የሕዝቦች ዕውቅናን መሻት ነው ይላል። በርግጥም ከፈረንሳይ አብዮት እስከ ዓረቡ ዓለም ነውጥ ያለውን እውነት ልብ ብሎ ለተመለከተ ሰው ትግሉ በማንነት ላይ ተንጠልጥሏል። መፍትሔውም ለቡድኖች ተገቢ ክብርን (dignity) መስጠት በሚል ሐረግ ተተብትቧል። ይሁን እንጅ እንዲህ ያለው መፍትሔ የሰመመን መርፌ እንጅ ዘላቂ ሊሆን አልቻለም። ሩቅ መሔድ አያስፈልግም። የቡድን መብቶችን ያለቅጥ ለግሷል ተብሎ የሚተቸው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ዛሬ ላይ አጣብቂኝ ውስጥ የገባው የቡድን መብታችንን ተነጥቀናል በሚሉ ወገኖች ነው።
አማራም ሆነ ወላይታ፣ ሀድያም ሆነ ከምባታ የሚያነሱት ጥያቄ ለማንነታቸው ምርኮኛ ከሆነ ውሎ አድሯል። ጥያቄያችንም ከዚህ ተቃርኖ ይቀዳል። ለብሔሮች የተጋነነ መብት ሰጥቷል የሚባለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት “ለምን ብሔርተኝነትን ማሸነፍ ተሳነው? የብሔሮችን መብት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መልሻለሁ ካለስ ጉዳዩ ለምን እየከሰመ አልሔደም?”

ውሃ ልክ የሌለው የማንነት ፖለቲካ
የማንነት ትርክት ኹለት መልኮች ያሉት ነው። አንድም ከግለሰባዊ ፍላጎት ይቀዳል አንድም ከማኅበረሰባዊ አምሮት ይወለዳል። እነዚህ ኹለት ጉዳዮች ሲያሻቸው ይጠፋፋሉ፤ ደስ ሲላቸው ይደጋገፋሉ። ግለሰቦች ለወጡበት ማኅበረሰብ ባሪያ መሆናቸው አንገብግቧቸው ያምፃሉ። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ለኖሩበት ሕዝብ ጠበቃ ሆነው ትግል ያካሒዳሉ። ተቃርኖ የወለደው የማንነት ትርክት ቡድናዊ መልክን ሲላበስ ፖለቲካን ይከናነባል። እኛ እና እነሱ ማለት ይጀምራል።

ታዋቂው የፖለቲካ ታሪክ ተመራማሪ ፍራንሲስ ፉክያማ በ2018 ለንባብ ባበቃው “IDENTITY” በተሰኘ መጽሐፉ የማንነት ፖለቲካን ሥነ ሕይወታዊ መልክ ያስይዘዋል። በዚህ ዙሪያ የሚደረገው ትግልም አንድ አይደለም ይላል። የፉክያማ ሙግት megalothmia እና isothymia የሚሉ ቃላትን ተንተርሷል። megalothmia እኔ ከሌላው የተሻልኩ ስለሆንኩ ከፍ ያለ ቦታ ይገባኛል የሚል ጥያቄን ያዘለ ነው። ከዚህ በተቃራኒው isothmia የእኔ ማንነት ከሌላው ያነሰ አይደለም ለሚል የእኩልነት አስተሳስብ ያደላል። ታዋቂው የፖለቲካ ታሪክ ተመራማሪ ፍራንሲስ ፉክያማ በዛሬዋ ዓለም በብሔር ማንነት ዙሪያ የሚደረጉ ትግሎች ከኹለቱ ባንዱ የሚሰፈሩ ናቸው ይላል። ከፊሉ ብሔር ከህዳጣን ጋር መመደቡ ያንገበግበዋል። ሌላው ጎራ ለእኩልነት ይዳክራል።

ይህ እውነት አሁናዊ ብቻ አይደለም። ፕሉቶ “The Republic” በተሰኘ ድርሳኑ መምህሩ ሶቅራጥስ ከአቴንስ ባላባቶች ጋር በነበረው ውይይት ሰለሰው ልጆች እኩልነት ይሰብክ እንደነበር ያወሳል። የግሪክ ባላባቶች አረዳድ ግን ከዚህ በተቃራኒው ነበር። የእነሱ ትግል ከሌላው ጋር እኩል ግሪካዊ ከመባል መሻት የተጠናወተው ነው። ሶቅራጥስ እኩልነትና የሰው ልጅ ክብርን መሻት ተፈጥሯዊ መሆኑን ሲሰብክ ባላባታዊ አስተዳደሩ ከዚህ በተቃራኒው ቆሞ ለፍፏል። ይህ ደግሞ ከላይ የተመለከትናቸውን ቃላት እስከ መፍጠር አድርሷል። የዓለም የፍልስፍና ጅረት ነፃነት፣ እኩልነትና ፍትሕ በሚሉ ቃላት እየተመራ ሰፊ ተዋስዖ ተደርጎበታል።

የፈረንሳያዊው ፈላስፋ ሩሶ አቀራረብ ግን በታለመለት መንገድ ብቻ የሚሔድ አልነበረም። ሩሶ “Discourse on the origins of Inequality” በተሰኘ ሥራው ሕዝብ ለምን ደስታን ያጣል ሲል ይጠይቃል። ከዛም በጋርዮሽ ስርዓት ውስጥ የነበረ ማኅበረሰብ መበደልን የወል ያደረገ አልነበር ይላል። እንዲህ ያለው የወል ደስታ ማጣትና እንደ ማኅበረሰብ ተበደልኩ ማለትም በጊዜ ሒደት የተፈጠረ መሆኑን ያወሳል። “እኩልነትና የወል ደስታ ተፈጥሯዊ ነው? ሰው ሰራሽ?” የሚለው ሙግት እልባት ባያገኝም የዴሞክራሲ ማዕዘን ለመሆን ግን አላረፈድም።

የዓለምን ታሪክ የቀየረው የፈረንሳይ አብዮት አዕማዶች የወል ደስታ ሌላኛው ገፅታ የሚባሉት እኩልነት፣ ወንድማማችነትና ነፃነት ናቸው። የፓሪስ ፖለቲካን የናጡት ጭሰኞች የሰው ልጆች በተፍጥሯቸው ነፃና እኩል ናቸው የሚለውን ትርክት ልዕልና እንዲኖረው አድርገዋል። ሕዝባዊ ተበዳይነትንም ለመገርሰስ ጥረዋል። ሰብዓዊ ፍጡራን ሁሉ የተከበሩ ናቸው የሚለውንም አውጀዋል። ይህ አዋጅ በዘመናዊው ዓለም ዴሞክራሲ ውስጥ መሰረታዊ መርህ ተደርጎ መወሰድ የጀመረውም ከዚህ በኋላ ነው።

ፉክያማ የጀርመን፣ የጣሊያን፣ የጃፓን፣ የአየርላንድ፣ የእስራኤል እና የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥታትን ዋቢ በማድረግ የሰው ልጆች ክብር የሕገ መንግሥታቸው መሰረታዊ መርህ እንደሆነ ያሰርዳል። በ1949 የጸደቀው የጀርመን ሕገ መንግሥት አንቀጽ 1(1) “የሰው ልጆች የማይሸራረፍ ክብር አላቸው” ይላል። ቁም ነገሩ ግን እኩልነትና ነፃነት ብሎም ክብር ሕገ መንግሥታዊ መሆናቸው ብቻ አይደለም። ዋናው ነገር “እኩልነት፣ ነፃነትና የሰው ልጆች ክብር በፖለቲካ ውስጥ እንዴት ይሰፍናሉ?” የሚለው ነው።

እኩልነትና ነፃነት በፖለቲካ ውስጥ በሕግ የበላይነትና በዴሞክራሲያዊ ተጠያቂነት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ሁሉም ሰው ተጠያቂ ብቻ ሳይሆን በሕግ ፊትም እኩል ነው። ይህ ግን በየአገራቱ የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ እኩል ተግባራዊ አይደረግም። አምባገነናዊ መንግሥታት ኹለቱን ጉዳዮች ይደፍቃሉ። ዴሞክራሲያዊ የሆነ ሕገ መንግሥት ያላቸው አገራት ለነፃነትና ለእኩልነት በሰጡት የተለጠጠ መብት ተመልሰው የወል ደስታን ይደፈጥጣሉ። ይህ ደግሞ ቁጥሩ ይለያይ እንጅ በየትኛውም አገር ፖለቲካ ውስጥ የእኩልነትና ነፃነት ጥያቄ መቼም እንዳይከስም አድርጎታል። ሕዝቦች በፖለቲካ ስርዓት ላይ ያላቸው ደስታም ምሉዕ እንዳይሆን ትልቅ ክፍተትን ፈጥሯል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክም በዚህ እውነት የተቀነበበ ነው። ያለፈውን መቶ ዓመታት ታሪክ ለተመለከተ ሰው ነፃናትና እኩልነት ከፍ ያለ ትኩረትን የሳቡ ጉዳዮች ነበሩ። የምጣኔ ሀብትም ሆነ የብሔር እኩልነት ጥያቄን ያነሱ ወገኖች ነፍጥ አንግበው በተለያዩ ወቅቶች ታግለዋል። ቡትቶ የለበሰው ተራ ወታደር ሕይወት አሳስቧቸው መፈንቅለ መንግሥት ካደረጉት መንግሥቱና ግርማሜ ነዋይ አንስቶ የብሔር ጭቆና አስጨንቋቸው ደደቢት እስከ ወረዱት ሰባት ወጣቶች ድረስ እኩልነት አጀንዳ ሆኖ ዘልቋል። በኋላም ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ነገሩን ለመፍታት ተሞክሯል። ኢትዮጵያ እንደ ጀርመን የሰው ልጅችን ክብር የሕገ መንግሥቷ መርሆ ባታደርግም እኩልነትና ነፃነትን ፈቀድኩ ካለች ኹለት ዐሥርታትን ተሻግራለች። ይሁን እንጂ የእኩልነት ጥያቄው ዛሬም ከሰገነት ላይ አልወረደም። የብሔሮች ጉዳይ የማያዳግም ምላሽ ተሰጠው ቢባልም ብሔርተኝነቱ አልረገበም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያለውን ለተመለከተ ሰውም ብሔርተኝነት እንደ አብዮት ስርዓቱን መናጥ ጀምሯል።

እኩልነትን እየናፈቁ እኩልነትን መግፋት!
የኢትዮጵያ ፖለቲካ የዓለም ፖለቲካ አካል እንደ መሆኑ መጠን ወቅታዊና ሁለንተናዊ ጉዳዮች የተጫኑት መሆኑ አያጠያይቅም። ይህ ማለት ግን የአገራችን ነባራዊ ችግር ከውጭ ወደ ውስጥ የሚፈስ ብቻ ነው ማለት አይደለም። ዘመናትን ስላስቆጠረው የሕዝቦች የእኩልነትና ነፃነት ትግል ስናወራም ከዚህ እውነት አናመልጥም። ኢሕአዴግ መራሹ ኀይል ሥልጣኑን ከተቆናጠጠ በኋላ ለእኩልነትና ነፃነት መራር ትግል አደረኩ ቢልም ምሉዕ ድልን ግን ማስመዝገብ አልቻለም።ለዚህ አራት ጉዳዮችን መነሻ ማድረግ የሚቻል ይመስለኛል።

የመጀመሪያው ከኢትዮጵያ የፖለቲካዊ ስሪት ይመነጫል። በአሁኑ ወቅት ያለው የብሔሮች እኩልነት ትግል አንድም “እኔ ከሌላው ጋር መስተካከል አለብኝ” በሚል የሚቃኝ ሲሆን አንድም “የለም ከህዳጣን ጋር አልጨፈለቅም” በሚል አመለካከት የተገራ ነው። ይህ አስተሳሰብ ሶቅራጠስ አንስቶት ፉክያማ ከዛሬ ዘመን ጋር ካዋደዳቸው megalothmia እና isothmia ጽንሰ ሐሳቦች ጋር ይተሳሰራል። በዛሬው የአገራችን ፖለቲካ ውስጥ በርካታ የዳር አገር ብሔር ብሔረሰቦች ቢያንስ እንደ መሐል አገሩ ሕዝብ እኩል መሆን አለብን ብለው መታገላቸው የማይታበይ ሀቅ ነው። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ እኔ ትልቅ ሕዝብ ነበርኩ ከሌሎች ጋር እኩል አልጨፈለቅም፤ እንደውም አሁን የተሰጠኝ ቦታ በራሱ ተገቢ አይደለም የሚል ቡድን መኖሩ አያጠያይቅም። ወቅታዊው የደቡብ ክልል ፖለቲካ ለዚህ ማሳያ የሚሆን ይመስለኛል። ክልል የመሆን ጥያቄን ያነሱ በርካታ ብሔሮች ከምጣኔ ሀብታዊ ተጠቃሚነት ይልቅ በመልክዓ ምድር ከሌሎች አናሳ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር መካለላቸውን እንደ ስህተት ይጠቅሳሉ።

ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ የቀረው የደቡብ ሕዝብ ቢያንስ እንደ ሲዳማ፣ ወላይታ፣ ሀድያ፣ ከፋ…… እኩል መሆን አለብኝ ብሎ ይጠይቃል። እዚህ ላይ አንድ ቁም ነገር ማንሳቱ ተገቢ ይመስለኛል። እንደ ሌላው ልሁን ማለትም ሆነ ከሌላው እልቃለሁ ብሎ ማሰብ ተገቢ እውቅና አልተሰጠኝም ከሚል የፖለቲካ ሐቲት የሚመነጭ ነው። ይህ ደግሞ የብሔር ጥያቄን ሲላበስ ብሔርተኝነት መውለዱ አያጠያይቅም። ከዚህ አንጻር ዛሬ ላይ ያለው የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ አንዱ መነሻው ከሌላው እኩል መሆንን በመቀበልና ባለመቀበል መካከል የሚዋልል መሆኑን መገንዘብ ያሻል።

ኹለተኛው ነጥብ ከማንነት ፖለቲካ ተለዋዋጭነት ጋር የሚተሳሰር ነው። ማንነት አዕምሯዊ እንደመሆኑ መጠን እንደኩሬ ውሃ ረግቶ አይቀመጥም። ለአንድ ማኅበረስብ ትናንት የሞቀው ልማዱ ዛሬ ሊበርደው ይችላል። ከዚህ በፊት በደስታ የተቀበለው ነገር ነገ ለውድቀት ዳርጎኛል ያስብለው ይሆናል። ለእንዲህ ያለው ሐቲት አገራዊ ምሳሌን ለመጥቀስ አልደፍርም። ከዛ ይልቅ ጀርመናዊውን አክራሪ ብሔርተኛ ጸሐፊ ፓውል ዲ ላጋርድን አነሳለሁ። ላጋርድ የከተሞች መስፋፋት፣ የኢንዱስትሪዎች መብዛትና የሌላ አገራት ዜጎች መበራከት የጀርመናዊያንን መንፈስ አጥፍቶታል ብሎ ያምን ነበር። በመሆኑም ባሕላችንን ከመበስበስ መታደግ ካለብን የውጭ ዜጎችን ማስወገድ ያስፈልጋል እያለ ለፍፏል።

አገሬው መጀመሪያ ላይ ንግግሩን እብደት አደርጎ ቢወስደውም በጊዜ ሒደት ግን ለውድቀቱ ሁሉ መነሻ የጀርመን መንፈስ መላሸቅ መሆኑን ማመን ጀመረ፤ አይሁዶችንም ለዚህ ተጠያቂ አደረገ። የ‘አርያን’ ዘር ነኝ የሚል ጀርመናዊ ሁሉ ለሥራ አጥነቱም ሆነ ለፍቅር ሕይወቱ መበላሸት አይሁዶችን ተጠያቂ ማድረግ ያዘ። ሂትለርን አንግሶም በብሔርተኝነት ስካር አይሁዶችን ጨፈጨፈ። ፉክያማ እንዲህ ያለውን የብሔርተኝነት ሒደት የሥነ ልቦና መናወጥ ሲል ይጠራዋል። በርግጥም ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ ላይ የሚስተዋለው አክራሪ ብሔርተኝነት አንዱ መነሻው ሥነ ልቦናዊ ቀውስ የወለደው ነው።የጨቋኝና ተጨቋኝ፤ የገዥና ተገዥ፣ የበላይና የበታች ትርክት እስረኞች ሥነ ልቦናዊ መናጋት ውስጥ ተዘፍቀዋል። ለእነዚህ ወገኖች የውደቀታቸው ሁሉ መነሻ ከሌላ አከባቢ መጡ የሚሏቸው ሕዝቦች ናቸው። በዚህ የተነሳም ለማድረግ አይደለም ለማሰብ የሚከብዱ ጉዳዮችን ሲፈፅሙ ማየት ተለምዷዊ ሆኗል። ይህ ሥነ ልቦናዊ መረበሽ በዘመን ሒደት በፖለቲካዊ ስርዓት ለውጥ የሚጠገን አይመስልም። ይልቁኑ ዘመኑን እየዋጀ መልኩን እየቀያየረ እንደ ምዕራባዊያኑ የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ መቀጠሉ አይቀርም።

ድል የራቀው የኢትዮጵያዊያን የእኩልነትና የነፃነት ትግል ከላይ ባሉት ጉዳዮች ከውጩ ዓለም ጋር ተመሳሳይ ገፅታ ቢኖረውም የራሱ መልክ ያለው መሆኑ ግን አያከራክርም። ከዚህ አንጻር ኹለት ነገሮች የላቀ ሚና ነበራቸው። አንደኛው የብሔሮች ትግል ቅርፅ የያዘ አለመሆን ነው። ከመቶ ዓመት በፊት የነበረው የአውሮፓውያን የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ በውሉ የተመራና ፖለቲካዊ ቅርፅን የፈጠረ ነበር። የኢትዮጵያዊያኑ ግን በዚህ ሒደት አልተጓዘም። ዛሬ ላይ ያለው የብሔሮች ተገቢ ዕውቅናን የመፈለግ እንቅስቃሴ አውሮፓውያን ከመቶ ዓመት በፊት ካለፉበት ታሪክ ጋር ይመሳሰላል። የምዕራቡ ዓለም እንደኛ ካለው የብሔርተኝነት ትርምስ የወጣው ለየአካባቢዎቹ መንግሥታት የላቀ ነፃነትን በመስጠት ከዛ ከፍ ሲልም ኮንፌደሬሽናዊ አስተዳደርን እስከመፍቀድ በመድረስ ነበር። መድሃኔ ታደሰ (ፕሮፌሰር) በቅርቡ አንድ መድረክ ላይ ያቀረቡት አገራዊ ምክር ሐሳብም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነው። እንደ መድሃኔ ገለጻ በብሔርተኝነት ማዕበል የሚናጠው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሊረጋጋ የሚችለው ፌደራሊዝሙን ከዚህ በላይ በማላላትና ኮንፌዴራላዊ ስርዓትን እስከ መተካት በመድረስ ነው።

ይህ አገላለፅ ከዓመታት በፊት በአለን ሎቪስን ይቀርብ የነበረውን ትችት ትክክልነት የሚያረጋግጥ ይመስለኛል። ሎቪስ “Ethnic Federalism in Dominant party state: The Ethiopian Experience 1991-2000” በተሰኘ ጥናታቸው የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም መሰረታዊ ችግሩ በአውራ ፓርቲ የሚዘወር መሆኑ ነው ይላሉ። በዚህ የተነሳም ከፌደራል እስከ ቀበሌ ያለው አደረጃጀት በሥም ያልተማከለ ቢባልም የአሃዳዊነት ተቀጥያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ብሔር ብሔረሰቦችም ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት ናቸው ተብሎ ቢታወጅም በተግባር ግን እሱ አልታየም። ይህ ደግሞ የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በጥቂቶች መዳፍ እንዲወድቅ አድርጎታል። በእኔ ምልከታ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከዚህ ዓይነቱ የዕዝ አገዛዝ እንዲወጣ ከተፈለገ የካናዳን ፌደራሊዝም ሞዴል ሊከተል ይገባዋል። በካናዳ ለፌደራል መንግሥት ወንበር የሚወዳደር ፓርቲ ለክልል ሥልጣን አይፎካከርም። እንዲህ ያለው አካሔድ ደግሞ የክልሎችን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ከፍ ያለ ሚና ይጫወታል ።

ኢሕአዴግ መራሹ ኀይል የእኩልነትና የነፃነት ጉዳይን ለማስፈን የተቸገረው ከላይ ባነሳናቸው ፖለቲካዊ ነጥቦች ብቻ አይደለም። ገዥው ግንባር የአንበሳውን ድርሻ የተጫወተበት ሕገ መንግሥት የብሔርን ጉዳይ እንዳይከስም አድርጎ ማቅረቡም ሌላው መሰናክል ነበር። እንዲህ ያለው እውነት ደግሞ ብሔርና ብሔርተኝነት የትናንት ብቻ ሳይሆን የነገም ፖለቲካችን ስንቅ እንዲሆን ያደርገዋል። በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ከአገራዊ ማንነት ይልቅ ለብሔር ማንነት የሚያደላ ብቻ ሳይሆን መሰረታዊ መርሆውንም ብሔር ያደረገ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም። ይህ ደግሞ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን አንድ የፖለቲካ ምጣኔ ሀብታዊ ማኅበረሰብ የመፍጠር ግብ ሩቅ አድርጎታል። ዛሬ ላይ ያለውን የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ስንመለከትም ሕገ መንግሥቱ በራሱ ተጠልፎ ሊወድቅ እንደሚችል እንገነዘባለን። ከዚህ አንጻር አሁን ያለውን የፖለቲካ ምስቅልቅል ፈር በማስያዝ በኩል ፌደራሊዝሙን ላላ ከማድረግ ባልተናነሰ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ እንዳይከስም ተደርጎ የቀረበውን የብሔር ፖለቲካ ማስተካከል ያሻል።

ይነገር ጌታቸው በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን በማገልገል ላይ የሚገኙ ባለሙያ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው mar.getachew@gmail.com ሊገኘኙ ይችላሉ።

አዲስ ማለዳ ሐምሌ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here