የእለት ዜና

“አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአጎዋ ተጠቃሚነት ያስወጣችብትን ውሳኔ ልታጤነው ይገባል”፡-የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር

ሰኞ ታህሳስ 18/ 2014 (አዲስ ማለዳ) አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአጎዋ ተጠቃሚነት ያስወጣችብትን ውሳኔ አጥብቃ ልታጤነው እንደሚገባ ኢትዮጵያ አመልክታለች።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአጎዋ የንግድ ሥርዓት ያስወጣችበትን ውሳኔ በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል።

የአፍሪካ አገራትን በንግድና ሥራ እድል ተጠቃሚ ከሚያደርገው የአጎዋ ንግድ ስርዓት አሜሪካ ኢትዮጵያን ማስወጣቷ የኢትዮጵያን መንግስት እንዳሳዘነው ነው መግለጫው ያመለከተው።

የኢትዮጵያ መንግስት ሰላምና መረጋጋትን፣ ፖለቲካዊ መግባታትና ኢኮኖሚያዊ እድገትን ሊያመጡ የሚችሉ ሥራዎችን ባለፉት ሦስት ዓመታት ማከናወኑን ያመለከተው መግለጫው በተለይ ደግሞ የሁለቱን አገራት ረጅም ጊዜ የቆየ ግንኙነት ያማከለ የለውጥ ሥራዎች መከወኑንም አንስቷል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

ከአሜሪካ ልዩ ልዩ ተቋማት ጋር ደግሞ የሁለትዮሽ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ግንኙነቱን ለማጠንከር እየተሰራ መሆኑን ያብራራው መግለጫው፤ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን ከአጎዋ ማስወጣት በአጎዋ የሥራ እድል የተፈጠረላቸውን በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን የሚጎዳ ተግባር ከመሆን ባለፈ በእነሱ ስር ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎችንም ኑሮ የሚያመሳቅል መሆኑንም አስታውቋል።

በዚህም አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአጎዋ ተጠቃሚነት ያስወጣችበትን ውሳኔ አጥብቃ ልታጤነው እንደሚገባ ጠይቋል።

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!