የእለት ዜና

ሆቴሎች ከውጭ የሚመጡ እንግዶችን በተሟላ መስተንግዶ ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸው ተገለፀ

አርብ ታህሳስ 22/2014 (አዲስ ማለዳ) በአገሪቱ የሚገኙ ሆቴሎች ከውጭ የሚመጡ እንግዶችን እንደ ዕድል በመቁጠር በልዩ ሁኔታ ለመቀበልና ለማስተናገድ የተሟላ ዝግጅት ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ ሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ገለጸ።

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት ሲመጡ የውጭ አገራት ዜጎች ይዘው ለመምጣት ጥረት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ሆቴልና መሰል አገልግሎት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍትህ ወልደሰንበት ሁሉም በአገሪቱ የሚገኙ ሆቴሎች የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን “የአንድ ሚሊዮን ዲያስፖራ የአገር ቤት ጉዞ ጥሪ” ተቀብለው ለመጡ ዲያስፖራዎች በደስታ ለመቀበል ዝግጁ ናቸው ብለዋል።

አክለውም በፀጥታ፣ በመስተንግዶና በመሰል ጉዳዮች ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ለእንግዶቹ አርኪ መስተንግዶ ለመስጠት የተሟላ ዝግጅት መደረጉንም ገልፀዋል።

ዲያስፖራው የሆቴል አገልግሎት ለማግኘት ለዓለም አቀፍ የሆቴል ቡኪንግ ኤጀንቶች የሚከፍሉትን ገንዘብ ለማስቀረት በቅርቡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በአንድ የግል ድርጅት አማካኝነት የተከፈተውን የሆቴል ቡኪንግ አገልግሎት እንዲጠቀሙ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ዶክተር ፍትህ አመልክተዋል።

በኮቪድ 19ና በአገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ተቀዛቅዞ የነበረው የሆቴል ሥራ በአሁኑ ጊዜ በጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፣ ሆቴሎቹ ከወዲሁ ከውጭ ወደ አገር የሚመጡ እንግዶች በልዩ ሁኔታ ለመቀበል፣ አርኪ መስተንግዶ ለመስጠትና የተለያዩ የመዝናኛ ዝግጅቶችን ከማዘጋጀት አኳያ ፍክክር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል።

ዲያስፖራው ወደ አገር ቤት መምጣቱ ሕወሓት በአገሪቱ ላይ ያደረሰውን ጉዳት በተጨባጭ አይቶ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እውነታውንና አስነዋሪ ድርጊቱን ከማጋለጥ ረገድ ሚናው የጎላ ነው ያሉት ዶክተር ፍትህ፣ በውጭ አገራት ሆነው የኢትዮጵያ ድምጽ በመሆን ብርቱ ተጋድሎ ያደረጉ ዲያስፖራዎች አሁንም በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት አሻራቸውን ማሳረፍ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

አስጎብኝ ድርጅቶች ዳያስፖራውን ለማበረታታት ከተለያዩ መስተንግዶ የዋጋ ቅናሽ ማድረጋቸውን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ክልሎችም በተመሳሳይ መልኩ ዳያስፖራውን በጥሩ ሁኔታ ለመቀበል ዝግጅት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ሆቴሎች ዳያስፖራዉን በልዩ ሁኔታ ለመቀበል 30 በመቶ የወጋ ቅናሽ ማድረጋቸዉን አመልክተው፤ ዳያስፖራዉ ወደ ሚኖርበት አገር ሲመለስ የበለጠ ስለ አገሩ ጠበቃና አምባሳደር እንዲሆን በሁሉም ረገድ የተሟላ ዝግጅት መደረጉን ዶክተር ፍትህ አስታውቀዋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!