የእለት ዜና

የቤንሻጉል ሕዝቦች ነጻ አውጭ ንቅናቄ ሠራዊት የቀድሞ መሪ ከአሶሳ ማረሚያ ቤት አመለጠ

ከዚህ በፊት የዕድሜ ልክ ዕሥር ተፈርዶበት አምልጦ ነበር

የቤንሻጉል ሕዝቦች ነጻ አውጭ ንቅናቄ (ቤሕነን) የቀድሞ ሠራዊት መሪ አብዱልዋሀብ መሐድ ታሥሮ ከነበረበት አሶሳ ዞን ማረሚያ ቤት ማምለጡን አንድ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
የዘጠኝ ዓመት ዕሥር የተፈረደበት አብዱልዋሀብ ያመለጠው ታኅሣሥ 18/2014 መሆኑ ተገልጿል። ግለሰቡ ከዚህ በፊትም እንዲሁ 2001 የዕድሜ ልክ ዕሥራት ተፈርዶበት የነበረ ሲሆን፣ 2002 ላይ ከማረሚያ ቤት አምልጦ ወደ ኤርትራ በመግባት ኢትዮጵያን ከሚወጉ ኃይሎች ጋር ሲሠራ እንደነበር ተገልጿል።

ከዚያ በመቀጠል 2009 ላይ የፌዴራሉና የክልሉ መንግሥት ግለሰቡ ከሚመራው ቡድን ጋር ባደረጉት የሠላም ድርድር ተስማምቶ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ሠላማዊ ኑሮ መምራት ጀምሮ እንደነበር ነው የተመላከተው።
ግለሰቡ ይመራቸው የነበሩ ታጣቂዎች ከመንግሥት 20 ሚሊዮን ብር መቋቋሚያ ተቀብለው ተበታትነው ከቆዩ በኋላ፣ ሰኔ 2010 ዳግም አሶሳ ላይ ጥቃት በፈጸሙበት ወቅት መሪው ራሱ ተሳታፊ በመሆን የሰው ነፍስ አጥፍቷል ተብሏል።

በዚህም ግለሰቡ ተከሶ ሲከራከር ከቆዬ በኋላ፣ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የ16 ዓመት ከስድስት ወር ዕሥራት ተፈርዶበት እንደነበር ታወቋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ፍርደኛው ለፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ አቅርቦ ቅጣቱ ወደ ዘጠኝ ዓመት ዕሥር ዝቅ ተደርጎለት የነበረ ቢሆንም፣ ዐቃቤ ሕግ በቅጣት ውሳኔው ባለመስማማቱ በፍርድ ክርክር ሒደት ላይ ሳለ ግለሰቡ አምልጦ መጥፋቱ ነው የተነገረው።

ግለሰቡ ፍርድ የተሠጠው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት ሆኖ፣ ለቤተሰብ እንዲቀርብ በሚል ወደ አዲስ አበባ ሌሎች ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች እንዳልተወሠደ ነው የተጠቆመው።

ታሳሪው በፌዴራልና በክልሉ መንግሥት በጥብቅ ሲፈለግና ከፍተኛ ክትትል ሲደረግብት የነበረ ከመሆኑም አንጻር፣ በርካታ ዕሥረኞች ካሉበት ማረሚያ ቤት ቀን ላይ በግልጽ ለኹለተኛ ጊዜ ማምለጡ፣ ሴራ ሳይኖርበት እንዳልቀረ ያመላክታል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ መረጃ የሠጡት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊው ጠቁመዋል።

አሁን ላይ የቤንሻንጉል ክልል የፀጥታ ኃይሎች ዕሥረኛውን እየፈለጉት ቢሆንም፣ ቦታው ለሱዳን ካለው ቅርበት፣ እንዲሁም ሰውዬው መውጫ እና መግቢያውን የሚያውቅ፣ በትግልም ለ20 ዓመት ገደማ የቆዬበት በመሆኑ በቀላሉ ሊገኝ ይችላል ተብሎ እንደማይታሰብ ነው የሥራ ኃላፊው የገለጹት።

ግለሰቡ ሱዳን ከገባ በኋላም እንደከዚህ ቀደሙ ወጣቶችን መልምሎ በማሠልጠን፣ በመተከልና አሶሳ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎች ላይ ተመሳሳይ የሽብር ድርጊቱን ሊቀጥል እንደሚችል ነው የተመላከተው።

የአብዱልዋህብ አጋር የነበሩ ሰዎች ሱዳን ውስጥ በርካታ ወጣቶችን በማሰልጠን ክልሉ ውስጥ ረብሻ ሲፈጥሩ ቆይተዋል የሚሉት አስተያየት ሰጭው፣ በዚህም የሰውዬው ከዕሥር ቤት ማምለጥ ለአካባቢው ሠላምና ደኅንነት አደገኛ ነው ብለውታል።

የአሶሳ ዞን ማረሚያ ቤቶች መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ሐሩን አብዱራማን ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ግለሰቡ ከተፈረደበት ከስድስት ወር በኋላ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተጣለበት ቅጣት ላይ ጥያቄ ማቅረቡ ስሜታዊ እንዳደረገው እና ለልማት ሥራ በሚል ከማረሚያ ቤት ሲወጣ በነበረበት ወቅት እንዳመለጠ አስረድተዋል።

በተመሳሳይ ወንጀል ከእሱ ጋር ተፈርዶባቸው የነበሩ አራት ግለሰቦች የዕሥር ጊዜያቸውን ጨርሰው ወጥተዋል። ግለሰቡም ከተፈረደበት ዘጠኝ ዓመት ውስጥ ግማሹን ጨርሶ የነበር ቢሆንም፣ ዐቃቤ ሕግ ጊዜው ካለፈ በኋላ ከሕግ አግባብ ውጭ በዕሥሩ ላይ ጥያቄ በማቅረቡ ተጨማሪ ጊዜ ላለመታሠር በሚል ነው ሊያመልጥ የቻለው በማለትም ኃላፊው አብራርተዋል።

ከአብዱልዋህብ ውጭ ከማረሚያ ቤቱ ያመለጠ ሌላ ታራሚ እንደሌለ የሚናገሩት ኃላፊው፣ እሱም በቅርብ ቀን በቁጥጥር ሥር ይውላል የሚል ግምት እንዳለቸው ተናገረዋል። አያይዘውም ግለሰቡ ወደ ሱዳን እንዳይወጣ ኹሉም ቦታዎች በፀጥታ ኃይሎች መዘጋታቸውን ገልጸው፣ ዕሥረኛው ወደ ሱዳን ከመሸሽ ይልቅ ተጸጽቶ ተመልሶ ይመጣል የሚል ዕምነት እንዳለቸው ተናግረዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 165 ታኅሣሥ 23 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!