የእለት ዜና

በአዲስ አበባ ጫማ በማጽዳት ላይ የተሠማሩ ወጣቶች ከሥራ መታገዳቸውን ገለጹ

የእገዳው ምክንያት የዳያስፖራ መምጣት ነው ተብሏል

በአዲስ አበባ በተለይም በመሀል ከተማ ጫማ በማጽዳት ሥራ (ሊስትሮ) ላይ የተሠማሩ ወጣቶች ከሥራቸው መታገዳቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ወጣቶቹ ከሥራቸው የታገዱት በአዲስ አበባ ደንብ አስከባሪዎች ሲሆን፣ ከሥራ የታገዱበት ምክንያትም የገናን በዓል በአገራቸው ለማሳለፍ ወደ ኢትዮጵያ ከሚመጡ ዳያስፖራዎች ጋር በተያያዘ መሆኑን ተነግሯቸዋል። አዲስ ማለዳም በተለይ በመሀል የከተማዋ አካባቢዎች በጫማ ሥራ ላይ የተሠማሩ ወጣቶች በሥራ ቦታቸው ላይ አለመኖራቸውን ተዘዋውራ ተመልክታለች።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ወጣቶች፣ “አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ ወደ ኢትዮጵያ ሊመጣ በመሆኑ ከሥራችሁ ተነሱ ተብለን ንብረታችንን ተቀምተናል” ሲሉ ተናግረዋል።

ቤተሰብ የምናስተዳድርበትን ሥራ እንዳንሠራ መታገዳችን አግባብንት የጎደለው ድርጊት መሆኑ ሳያንስ ደንቦች ንብረታችንን ቀምተውናል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ ካባለፈው ታኅሳስ 16/2014 ጀምሮ ከሥራ መታገዳቸውንና ንብረታቸውን መቀማታቸውን ነው የገለጹት።
መስፍን አርሳዶ የተባሉት ግለሰብ ለስምንት ዓመት ቤተሰብ የሚያስተዳድሩት የጫማ ማጽዳት ሥራ (ሊስትሮ) በመሥራት እንደነበር ተናግረው፣ ሰሞኑን ግን የዳያስፖራውን መምጣት ምክንያት በማድርግ ደንብ አስከባሪዎች ከሥራቸው እንዳነሷቸውና የሥራ ዕቃዎቻቸውንም እንደወሰዱባቸው ተናግረዋል።

ደንብ አስከባሪዎች፣ “ዳያስፖራዎች ሊገቡ ስለሆነ የእናንተ እዚህ መቀመጥ ለገጽታ ጥሩ አይደለም” በማለት ነው ያነሱን የሚሉት መስፍን፣ ለዕይታ ጥሩ አይደለም የተባለው ድሃ ስለሆን ነው፤ ድህነታችንን ደግሞ ለዳያስፖራዎችም ቢሆን የተደበቀ አይደለም ሲሉ ነው አስተያየት የሠጡት።

አክለውም፣ “በዓመት ኹለት ሦስት ጊዜ ደንቦች ዕቃችንን ይወስዱብናል፤ እኔ ራሱ ኹለት ጊዜ ሙሉ የሊስትሮ ዕቃየን ተቀምቻለሁ። ይህን ዕቃ የገዛሁት ጫማ ጠርጌ እንጂ ሰረቄ አይደለም፤ ሲወሰድብኝ ግን እንደ ወንጀለኛ ተቆጠሬ ነው” ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
ዳያስፖራ ሊመጣ መሆኑን ተከትሎ አንድ ሺሕ 200 ብር የሚገመት ሸራና የጫማ ቀለም ተቀምቻለሁ የሚሉት መስፍን፣ 2010 እና 2013 ላይም 14 ሺሕ ብር የሚገመት ዕቃ ደንቦች ቀምተውኝ ነበር ሲሉ ያስታውሳሉ።
ግለሰቡ የተወሰደባቸውን ንብረት ለማስመለስ ለመንግሥት አካል ቅሬታ ማቅረባቸውን ገልጸው፣ ነገር ግን “ደንቦች ንብረቴን ወደ ግላቸው ነው ያስገቡት” ሲሉ ነው በምሬት የተናገሩት።

ምንም እንኳ የዳያስፖራው ወደ ኢትዮጵያ መምጣት አገሪቱ ከደረሰባት ወቅታዊ ፈተና እንድትወጣ ትልቅ ሚና ቢኖረውም፣ ወጣቶቹ ከሥራ መታገዳቸው ቤተሰባቸውን ጭምር ለችግር መዳረጉን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ርብቃ ወልደኪዳን የተባሉ እናት ልጆቻቸውን የሚያስተዳድሩት በሊስትሮ ሥራ በሚያገኙት ገቢ ሲሆን፣ ካሳለፍነው ታኅሳስ 16/2014 ጀምሮ በደንብ አስከባሪዎች ሥራ እንዳይሠሩ መከልከላቸውን ይናገራሉ።

“ኹለት ልጆችን የማስተምረውና ኹለት ሺሕ 500 ብር የቤት ኪራይ የምከፍለው በሊስትሮ ሥራ ተሰማርቼ በማገኘው ገቢ ነው። ሌላ ሥራ እንዳልሰራ ኹለት ጊዜ በኦፕራሲወን ስለወለድኩ አልችልም” የሚሉት ርብቃ፣ ከሥራ በመታገዳቸው ልጆቻቸው ችግር ላይ እንደሚወድቁ ነው የተናገሩት።

አያይዘውም፣ ልጄ ከትምህርት ቤት መልስ መጥቶ እማዬ ምግብ ስጭኝ ይለኛል፤ ምን ልስጠው? ምን ማድረግ አለብኝ? የሚሉት ርብቃ፣ መንግሥት ለገጠማቸው ችግር መፍትሔ እንዲሠጣቸው ጠይቀዋል።

ርብቃ የሊስትሮ ዕቃቸውን (ወንበር፣ ብሩሽ፣ ጣውላ) ደንቦች እንደቀሟቸው ገልጸው፣ ሌሎችም ተወስዶባቸዋል ብለዋል። የት እንግባ? ምን እንስራ? የሊስትሮ ዕቃችንን እንዴት ይጭኑብናል? የሚሉት ርብቃ፣ መንግሥት በአስቸኳይ መፍሔ ሊሰጠን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ወጣቶቹ ሥራ እንዲያቆሙ ከመደረጋቸውና ንብረታቸው ከመወረሱ በተጨማሪ፣ ንብረታችንን አትውሰዱብን ብለው የጠየቁት መታሠራቸው ተገልጿል።

“እዚህ መሥራት አትችሉም ብለው ዕቃችንን ቀምተውናል። ለምን ይወሠድብናል ብለው የሞገቱ ሦስት ጓደኞቼ ዕቃቸውም ተቀምቶ እነሱም ወደ እስር ቤት ተወስደዋል” የሚሉት ደግሞ ዙሪያሽ አብራር ናቸው። ዙሪያሽ አባታቸው በሕይወት የሌለ ልጆችን ሻይና ቡና በመሸጥ እያስተዳደሩ ስድስት ዓመት እንደቆዩ ገልጸው፣ አሁን ላይ ሥራ አቁሙ በመባላቸው ቅሬታ እንዳሳደረባቸው አንስተዋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ “ገና ለገና ዳያስፖራ ይመጣል ተብሎ እንዴት ድሆች ከስሥራቸው ይባረራሉ?” ሲሉ ጥያቄ ያነሳሉ። ወደሚመለከተው አካል ሒደን ቅሬታችን አቅርበን ነበር የሚሉት አስተያየት ሰጭዎቹ፣ እስከ 15 ቀን ድረስ ሥራ መጀመር እንደማይችሉና የተቀማ ንብረታቸንም እንደማይመለስ ተነግሮናል ብለዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 165 ታኅሣሥ 23 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!