የእለት ዜና

ለቀድሞ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚወጣው የጥቅማጥቅም ወጪ የተጋነነ መሆኑ ተመላከተ

ለአንድ የቀድሞ ባለሥልጣን የ120 ሺሕ ብር ረከቦት ተገዝቷል

በጋዜጣው ዘጋቢ
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሥር የሚገኘው ከኃላፊነት የተነሱ የሕዝብና የመንግሥት ባለሥልጣናት ጥቅም ማስጠበቂያ ጽሕፈት ቤት በሚያቅርበው መጠየቂያ፣ በገንዝብ ሚኒስቴር በኩል የሚፈጸሙ ግዢዎች የተጋነኑ እና አግባብነት የጎደላቸው መሆኑ ተመላክቷል።
የሚፈጸሙት ግዢዎች ከቤት ዕቃዎች እንደ ሶፋ፣ አልጋ፣ ጠረጴዛ፣ የቴሌቭዥን ማስቅመጫ፣ መጋረጃ፣ የወኃ ታንከር፣ አልባሳትን እና የቡና ረከቦትንም ይጨምራል። ከቤት ዕቃዎች በተጨማሪ የመኪና ወንበር ልብስ እና በባልሥልጣኑ ሥም ላሉ መኪኖች 4 ጎማ በየዓመቱ እንደሚገዛ ማወቅ ተችሏል።

ዋጋቸውም ለነዚህ መገልገያዎች ከሚወጣው መደበኛ የመግዣ ዋጋ በጣም የተጋነነ እና አግባብነት የሌለው መሆኑን የጽሕፈት ቤቱ ሠራተኛ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። አክለውም፣ ኢትዮጵያ ካለችበት የምጣኔ ሀብት ቀውስ እና የጦርነት ወቅት አንጻር እንዲህ ዓይነት ወጪ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር መሆኑን ይናገራሉ።

ባለሥልጣናቱ ከቀድሞ አስተዳድር ጀምሮ አሁኑ አስካሉት ጠቅላይ ሚኒሰትር ድረስ በማማከር እና በተለያዩ መስኮች ላይ የሚያገለግሉ መሆናችው የሚታወቅ ነው።
ከቀድሞ ባለሥልጣናት መካከል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ እና የመለስ ዜናዊ ባለቤት አዜብ መስፍን ይገኙበታል።

የጽሕፈት ቤቱ ባልደረባ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ለአዜብ መስፍን በተለይ አትላስ አካባቢ ለሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ከ120 ሺሕ ብር በላይ ወጪ ተደርጎ አንድ የቡና ረከቦት እንደተገዛ እና ሌሎች እንደ መጋረጃ ያሉ መገልገያዎችም በከፍተኛ ወጪ ከመንግሥት ካዝና ገንዘብ ወጥቶ እንደተገዙ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን በመጡበት ጊዜ ከመንግሥት ካዝና የሚወጣውን ወጪ፣ በተለይም በሕክምና ሠበብ እና በሥራ ምክንያት ተብሎ ይወጣ የነበረውን የውጪ ምንዛሬ ለማስቀረት ሥራዎች ተጀምርው እንደነበር እና ለአንድ ባለሥልጣን 15 አስታማሚን ጨምሮ የውጪ ምንዛሬ መጠየቂያ ሠነድ እንደገጠማቸው ለመገናኛ ብዙኃን የገለጹት የሚታወስ ነው።

በተያያዘ የአዲስ ማለዳ ምንጭ፣ ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በ68 ሺሕ ብር ወጪ ከአዞ ቆዳ የተሠራ ጫማ በምርጫቸው መገዛቱን አስታውሰው፣ በተለያየ ጊዜ በ10 ሺሕዎች የሚቆጠር ገንዝብ ለፕሮቶኮል ልብስ ከፍተኛ ወጪ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ሌሎች እንደ ቀድሞው የትምህርት ሚኒስቴር ተፈራ ዋልዋ ፣እንዲሁም አዲሱ ለገስ ያሉ ባለሥልጣናት ከመንግሥት ካዝና ለሚወጣ ገንዘብ እንደሚጠነቀቁ ገልጸዋል።

ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ፣ የውጪ ምንዛሬ ዕጥረት ባለባት ደሃ አገር ላይ እንደዚህ ዓይነት ኃላፊነት የጎደለው ተግባር መፈጸሙ አግባብ እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ በተለይም በኮሮና ቫይረስ እና ጦርነት ኢኮኖሚዋ በቀጨጨ አገር ላይ ገደብ የሌለው ወጪ አላስፈላጊ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የሕግ አማካሪ ለአዲስ ማለዳ እንደጠቀሱት፣ በተለምዶ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እየተባለ ይጠራል እንጂ፣ በሕግ ዐዋጁ የጸደቀ እንዳልሆነ ያነሳሉ። ይህ የጥቅማ ጥቅም አስከባሪ ጽሕፈት ቤትም ሕጋዊ ተቋምነቱ በዐዋጅ መጽደቁ አጠራጣሪ ነው ብለዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 164 ታኅሣሥ 16 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!