የእለት ዜና

51 ኢትዮጵያዊያንን ሲያዘዋውሩ የነበሩ ሁለት ታንዛኒያዊያን ተያዙ

ዕሮብ ታህሳስ 20/2014 (አዲስ ማለዳ) የታንዛኒያ ፖሊስ 51 ኢትዮጵያዊያንን ሲያዘዋውሩ ነበር ያላቸውን ሁለት ታንዛኒያውያን መያዙን አስታወቀ፡፡

ሁለት ታንዛኒያውያን 51 ኢትዮጵያዊያንን በህገ ወጥ መንገድ ሲያዘዋውሩ በፖሊስ መያዛቸው ነው የተገለፀው፡፡

እንደ ሲጂቲኤን ዘገባ ከሆነ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለማቅናት በሚል በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ ኢትዮጵያዊያኑ ከነ አዘዋዋሪዎቹ በፖሊስ ተይዘው ታስረዋል፡፡

የታንዛኒያ ፖሊስም ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎቹ የተያዙት በዶዶማ ክልል በጭነት ተሽከርካሪ ውስጥ አድርገው ከታንዛኒያ ለማስወጣት ሲሞክሩ በህግ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ከወንጀሎቹ ጀርባ ተጨማሪ ወንጀሎችን ያከናውኑ መሆና አለመሆኑን ለማጣራት ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራዎችን እንደሚያካሂድም ተገልጿል፡፡

ታንዛኒያ ኢትዮጵያዊያን በህገወጥ መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት የሚመርጧት መሸጋገሪያ አገር ስትሆን በህገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የተገኙ ኢትዮጵያዊያን በታንዛኒያ እስር ቤት እንደሚታሰሩም የሲጂቲኤን ዘገባን ዋቢ አድርጎ አል አይን ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትም ከታንዛኒያ አቻው ጋር በመነጋገር በየጊዜው በታንዛኒያ እስር ቤቶች ያሉ ዜጎችን ወደ አገራቸው በመመለስ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!