የእለት ዜና

ወደ አማራ ክልል የሚመጡ የዳያስፖራ ጎብኝዎችን የጊዜ ቆይታ ለማራዘም እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

ህወሓት በአማራ ብሔራዊ ክልል ባደረሰው ከፍተኛ ጉዳት የወደመውን ኢኮኖሚ መልሶ ለመገንባት እንዲያስችል ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ዳያሰፖራ አባላት፣ በክልሉ የሚኖራቸውን የጉብኝት ጊዜ ለማራዘም እየሠራ መሆኑን የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
በዚህም በቅርቡ የሚከበረው የገና በዓልን ታሳቢ በማድረግ ላሊበላ ላይ ሠፊ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ነው የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አበበ እምቢያለ ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።

በዋናነት የአካባቢውን የጸጥታ ኹኔታ አስተማማኝ ለማድረግ ከመሥራት ባለፈ፣ በህወሓት ታጣቂዎች የፈረሰውን የላሊበላ ኤርፖርት ጊዜያዊ በረራ ለማስጀመር ለኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ከአስራ አምስት ቀን በፊት ደብዳቤ መጻፉን ገልጸዋል። በዚህም የላሊበላ ኤርፖርት ለበዓሉ ጊዜያዊ የበረራ አገልግሎት እንደሚጀምር ጠቁመው፣ አሁን ላይ በክልሉ መንግሥት በተቋቋመ ግብረ ኃይል የጥገና ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አመላክተዋል።

እስካሁን ይህን ያህል ሰው በዓሉን ይታደማል ተብሎ የተያዘ ዕቅድ ባይኖርም ከፍተኛ ታዳሚ ሊመጣ እንደሚችል ይገመታል ያሉት ኃላፊው፣ በከተማዋ የሚገኙ ሆቴሎች ምግብ ማቅረብ እንዲችሉና የመኝታ አገልግሎት እንዲሠጡ ምርቶችና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶች ከያሉበት አካባቢ ወደ ከተማዋ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

የስልክ አገልግሎት ቴሌ ያስጀመረ ሲሆን፣ የመብራት አገልግሎት ለማስጀመርም ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር እየተነጋገርን ነው ያሉት ኃላፊው፣ በዚህም ከበዓሉ በፊት በከተማዋ የመብራት እና የውኃ አግልግሎት ይኖራል ነው ያሉት።

በተያያዘም፣ በቀጣይ የሚከበረውን የጥምቀት በዓልን በክልሉ በድምቀት በማክበር የዳያስፖራውን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም እንደሚሠራ ነው የገለጹት። በተለይ በጎንደር እና ሰሜን ሸዋ ምንጃር ወረዳ፣ የጥምቀት በዓል በክልል ደረጃ በድምቀት የሚከበር መሆኑን አብራርተዋል።
ጣና ሐይቅ ላይም እንዲሁ ትልቅ የታንኳ ቀዘፋ ትዕይንት የሚዘጋጅ ሲሆን፣ የአዊ ፈረሰኞች ማኅበርም የተሻለ የፈረስ ጉግስ ፌስቲቫል እንዲያዘጋጁ ማድረግ የዕቅዱ አንድ አካል ተደርጎ እየተሠራ ነው ተብሏል።

የዓባይ ወንዝ መነሻ በሆነችው ሰከላ ወረዳም በተጨማሪ የግዮን በዓል የሚከበር መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ አክለውም በደብረ ታቦር ከተማ የመርቆርዮስ በዓል በፈረስ ጉግስ ታጅቦ እንደሚከበር ነው ያነሱት። ይህም ቱሪስቶች ተመችቷቸው ረጅም ጊዜ ቆይታ እንዲኖራቸው በማድረግ፣ ቀድሞ በኮሮና ቫይረስ አሁን ደግሞ በጦርነት ክፉኛ የተጎዳውን የክልሉን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ይሠራል ተብሏል።

በአማራ ክልል በርካታ የቱሪስት መስኅቦች መኖራቸውን ተከትሎ ብዙ ዳያስፖራዎች ወደ ክልሉ ስለሚመጡ፣ ከተቻለ በቅናሽ ካልሆነም በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ ታቅዷል ብለዋል። በዚህም በባህር ዳር ከተማ የሆቴሎች ማኅበር 30 በመቶ ቅናሽ እንዲኖር እየሠራ ሲሆን፣ ይህንንም በክልሉ ወዳሉ ሌሎች ከተሞች ለማስፋት ታስቧል ሲሉ ገልጸዋል።

ወደ አገራቸው የሚመጡ ኢትጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዚያውም በህወሓት ጉዳት የደረሰባቸው ኹሉንም አካባቢዎች ተዘዋውረው እንዲመለከቱ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑም ተገልጿል። በዚህም ጎብኝዎች ለተጎዱት ማኅበረሰቦች የሥነ-ልቦናም ይሁን የቁሳቁስ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ነው ኃላፊው የጠቆሙት።


ቅጽ 4 ቁጥር 164 ታኅሣሥ 16 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!