የእለት ዜና

በአማራ ክልል የመንግሥት ተቋማት መደበኛ ሥራዎቻቸውን እንዲጀምሩ ውሳኔ መተላለፉ ተገለጸ

በአማራ ክልል የመንግሥት ተቋማት መደበኛ ሥራዎቻቸውን እንዲጀምሩ ውሳኔ መተላለፉን የክልሉ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል ተብሏል።
የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቶ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡን እና በተወሰኑ ጉዳዮች ዙሪያ ማሻሻያ ማድረጉን የክልሉ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ግዛቸው ሙሉነህ ተናግረዋል ነው የተባለው።
የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት በውይይቱ፣ የተገኘውን አንፃራዊ ድል ከግምት ውስጥ በማስገባት ተቋማት መደበኛ ሥራዎቻቸውን እንዲጀምሩ እና በየደረጃው ከሚገኙ ሠራተኞቻቸው ጋር በመወያየት ዕቅዳቸውን አሻሽለው እንዲተገብሩ እንደተወሰነ ተመላክቷል።
የተፈናቀሉ የመንግሥት ሠራተኞች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ፣ የኅልውና ዘመቻውን ለመደገፍ የወጡ የመንግሥት ሠራተኞች ተመልሰው ከመደበኛ ሥራቸው ጎን የኅልውና ዘመቻውን እንዲደግፉም ውሳኔ ተላልፏልም ተብሏል።
የክልሉን የጸጥታ ኹኔታ በሚመለከት የተወያየው የክልሉ ካቢኔ፣ በኹሉም የክልሉ አካባቢዎች የ24 ስዓት የተጠናከረ የጥበቃ አገልግሎት እንዲደረግ አቅጣጫ ማስቀመጡ ተዘግቧል።
በኬላዎች፣ መግቢያ እና መውጫ በሮች እና በተመረጡ አካባቢዎች ፍተሻው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ኃላፊው፣ ሕዝቡ በተለይም ወጣቶች የየአካባቢያቸው የሠላም አርበኛ መሆን አለባቸው ማለታቸው ተመላክቷል።
ግዛቸው እንደሚሉት፣ ሥርቆት፣ ሥርዓት አልበኝነት፣ ዘረፋ እና የሕዝቡን ሠላም የሚነሱ ጉዳዮች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 164 ታኅሣሥ 16 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!