የእለት ዜና

በሱማሌ ክልል የተከሠተው ድርቅ ተባብሶ ሊቀጥል ይችላል ተባለ

በሦስት ወራት ከ150 ሺሕ በላይ እንሰሳት ሞተዋል

በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል የተከሰተው ድርቅ በቀጣይ ወራትም ተባብሶ ሊቀጥል ይችላል ሲል የክልሉ አርብቶ አደር ልማት ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የሱማሌ ክልል የአርብቶ አደር ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ መሐመድ ገኣሌ አብዲ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ዝናብ ይዘንብባቸዋል ተብሎ በሚታመንባቸው ያለፉት ሦስት ወራት ውስጥ ዝናብ ባለመዝነቡ፣ የተከሰተው ድርቅ ከዚህ ቀጥሎ ባሉት የበጋ ወራትም ተባብሶ ሊቀጥል እንደሚችል አመላክተዋል። ምክትል ኃላፊው አያይዘውም፣ ክልሉ በዋናነት ዝናብ የሚያገኘው በበልግ እና መኸር ወቅት በመሆኑ በመጭዎቹ ሦስት የበጋ ወራት ዝናብ ይዘንባል ተብሎ አይጠበቅም ብለዋል።

በዚህም፣ በዝናብ ዕጥረት ምክንያት የውኃ ጉድጓዶች መድረቃቸውን እና በቀጣይም ውኃ ለማግኘት ይበልጥ አስቸጋሪ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የድርቁ ሁኔታ ይለያይ እንዲ በኹሉም የክልሉ ዞኖች መከሰቱን የጠቆሙት ኃላፊው፣ በቀጣይ ወራትም አስከፊ ኹኔታ የሚከሠትባቸው ቦታዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ነው የገለጹት።

ምክትል ኃላፊው በክልሉ ድርቅ ከተከሠተባቸው ዞኖች ውስጥ በዳዋና ሸበሌ ዞኖች ያለው በጣም የከፋ ነው ካሉ በኋላ፣ በእነዚህ ዞኖች አስተማማኝ የውኃ ምንጭ የሌላቸው ማኅበረሰቦች በርካታ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ፣ በአፋሌር እና ኮራይ ዞኖችም በድርቁ የተነሳ መጠነ ሠፊ ጉዳት እየታየ ነው የሚሉት ኃላፊው። ከተጠቀሱት ዞኖች በተጨማሪ ሲቲ ዞን ውስጥም እንዲሁ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት መድረሱን ሳይጠቅሱ አላለፉም።

የቦረና ዞን አጎራባች በሆነው ዳዋ ወረዳ ብቻ በጥቅምት ወር በተደረገ ጥናት ከ47 ሺሕ በላይ የቤት እንስሳት እንደሞቱና፣ ከ60 ሺሕ በላይ አርብቶ አደሮች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው መገለጹ ይታወሳል።
በክልሉ ገጠራማ አካባቢዎች የሚኖረው ማኅበረሰብ የተራራቀ ስለሆነ እርስበርስ ለመተጋገዝ እና ያለውን ሀብት በጋራ ለመጠቀም አስቸጋሪ እንዳደረገው ጠቁመው፣ በዚህም የተነሳ ድርቁ አስከፊ ጉዳት ማስከተሉን ተናግረዋል።

በርካታ አርብቶ አደር ማኅበረሰብ በሱማሌ ክልል መኖሩን ተከትሎ፣ አርብቶ አደሮች ውኃ ለማግኘት በክልሉ ውስጥ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የቤት እንስሳትን ይዘው እንደሚሰደዱ አንስተዋል።

እስካሁንም ሦስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውሰጥ ከ150 ሺሕ የማያንሱ ግመሎች፣ ፍየሎችና ሌሎች የቤት እንስሳት በድርቁ ምክንያት መሞታቸው ተመላክቷል። በቀጣይ ወራትም በድርቁ ምክንያት የሚሞቱ የቤት እንስሳት ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል ነው የተገለጸው።
በድርቁ ምክንያት ባጋጠመው የከፋ የመጠጥ ውኃ ዕጥረት ከሚሞቱት የቤት እንስሳት በተጨማሪ፣ በክልሉ አሁን ላይ ከአራት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ዕርዳታ ፈላጊ እንደሆኑ ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል።

የክልሉ መንግሥት ከተለያዩ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች ጋር በመሆን ውኃ ማጠራቀሚያ ቁሳቁሶችን እንደሚያቀርብና ውኃ በቦቴም እንደሚያሠራጭ ምክትል ኃላፊው አመላክተው፣ ድርቁ በዚህ ከቀጠለ ከእስካሁን የባሰ ጉዳት ሊደርስ ስለሚችል ድጋፍ ማድረግ የሚችሉ አካላት እርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በክልሉ በድርቅ ምክንያት የተከሠተውን ችግር ለመከላከል 60 ሚሊዮን ዶላር ገደማ የሚያስፈልግ ሲሆን፣ እስካሁን የተገኘው ገንዘብ ግን ግማሹንም እንደማይሸፍን መረጃዎች ያመላክታሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 164 ታኅሣሥ 16 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!