የእለት ዜና

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ በአብላጫ ድምፅ ፀደቀ

ዕሮብ ታህሳስ 20/2014 (አዲስ ማለዳ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 2ኛ ልዩ ስብሰባው ከሕግ፣ ፍሕት እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በረቂቅ አዋጁ ላይ የቀረበለትን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ ነው ያጸደቀው።

ረቂቅ አዋጁ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎበት በውይይቶች የተገኙ ግብዓቶችን መሰረት በአንቀጾች ላይ ክለሳና ማስተካከያ መደረጉ ተገልጿል።

በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይም የምክር ቤቱ አባላት በረቂቅ አዋጁን ወቅታዊነት እና አስፈላጊነት ላይ ጥያቄና አስተያየት አንስተው፤ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዕጸገነት መንግስቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ በ13 ተቃውሞ እና በአንድ ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ መጽደቁን ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በጋራ እንዲመክሩና ብሔራዊ መግባባትን እንዲፈጥሩ ለማስቻል በሚል ከዓመታት በፊት ጀምሮ ሲጠየቅ የነበረውን አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋም ጉዳይ ከመጋቢት 2010 በኋላ እንደአዲስ የተደራጀው መንግሥት በምርጫ ማግሥት ይህንኑ እውን ለማድረግ ቃል ገብቶ እንደነበር ይታወሳል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!