የእለት ዜና

ኢትዮጵያ 20 ቦታ የተሸነሸነችበት ካርታ

ሠሞኑን በማኅበራዊ ሚዲያ ብዙዎችን አነጋግሮ የነበረው፣ አዲሱ ኢትዮጵያን ለማካለል የቀረበ ኃሳብ በሚል ይፋ የተደረገ ካርታ ነበር። ብዙዎች አስተያየታቸውን በትችትም መልክ ይሁን በድጋፍ ከሰጡ በኋላ በወሰን አጣሪ ኮሚቴ የቀረበ አይደለም ተብሎ እንዲጣጣል ተደርጓል።
አዲሱ የአከላለል መንገድ ተብሎ የቀረበው በአማካሪ አካላት እንጂ፣ መጀመሪያውንም መንግሥት ባቋቋመው አካል እንዳልሆነ ቢነገርም፣ ኋላ ላይ ግን በሕብረተሰቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ከታየ በኋላ ገሸሽ ተደርጓል የሚሉ አሉ። የሕብረተሰቡን ትኩሳት ለመፈተሻነት ነው ሆን ተብሎ በዚህ ድርድር እየተባለ በሚወራበት ወቅት ይፋ የተደረገው ብለው የሚሞግቱ ቢኖሩም፣ እኛ ነን ያዘጋጀነው ብሎ ራሱን የሚያሳውቅ ባለመገኘቱ ለትችትም ሆነ ለሙገሳ አለመመቸቱን የተናገሩ ነበሩ።

ካርታው በግለሰብ ደረጃ ለወሬ በሚል የተሠራ እንደማይሆን የጠቀሱ የወሬ ተንታኞች፣ ሆን ተብሎ በባለሙያ የተዘጋጀ መፈተሻ፣ አሊያም የሆነ ጉዳይን ማስቀየሻ ሊሆን እንደሚችል መላምታቸውን ያስቀምጣሉ። ከዚህ ቀደም ትላልቅ የሆኑና ለአስተዳደር የማይመቹ አማራና ኦሮሚያ ክልልን የመሳሰሉ አካባቢዎች ሦስት አራት ቦታ እንዲከፋፈሉ የገዢው ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ሳይቀሩ ይናገሩ እንደነበር የሚያስታውሱ አሉ። ይህ አመለካከት አሁንም በብዙዎች ዘንድ እንዳለ ያመላከተው አዲስ ተብሎ እንደሐሳብ የቀረበው ካርታ ሲሆን፣ ክልል የተባሉትን ነባሮቹን ግዛቶች በማብዛት ወደ 20 ክፍለ-አገሮች የሚያሳድግ ነው።

የቀድሞ ዘመን ካርታ እንዳይመለስ በሚል ለዘመናት የቆዩ ነገሮችን አምርረው የሚጠሉ አካላትን ላለማስቆጣት በሚል፣ ከነባሩም የትላልቆቹ ክልሎች ሥም እንዲቀጥል ተደርጓል። ከአማራ ክልል ወሎ፣ ከኦሮሚያ ወለጋ እንዲለዩ የተደረገ ሲሆን፣ ሸዋ ከኹለቱም ተቀንሶ መልሶ እንዲመሰረት ተደርጓል። ይህን የመሳሰሉ አዲስና ያልተለመዱ አከላለሎችን ይፋ ያደረገው ይክ ካርታ፣ ማንነትን መሠረት አድርጎ በተመሳሳይ ሌላ ቦታን አካለለ እንጂ ነባሩ የፈጠረውን ችግር የሚቀርፍ አይደለም በሚል ተተችቶ ነበር።

ወለጋንም ሆነ ወሎን ራሳቸውን የቻሉ ክልሎች ለማድረግ የሚሞክሩት ላይ አንድነትን ሊያጠፉ ነው በሚል የሚሠነዘርባቸው ትችትን ማንም የሚያውቀው እንደሆነ የጠቀሱ አስተያየት ሰጪዎች፣ እነዚሁ ተቺዎች አገሪቷ በዘር የተመሠረተ ክልል እንዳይቀጥልባት የሚፈልጉ ናቸው ይላሉ። የቀደመው ዘመን ከርቀትና ከተፈጥሮ ጋር በተያያዘ የተካለለው እንዲቀጥል ቢፈልጉም፣ ፍላጎታቸውን በፍራቻ እንደማይናገሩ ይጠቁማሉ። “መሬቱ የእኛ ብቻ ነው” የሚሉትን ለማስቀረት ትላልቆቹን አፍርሶ መጠነኛ ተመጣጣኝ ግዛቶች እንዲቋቋሙ የሚመኙት ሰዎች፣ የሚያሰጋቸው አካል ቀድሞ ካልፈረሰ የእነሱ እንዲቆራረጥ አንደማይፈልጉ ይናገራሉ።

አዲስ ተብሎ የቀረበው ካርታም የማኅበረሰብን ሥጋትና ምኞት ያሳየ ነው የሚሉት አስተያየታቸውን የሰጡ ግለሰቦች፣ አብዛኛው የሚፈልገውን ከመናገር ተቆጥቦ ጠላት ላለማብዛት እየተያየ እንደሚገኝ ያመለክታሉ። የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል እንደሚባለው፣ ከእዛም ብሶ ውጭ እያደርን ነው በሚል ሐሳባቸውን ሠንዝረዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 164 ታኅሣሥ 16 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!