የእለት ዜና

በምክክርና ድርድር መሀል ያለው ልዩነት ግልፅ ይሁን!

አገራችን ኢትዮጵያ በጦርነት ወጀብ ውስጥ ከገባች 420 ቀናት ገደማ ተቆጥረዋል። በእነዚህ ቀናት የተለያዩ ጦርነቱን የተመለከቱም ሆኑ እያንዳንዱ ውጊያ ላይ የተመረኮዙ መረጃዎች ለሕዝብ ሲቀርቡ ቆይቷል። በመከላከያ ላይ ጥቃት ተሠነዘረ ከሚለው ጉዳይ ባሻገር፣ መቀሌ ተያዘች፤ መከላከያ ትግራይን እንዲለቅ ተወሰነ፤ እንዲሁም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው የህወሓት ታጣቂዎች ደሴንና ኮምቦልቻን ያዙ የሚለው ወሬ በብዙዎች ዘንድ በከፍተኛ መጠን መነጋገሪያ ከነበሩት ጉዳዮች በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱ ናቸው።

በሌላ በኩል፣ ሴራን የመሳሰሉ ወሬዎችና የድልም ሆኑ የሽንፈት መረጃዎች መነጋገሪያ የነበሩትን ያህል፣ በሕዝብ ዘንድ ቁጣን የቀሰቀሱ ጉዳዮችም ነበሩ። የሕዝብን ቁጣ መለኪያና መሥፈሪያ መንገድ ባይኖርም፣ በማኅበራዊ ሚዲያ የነበረን የሐሳብ መንሸራሸር በመመልከት መገመት የሚቻል ነው። ለምሳሌ ያህል መከላከያ ከትግራይ መውጣት አልነበረበትም በሚሉና አማራጭ አልነበረም በሚሉ መካከል የነበረና አሁንም ድረስ ያልረገበ ክርክር አንዱ የሕብረተሰቡን አስተሳሰብ መጠቆሚያ ነበር።

አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ማለት በሚቻል መልኩ ጦርነቱን ደግፎታል በሚባልበት በዚህ ወቅት ድርድር ሊደረግ ነው የሚለው ወሬ ገና ከመነሻው በብዙዎች ዘንድ ተቃውሞ ገጥሞታል። የናይጄሪያው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ለድርድር አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀ ቡድንን እንዲያነጋግሩ መንግሥት ፈቀደ በሚል ተነስቶ የነበረውን ተቃውሞ፣ “ድርድር አይደለም” በሚል በተደጋጋሚ ማስተባበያ ተሰጥቶበት ነበር። ከዛ ቀደም ምንም ዓይነት ድርድር እንደማይደረግ ሲነገር የነበረው ቃል ታጥፎ፣ “ተከዳን” በሚል የብዙዎችን መስዋዕትነት ገደል የከተተ ሐሳብ ነው በሚል ታስቦ ከሆነ እንዲቀር ያስጠነቀቁም ነበሩ። እንዲህ ዓይነት የሐሳብ ፍጭቶችም ሆኑ አለመግባባቶች የሚከሰቱት፣ መንግሥት ግልፅ የሆነ መረጃን በወቅቱ ለሕዝብ ማድረስ ባለመቻሉ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ሕዝብ መረጃ የማግኘት መብቱ በጦርነት ወቅት ሊከበርለት የሚገባ ሲሆን፣ ወታደራዊ ምስጢር ያልሆኑ መሰማታቸው የማይቀር ተግባራትን፣ ጠላት ተብሎ የተፈረጃ አካል እንደፈለገው አድርጎ ሕዝብን ከመንግሥት ለመነጠያ አድርጎ ከመጠቀሙ አስቀድሞ ይፋ ሊደረጉ ይገባል። ድርድር ስለተባለው ጉዳይ፣ መንግሥት አሸባሪ ካለው አካል ጋር ማን ተገናኝቶ ይነጋገራል በሚል ሕግ እንዳይጣስ የሚመክሩ የመኖራቸውን ያህል፣ ከመንግሥት ጎን ሁነው ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች፣ ንብረትና ሐብት ለወደመባቸው፣ እንዲሁም ለተዘረፈባቸው የሚያስተላልፈው መልዕክት ሊታሰብበት ይገባል።

አንድ ቡድን መሣሪያ አንግቦ በጉልበት ሞክሮ አልሳካ ሲለው መደራደር ይችላል የሚል ትምህርት ለሌሎችም እንዳያስተላልፍ፣ እንዲህ ዓይነት ተግባር ከመደረጉ አስቀድሞ በኹሉም አቅጣጫ ሊታሰብብት እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች። በምዕራባውያን ጫናም ሆነ ጥቅም ለማግኘት ሲባል በታሪክ ላይ ተጠያቂ የሚያደርግንና ፍትሕን የሚያጓድል ተግባር ላይ ማንም ቢሆን መሳተፍ እንደሌለበት ይታመናል።

ሠላም ኹሌ በጦርነት ይመጣል ባይባልም፣ ዝግጁ ሆኖ መጠበቁ እንዳለ ሆኖ ሌሎች አማራጮችን መፈለጉ በሐሳብ ደረጃ ክፉ ላይሆን ይችላል። ሠላም ፈላጊ መሆንን ለማመልከት ታረቁም ሆነ ተደራደሩ ለሚል ሦስተኛ ወገን፣ በምንም ዓይነት አይታሰብም ብሎ ከመታበይ፣ እሺ ብሎ ሕዝብን በግልፅ አማክሮ የመደራደሪያ ሐሳብን ጠንከር ባለ አቋም ማቅረብ አማራጭ ሊሆን ይችላል። ይህ ግን በሕዝብ ዘንድ ያለ ተቀባይነትን አሳጥቶ፣ ጠላት ተብሎ የተፈረጀ አካል ከመጀመሪያውም ሲፈልገው የነበረን ነገር በተዘዋዋሪ ማሳካት እንዳይሆን ሊታሰብበት ግድ ይላል።

ጠላት ተብሎ በውጊያ ከሚገዳደሉት ቡድን ጋር በጦርነት ወቅት መነጋገር አዲስ የመጣ ዘይቤ አይደለም። በኢትዮጵያ ያለፉት 200 ዓመታት ታሪክ፣ ባለጋራዎች ከጦርሜዳ በፊትም ሆነ በኋላ ሲደራደሩም ሆነ ሲስማሙ ታይቷል። በአንድ ወቅት ንጉስ የነበሩት አፄ ምኒልክና የጎጃሙ ንጉስ ተክለኃይማኖት ብዙ ሰው ካለቀበት ውጊያቸው በኋላ አንዳቸው ተሸንፈውም ቢሆን ተደራድረው መስማማታቸውን የተቃወመ አልነበረም። ይልቁንም አሸናፊውንም ሆነ ተሸናፊውን ወገን ያስመሰገነ ተግባር ነበር። በአድዋው ጦርነት ወቅትም የውጭ ወራሪ ከነበረው የጣሊያን ጦር ጋር ከውጊያ በፊትም ሆነ ከሽንፈቱ በኋላ ድርድር ተደርጎ ውጤት እንደተገኘበት አይካድም።

በሌላ በኩል፣ ጣሊያን 40 ዓመት ቆይታ ስትመለስ የወልወል ጉዳይ በድርድር ይፈታል ብለው ሳይዘጋጁ ቃሏን አምነው ጉድ ከተሠሩት የዘመኑ መሪዎች መማር ይኖርብናል። እርስበርሳችን ባደረግናቸው ጦርነቶችም፣ ከድርድር የተገኘ መልካም ፍሬ የመኖሩን ያህል፣ ቃላቸውን ባልጠበቁ አካላት ጉድ የተሠሩም ነበሩ። ለምሳሌ፣ ከሰገሌው ጦርነት አስቀድሞ በንጉስ ሚካኤል ላይ የተሠራውን ደባ በማንሳት ፖለተከኛን ማመን እንደማይገባ የሚናገሩ አሉ። ከህወሓት ምሥረታ ጀምሮም ከኢሕአፓ ጋርም ሆነ ከደርግ ጋር ዘግይቶ የተደረጉ ድርድሮች ጊዜ መግዣና አሳቻ ሰዓት መጠበቂያ ሆነው ቡድኖችንም ሆነ አገርን ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈሉ የዘመናችን ባለሥልጣናት ሊማሩባቸው አንደሚገባ አዲስ ማለዳ ማስታወስ ትወዳለች።

የኃይማኖት አባቶች ሠይጣንን ውጣ ብለው ሳይደራደሩ እንደሚያባርሩት፣ ዓለማዊ መንግሥት ሕዝብን በኃይል ብቻ መግዛት እንደማይችል ለመረዳትና ከታሪክ ለመማር ሩቅ መጓዝ አይኖርብንም። የአሸናፊነት ሥነ-ልቦናም ሆነ ዕምነት ያለው ጠላቴ ከሚለው ጋር ተቀምጦ ለመደራደር ወደ ኋላ ለማለት እንደማይገባው ሊታወቅ ይገባል። ጥፋት ያጠፋም ሆነ ከባድ ወንጀል ሠርቷል ተብሎ የተጠረጠረም ቢሆን፣ ሕግ ፊት ቀርቦ ከበደላቸው ፊት ተከራክሮ ወይ ያሸንፋል ወይም ይሸነፍና ይቀጣል።

ድርድር መቀመጡ በራሱ ተሸናፊ እንደማያዳርግ ታምኖ፣ ሊታሰብበት የሚገባው በምን በምን ጉዳዮች ላይ መንግሥት ሕዝብን ወክሎ መደራደር እንደሚችል ነው። ስንት ሺሕ ዘመን በዘለቀና የእኛ ትውልድ በተረከበው በአገር አንድነትና በሉዓላዊነት ጉዳይ ላይ አሁን ያለነውም ሆነ ቀጣዩ ትውልድ መደራደርም ሆነ መቀየር እንደማይገባ አቋም ሊያዝ ይገባል። በባለፈው ዘመን ያለሕዝብ ይሁንታ የተቀየሩ ጉዳዮች በሚያስማማን መልኩ ሊቀየሩ እንደሚችሉ ማሰብም ይገባል።

የሕዝብ ይሁንታ አግኝቶ የሚካሄድ ከሆነ የድርድር ጉዳይ ሊሆኑ የሚገባቸው ተዋጊ ቡድኑን ብቻ የሚመለከቱ ሐሳቦች መሆን እንደሚገባቸው አዲስ ማለዳ ታምናለች። በሕግ መጠየቅ የሚኖርባቸውን የመለየቱ ሥራ እንዳለ ሆኖ፣ በቀጣዩ አገራዊ የምክክር መድረክ መሳተፍ የሚችሉም ሊለዩ ይገባል። እነማን እንደሆኑ ሕዝብ አስቀድሞ ማወቅ እንደሚያስፈልገው ከማመልከት ባሻገር፣ የውይይቱ አጄንዳዎችና ዓላማ መለየት ይኖርበታል። ድርድር የሚደረግ ከሆነም ማን መደራደርና ውይይቱን መካፈል ይችላል የሚለው የኹለቱ ዕቅዶች ልዩነትና ተመሳሳይነትን ጭምር ሕዝብ ሊያውቅ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

በአገራዊ የምክክር መድረኩ ምን ለማግኘት እንደታሰበና ምን ላይ ትኩረት እንደሚደረግ መተማመን ላይ በመድረስ ሒደቱን ሕብረተሰቡ ከስርከስር እየተከታተለ አስተያየቱን እንዲሰጥና ውጤቱም ቅቡልነት እንዲኖረው መሥራት ከመንግሥት ይጠበቃል። የኹለቱም ዋናው የመጨረሻ ግብና ዓላማ ዘላቂ ሠላምን ማምጣት ሊሆን ይገባል። ታጥቆ በመደራደር ካልሆነ እዋጋለሁ ብሎ ማስፈራሪያ መንገድን እንደአማራጭ መጠቀሙን ያልተወ አካል፣ በሠላማዊ መንገድ እታገላለሁ ካለ ጋር እኩል የመነጋገር አቅም አይኖረውም።

ጥላቻ ጥቅም ከማምጣቱ ይልቅ አገርንም ሆነ ራስን እንደሚጎዳ ሊታወቅ ይገባል። አገራዊ ጥቅምም ሆነ የትውልድ አብሮ የመኖር ጉዳይ በጊዜያዊ በደልም ሆነ ጥቂቶች አርቀው ባለማሰብ በፈጠሩት ችግር ዘላለማዊ ሆኖ እንዲቀጥል መደረግ እንደሌለበት የአዲስ ማለዳ አቋም ነው። በሕዝቦች መካከል የነበረ መቀራረብና ውኅደት ወደነበረበት እንዲመለስ ሕይወት ይሰጣል እንጂ፣ በግብዝነትም ሆነ በግትርነት አይሆንም ብሎ ድርቅ ማለቱ አያዋጣም። ልጅ እንኳን የያዘውን ይዞ ለሌላ ያለቅሳል እንደሚባለው፣ ለአገር ሲባል ያሉትን አማራጮች ኹሉ አሟጦ መጠቀም ግድ ይላል። ከግል የአመለካከት ሚዛን በመነሳት ይህን የመሳሰሉ ተግባራትን ከማድረግም ሆነ ካለማድረጋችን በፊት ውይይት በኹሉም ዘንድ ያስፈልጋል። መንግሥትም ሆነ ሕዝብ ትክክለኛ ውሳኔ ላይ እንዲያርፍ ራሱንም ከተጠያቂነትና ከጥላቻ ለማዳን ሒደቱን እያሳወቀ መጓዝ ይኖርበታል።


ቅጽ 4 ቁጥር 164 ታኅሣሥ 16 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!