የእለት ዜና

በአማራ ክልል የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ መገንቢያ ዕቅድ ለማዘጋጀት ጥናት እየተደረገ ነው

ክልሉ ለጦርነቱ ያዞረውን በጄት የፌዴራል መንግሥት እንዲተካ ዕቅድ ተይዟል

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት በአማራ ክልል የወረራቸውን አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል የመልሶ ግንባታ ዕቅድ ለማዘጋጀት ሙሉ ጥናት እየተካሄደ መሆኑ ተገለጸ።
መነሻውን ትግራይ ክልል ያደረገው የሰሜኑ ጦርነት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች መስፋፋቱን ተከትሎ፣ ህወሓት በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በሚገኙ የመንግሥትና ግለሰብ ንብረቶች ላይ ዘረፋ እና ውድመት ማድረሱ እስካሁን የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። መንግሥት በጀመረው የመልሶ ማጥቃት ህወሓት በወረራ ይዟቸው ከነበሩ አካባቢዎች ለቆ መውጣቱን መንግሥት አስታውቋል።

በዚህም ህወሓት በወረራ ለወራት ይዟቸው ከነበሩ የአማራ ክልል አካባቢዎችን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ፣ የክልሉ መንግሥት የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት የሚያስችል ዝርዝር ጥናት የሚያካሂድ ቡድን አቋቁሞ ወደ ሥራ ማስገባቱን በጥናት ቡድኑ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

የተጀመረውን ጥናት ውጤት መሠረት ያደረገ የመልሶ ግንባታ ዕቅድ ጥናቱ ከተጠናቀቀ በኋላ በአስቸኳይ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ እንደሚገባ ተጠቁሟል። በጥናቱ ላይ ተመስርቶ በሚዘጋጀው የመልሶ ግንባታ ዕቅድ ላይ የወደሙ ተቋማትን መልሶ በመገንባት ሒደቱ የሚኖሩትን ወጪዎች የፌዴራል መንግሥት እና የክልሉ መንግሥት የሚሸፍኗቸው እንደሚኖሩ አዲስ ማለዳ ሰምታለች።

በወረራ ተይዘው ከወደሙ አካባቢዎች ሥፋት አንጻር በመልሶ ግንባታ ሒደቱ የወደሙ የመንግሥት እና የግል ተቋማትን ወደ ነበሩበት ለመመለስ የሚያስፈልገው የገንዘብ እና የጊዜ መጠን ሠፊ ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ እየተገለጸ ነው። በዚህም የሚዘጋጀው የመልሶ ግንባታ ዕቅድ መሠረታዊ አገልግሎት ሠጭ ተቋማት በአስቸኳይ ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ የሚያደርግ እና በአጭር ጊዜ ሊገነቡ የማይችሉ ተቋማትን ደግሞ በሒደት መልሶ ለመገንባት የሚያስችል መሆኑ ተጠቁሟል።

ህወሓት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ወረራ መፈጸሙን ተከትሎ ወረራውን ለመመከት የክልሉ መንግሥት የክተት ጥሪ ማወጁ እና አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት ውጭ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሥራ እንዲያቆሙ በማደረግ የክልሉን በጄት ለጦተርነቱ ማዞሩን መግለጹ የሚታወስ ነው።

የክልሉ መንግሥት በወሰነው ውሳኔ መነሻነት መሠረታዊ አገልግሎት ሠጭ ተቋማት ከሚባሉት እንደ ፋይናንስ፣ መብራት፣ ውኃ እና መሰል አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ውጭ ያለው በጄት ለጦርነቱ ዘመቻ ዞሯል ተብሏል። በተጨማሪም ክልሉ በበጄት ዓመቱ የግድ አስፈላጊ ከሆኑ ስምሪቶች ውጭ የመስክ ስምሪትና አበል የሚከፈልባቸው ሥራዎችን እንዲታገዱ አድርጓል።

በዚህም የክልሉ መንግሥት በ2014 ለመደበኛ ወጪ የያዘውን በጀት ለጦርነቱ ማዋሉን ተከትሎ፣ ለጦርነቱ ያወጣውን ወጪ የፌዴራል መንግሥት የሚተካበት ሁኔታ ላይ ክልሉ እንደሚሠራ ተጠቁሟል። በክልሉ የወደሙ የመንግሥት ተቋማትን ወደ ሥራ ለማስገባት እና መልሶ ለመገንባት በጄት እንደሚያስፈልገውም ተገልጿል።

በጦርነቱ የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት መሠረታዊ አገልግሎት ሠጭ የመንግሥት ተቋማትን ወደ ሥራ ማስገባት አስፈላጊ ቢሆንም፣ በወረራ የወደሙ ከዞን እስከ ወረዳና ከተማ አስተዳደር የሚደርሱ አካባቢዎች በጄት ስለሌላቸው ተጨማሪ በጄት ከክልሉ ፈሰስ እንዲደረግላቸው ይፈልጋሉ ተብሏል።

ክልሉ በወረራ ተይዘው ከነበሩ አካባቢዎች በበጄት ዓመቱ መሰብስብ የነበረበትን የገቢ ግብር መስብስብ አለመቻሉ የተገለጸ ሲሆን፣ አካባቢዎቹ ለክልሉ ገቢ በጄት ጉልህ አስተዋጽዖ ነበራቸው ተብሏል።

አማራ ክልል በ2014 በጄት፣ ዓመታዊ በጄቱ 80.1 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ 43 ቢሊዮኑ ከፌዴራል መንግሥት የተመደበለት ነው። ክልሉ ቀሪውን በጀት ከታክስ ገቢ፣ ከዘላቂ ልማት እና በውጭ ብድር የሚሸፍን ሲሆን፣ 34.1 ቢሊዮን ብር ከታክስ ገቢ ለመሸፈን ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ በህወሓት በተወረሩ አካባቢዎች የገቢ ግብር አልሰበሰበም።


ቅጽ 4 ቁጥር 164 ታኅሣሥ 16 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!