የእለት ዜና

ከመገናኛ ብዙኀን የሚጠበቅ ጥንቃቄ!

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

በኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በፊት የጀመረው ግጭት ወደ ጦርነት ካመራበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬ እጅግ አሳዛኝ ዜናዎችን ስንሰማ ከርመናል። ከዚህ በኋላም ልንሰማቸው ያሉ እጅግ አሳዛኝ፣ ዘግናኝና ልብ ሰባሪ ታሪኮችና ክስተቶች አሉ።
በዚህ ጦርነት ከጠፋ የሰው ልጅ ሕይወትና ከወደመ ንብረት በተጓዳኝ የብዙዎች ልብና አእምሮ በከባድ ሁኔታ ተጎድቷል። በተመለከቱት ሁኔታ እንዲሁም በደረሰባቸው ጥቃትና በደል የተነሳ፣ ይህ የድባቴ እና ጭንቀት ስሜት ውስጥ ስቦ በማስገባት የሥነልቦና ችግር ሊፈጥርባቸው እንደሚችል እሙን ነው።

ይህ ጉዳይ በአገራችን ብዙም ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም። በእርግጥ በቀደመው ጊዜ ማኅበረሰቡ የመንፈስ ስብራቱን እንዲጠግንባቸው መንገድ የሚያሳዩ የተለያዩ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ነበሩ። ‹ሐሜት ይበዛበታል!› የሚባለው ጎረቤታሞች ሰብሰብ ብለው ቡና የሚጠጡበት ጊዜ ሳይቀር፣ ሰዎች ያላቸውን ጭንቀት ለመፍታትና እፎይታን ለማግኘት የሚያስችላቸው ጥሩ እድል ነበር።

ነገራችን ወዲህ ነው፤ በዚህ ጽሑፍ መግቢያ ላይ እንዳነሳሁት፣ በጦርነቱ ሳቢያ ብዙ ጥፋቶች ደርሰዋል። በሴቶችና ሕጻናት ላይ የደረሰው ጉዳትም ተቆጥሮና ተመዝኖ፣ ተነግሮና ተዘክሮ የሚያልቅ አይደለም። መገናኛ ብዙኀን ታድያ ከተከሰቱ አሳዛኝ ታሪኮች መካከል የአድማጭና ተመልካች ልብ ላይ ደርሰው ስሜቱን በመንካት እየሆነ ያለውን ሁኔታ ያስረዱልናል ያሏቸውን ከጥቃት ጋር የተያያዙ ታሪኮችን ያሳያሉ፣ ያሰማሉ።

በዚህ ጊዜ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች፣ ወጣቶችና እናቶች በትዕይንተ መስኮቶች ብቅ ብለው የደረሰባቸውን ጾታዊ ጥቃት ያስረዳሉ፤ ይናገራሉ። አንዳንዴ በጋዜጦችም ላይ ምስላቸው ይወጣል፤ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀንም ይቀባበላቸዋል።
በቅርቡ ጦርነትና ከጦርነት ጋር ተያያዥ የሆነ ጥቃት ይልቁንም አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ ያለ ጾታዊ ጥቃት ከሚያስከትለው የሥነልቦና ቀውስ ጋር በተገናኘ አንድ መድረክ ላይ ተሳትፌ ነበር። በመድረኩ የተገኙ አንድ ባለሞያ ሲያስረዱ፣ ‹ይህ ደረሰብን፣ ያ ተፈጸመብን› የሚሉ ሰዎች ጋር በተገናኘ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል።

እንዲህ ነው፤ ከወራሪው ኃይል ነጻ በወጡ አካባቢዎች አሁን አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኗል። በዚህ ወቅት ሰዎች ነጻ በመውጣታቸው በሚሰማቸው ደስታና የደረሰባቸውን በደል መተንፈስ ስለሚሹ አደባባይ ወጥተው የደረሰባቸውን ከመናገር አይቦዝኑም። በዚህ መካከል ግን ነገን ይዘነጉታል። ዛሬ የደረሰባቸው በተለይም ጾታዊ ጥቃት ነገ በሕይወታቸው ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ አያስተውሉትም። ፎቷቸው፣ ምስላቸው ዛሬ ብቻ ሳይሆን እስከ ዘለቄታው በበይነ መረብ ላይ ሊቆይ እንደሚችል ትኩረት አይሰጡም።

የደረሰው ጾታዊ ጥቃትና አስገድዶ መድፈር አይነገር ለማለት አይደለም። ነገር ግን መገናኛ ብዙኀን ይህን በሚያደርጉ ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል። ባለታሪኮች ፈቃደኛ ቢሆኑ እንኳ ሁኔታውን ማስረዳትና ገጻቸው እንዲሸፈን ምክረ ሐሳብ አቅርቦ ማስረዳት ተገቢ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 164 ታኅሣሥ 16 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!