የእለት ዜና

በባሕር ዳር ከተማ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችና የቴሌኮሙዩኒኬሽን ቁሳቁስ በቁጥጥር ሥር ዋሉ

ማክሠኞ ታህሳስ 19/ 2014 (አዲስ ማለዳ) በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የተለያዩ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎችና የቴሌኮሙዩኒኬሽን ቁሳቁስ በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡

ፖሊስና ሌሎች የፀጥታ አካላት ከማኅበረሰቡ የተሰጣቸውን ጥቆማ ይዘው ባደረጉት ክትትል ለግንኙነት መረብ የሚያገለግሉ የተለያዩ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ቁሳቁስን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ ወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ ም/ኮማንደር ጌታቸው ውድነህ በአሁኑ ወቅት ማኅበረሰቡ ከፖሊስ፣ ሚሊሻ፣ ሰላምና ሕዝብ ደኅንነት፣ ልዩ ኃይልና መሰል የፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ በመሆኑ ወንጀሎችን የመቀነስ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በዚህም ኅብረተሰቡ በሚሰጠው ጥቆማ በተደረገ ጥብቅ ክትትል ለቴሌኮሙዩኒኬሽን ግንኙነት የሚያገለግሎ ከ58 በላይ ትልልቅና ትንንሽ ባትሪዎች፣ የኤሌክትሪክ ባውዛዎችና የተለያዩ የአሉሚኒየምና የመዳብ የመስመር ገመዶችን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህን ወንጀል የሚፈፅሙ አካላትን ለመያዝ ክትትል ሲደረግ መቆየቱንና ለወንጀል የሚጠቀሙባትን ባጃጅ ይዘው ባደረጉት ምርመራ ለወንጀሉ ተባባሪ ከሆኑ 12 ተጠርጣሪዎች መካከል 8ቱ መያዛቸውንና በቀሪዎች ላይም ክትትል እየተደረገ መሆኑን ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ቁሳቁስ በመውሰድ የግንኙነት መረብ እንዲቋረጥ ተልዕኮ ይዘው የሚሰሩም ሊሆን ስለሚችል እንዲህ ዓይነቱን የማኅበረሰብ ጠንቅ የሚሆን ወንጀል በጥብቅ መከታተል እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የመሰረተ ልማትና ሌሎች የሕዝብ ሀብቶችን የሚመዘብሩ አካላት በማኅበረሰቡና ፀጥታ መዋቅሩ የጋራ ጥረት እንዲወገዱ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንደሚገባ ከከተማው ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!