የእለት ዜና

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ዳግም ወደ ሥራ ሊመልስ መሆኑ ተገለፀ

ሰኞ ታህሳስ 18/ 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ዳግም ወደ ሥራ ሊመልስ መሆኑን አስታውቋል፡፡

አየር መንገዱ የቦይንግ 737-ማክስ አውሮፕላኖች ዳግም ወደ ሥራ ለመመለስ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑንና የመጀመሪያ በረራውን ጥር 24/ 2014 እንደሚደረግ ነው የገለፀው፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ተወልደ ገብረ ማርያም ደህንነት የኩባንያው ቀዳሚ ጉዳይ መሆኑን በመጥቀስ አየር መንገዱ 737-ማክስ አውሮፕላኖችን ዳግም ወደ ሥራ ሲመልስም የተለያዩ አገራት የአቪዬሽን ቁጥጥር ተቋማት ለአውሮፕላኑ ዳግም የበረራ ፈቃድ ከሰጡ በኋላ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በዓለም 34 ያህል አየር መንገዶች አውሮፕላኑን ዳግም እየተገለገሉበት እንደሚገኙ ተጠቅሷል፡፡

አየር መንገዱ የቦይንግ 737-ማክስ አውሮፕላንን ለመመለስ ከመጨረሻዎቹ አየር መንገዶች ተርታ እንደሚሆን በገባው ቃል መሰረት የዲዛይን ማሻሻያ ሥራውንና ከ20 ወራት በላይ የፈጀውን ጥብቅ የማረጋገጫ ሂደት ሲከታተል እንደቆየና አብራሪዎች፣ ኢንጀሮች፣ የአውሮፕላን ቴክኒሻኖች እና የበረራ ባለሙያዎቹ በአውሮፕላኑ እርግጠኛ እስከሚሆኑ ድረስ መጠበቃቸውን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ አንድ ወር ውስጥም ለተጓዦች ተጨማሪ ዝርዝር መረጃዎችን እንደሚያቀርብ ከአየር መንገዱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!