የእለት ዜና

ጠላትም ከስሕተቱ እንደሚማር ልብ ይባል!

አንዴ ያደናቀፈ ድንጋይ መልሶ ካደናቀፈ ድንጋዩ እሱ ሳይሆን ተደናቃፊው እንደሚሆን እየተነገረን ያደግን ትውልዶች ነን። ከስሕተት መማር ከሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች እንሰሳትም የሚጠበቅ የተፈጥሮ ሕግ ነው። አንድ ጤነኛ አእምሮ ያለው ሰው ትክክል የሠራ ሲመስለውና ልፋቱ ወጤታማ ሲያደርገው የሠራውን ለመደጋገምና ኹሌ ውጤታማ ሆኖ ለመቀጠል እንደሚጥር ይታወቃል። በተቃራኒው አንዴ ያልሠራለትንና ያላዋጣውን መንገድ ደግሞ ማንም ሰው ላለመድገምና ለማሻሻል ይጥራል።

ከስሕተት ለመማርም ሆነ ስኬትን ለመደጋገም ያለፈውን ማስታወሱ ግዴታ መሆኑ ይታወቃል። የታሪክ ትምህርትም ሆነ የቅርብ ማስረጃን ማስቀመጥ ጥቅሙ ለሌላው መማሪያ እንዲሆን ብቻ ሳይሆን፣ ራሳችንም በጊዜ ቆይታ እንዳንዘነጋው ለማድረግ ነው። ስላለፈ ድርጊት የምንማርበት የትምህርት ዓይነት ታሪክ ብቻ ሳይሆን ኹሉም ዕውቀት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ማንኛውም ትምህርት ከእኛ ቀድመው በሙከራም ይሁን በፍልስፍና ያወቁት፣ ያስቀመጡልንን አስታውሰን ከእነሱ የምንማርበትና አስበልጠን የምንሠራበት ነው። በዚህ ረገድ ግለሰብም ሆነ ማኅበረሰብ ይህን የሚያደርግበት መደበኛም ሆነ ኢ-መደበኛ አሠራር ይኖረዋል።

ይህን ያህል ስለስሕተትና ትምህርት ያነሳነው አገራችንን ላለፉው ዓንድ አመት እያሳሰቧት ስላሉ ጉዳዮች ልናነሳ ወደን ነው። የኮቪድ ወረርሽኝ አንዱ የጋራ ሥጋታችን ቢሆንም፣ ኹሉንም ችግር ደርቦና አባብሶ ሊያዘልቅ የሚችለው የሠላሙ ጉዳይ ላይ ለማተኮር መርጠን ነው። አንድ ዓመት ከኹለት ወር የሆነው ጦርነት በሁኔታዎች እየተገለባበጠ ለብዙዎች ሞትና ሥቃይ፣ እንዲሁም ለአገር ሀብት ውድመት ምክንያት ሆኗል።

ከታሪክ የሚማር ሳይሆን ታሪክን እንደጦር መሣሪያ አረር ለመወራወሪያ በሚመርጥ ትውልድ ውስጥ ሆኖ፣ በዚህ አንድ ዓመት እንኳን ከተከሠተው እንማር ለማለት አዳጋች መሆኑን መመልከት ይቻላል። የተለያዩ የሽብር ተግባሮች መፈጸም ከጀመሩ ዓመታት ቢያስቆጥሩም፣ መማር ሳይቻል በመቆየቱ የጅምላ ፍጅት እንዲከሠት በር መክፈቱን አዲስ ማለዳ ታምናለች።

በግለሰብ ደረጃ እዚህም እዚያም ጥቃት ተፈጸመ እየተባለ ሲዘገብ፣ የአገርንም ሆነ የቡድንን ገጽታ እንዳያበላሽ በሚል ስንኩል ምክንያት አጥፊዎች የልብ ልብ እንዲያገኙ ተደርጓል። ይቅርታ ጠያቂ በሌለበት በተደጋጋሚ ይቅር ሲባሉ እንደፍርሃት የቆጠሩት ለመኖራቸው ማስረጃ የሚሆነውም ጥቃቱ አለን ለማለት ተብሎ ንጹኃን ላይ በመፈጸም አለማብቃቱ ነው። ከግለሰቦች ግድያ ወደባለሥልጣናት ግድያ አምርቶ የነበረው ጥቃት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጭምር ለመብላት የተሞከረበት እንደነበር የመስቀል አደባባዩ ታሪክ የመጨረሻው አስተማሪ መሆን ነበረበት። ነገር ግን፣ ይህም ክስተት አንድነትን ይሸረሽራል በሚል አንድነቱን ያልፈለገውን አካል በሠላም አቅፎ ለማቆየት ሲባል ከባድ መስዋዕትነት አስከፈለ።

ጥቂት በጥቂት እያለ ማኅበረሰብን በጅምላ ወደማጥቃት የተሸጋገረው የሥርዓት አልበኝነት ሒደት፣ ዕልባት ባለማግኘቱም በአንድ ጀንበር በርካቶች በታጣቂዎች ብቻ ሳይሆን፣ በተደራጁ ወጣቶችም ጭምር ሕይወታቸው እንዲቀጠፍ ሲደረግ ቆይቷል። ይህ ኹሉ የጭፍጨፋና የግድያ ዕርምጃ እየተሠማ አስቀድሞ ዕርምጃ የሚወስድ ባለመኖሩ፣ እራሱ ዕርምጃውን ሊወስድ የሚችለው ላይ ያልታሰበ ግን ሊታሰብ ይገባ የነበረ ጭፍጨፋ መፈጸሙ ለሕዝብ ይፋ ሆነ። በመከላከያ አባላት ላይ የተወሠደውና ጦርነት እንዲጀመር ምክንያት የሆነው ድንገት የተከሰተ ሳይሆን ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ የነበረና፣ ካለፈ ስሕተት መማር ባለመቻሉ የተከሠተ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ጦርነቱ የተጀመረ ሰሞን ከየትኛውም ወገን እንደአሁኑ ብዙዎች ሳያልቁ አለቀ ተቋጨ ተብሎ ነበር። ይህ ተስፋ ሰጪ ይሆናል ተብሎ የተነገረ ውጤት ግን ሕዝብ እንዲዘናጋ፣ ተሸናፊ የተባለ ወገን ደግሞ የበለጠ እንዲጠናከር ዕድል መስጠቱ ይነገራል። አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ቡድን ከሦስት ዓመታት በፊት ከሕዝብ ልቦና ውስጥ እንዲወጣ ተደርጎ ነበር። ይደግፉት የነበሩ ሳይቀር የሠራውን ጉድና ግፍ ሲሰሙ ድጋፋቸውን አቋርጠው ስለነበር ዕርምጃ ለመውሰድ አዳጋች እንዳልነበር ይገመታል።

ይህ ማምለጥ ያልነበረበት ዕድል ጥቅም ሳይሰጥ እንዳለፈው፣ ከዓመት በፊትም በተመሳሳይ ከማኅበረሰቡ ልቦና እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ መልሶ እንዲደገፍ ያደረገው ምን እንደነበር ሊጠና ይገባል። ከመንግሥት በኩል የተሠራ ስሕተት እንዳይደገም ብቻ ሳይሆን፣ ከተፋላሚ ወገን በኩል የተሠራውም መታየት ይኖርበታል። የሠሩትን ስሕተት ላይደግሙት እንደሚችሉም ከግምት ባስገባ መልኩ ነገሮች መታቀድ እንዳለባቸው ሊታሰብ ይገባል።

ትምህርት መወሰድ ያለበት ከወገን ጥሩና በጎ ጎን ብቻ አለመሆኑን አዲስ ማለዳ ማመላከት ትወዳለች። የራስን ደካማ ጎን ያለፍርሃት አውጣጥቶ በመለየት እንዳይደገም መሥራት ይገባል። ጥሩ ጎንም ለመሞጋገስ ሳይሆን ለማወቅ ሲባል በደንብ ተለይቶ ሊታወቅ ይገባል። ይህ በአጠቃላይ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን በየዘርፉ፣ ከውጊያ ስትራቴጂ አንስቶ እስከተዋጊዎች ብቃት የሚፈተሸበት ሊሆን ይገባል። ከዚህ በተጨማሪም፣ የሕዝብ ድጋፍን በተመለከተ ያለውን ዕውነታ ማጣራት፣ እንዲሁም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብን ከጎን ለማሰለፍ የነበረውን ሒደት በሥርዓቱ ቋንቋ ‹መገምገም› ያስፈልጋል።

በሌላ በኩል፣ ጠላት ተብሎ የተፈረጀው ወገን ብቃቱና ድክመቱ ምንድን ነው ብሎ ከራስ በበለጠ መገምገም ይጠበቃል። በምን በምን በልጧል? በምንስ ደካማ ነበር? በሚል ስኬቱን ከውድቀቱ እያገናዘቡ ከራስ ጋር አነጻጽሮ በማቀናጀት ማስተያየት ያስፈልጋል። ይህ ማለት ግን ነገሮች ባሉበት ይቀጥላሉ ብሎ ሳይሆን፣ ኹሌም ተሻሽሎ ይመጣል ብሎ ሳይንቁ በሚገባ በኹሉም መስክ ተዘጋጅቶ ለመጠበቅ ነው።

መከላከያ ሠራዊት ወደትግራይ ክልል እንዳይገባ የተወሰነው ከባለፈው ስሕተት በመማር ነው ተብሏል። ይህ ዕውነት ቢሆን እንኳን በአገር ድንበር ውስጥ እንደፈለገ የመንቀሳቀስ መብቱ በዘላቂነት ስለማይገደብ በምን መንገድ ችግሩን መወጣት እንደሚገባ ማሰብ እንጂ፣ ችግርን ሸሽቶም ሆነ ፈርቶ እንዲቀር ማድረግ አይኖርበትም። ቡድኑ አሸባሪነቱ በኹሉም አካባቢና ሕዝብ እንደመሆኑ ሊተውና እንደልቡ ሆኖ ሌላ የጥፋት ዕቅድ እንዲያወጣ ዕድል ሊሠጠው አይገባም። አሁንም ቢሆን ጥቃት መሠንዘሩን እንዳላቆመ የሚነገር በመሆኑ፣ ተዋጊውም ሆነ ሕብረተሰቡ ጦርነቱ ያበቃ እንዲመስለው መደረግ የለበትም። መንግሥት የተዋጊ ደም እንዲቀዘቅዝ ካደረገ፣ ደጋፊውም ሆነ ሕዝቡ እንዲዘናጋ ከሆነ ከባለፈው ስሕተት እንዳልተማረ አመላካች ነው።

በሌላ በኩል፣ ጦርነቱ በሰሜን ኢትዮጵያ ብቻ እንደተወሰነ ተደርጎ የሚካሄድ ዘገባም ሆነ ሪፖርት ሊስተካከል ይገባዋል። ከኦነግ ሸኔ ጋር የሚካሄደው ውጊያ እንደሰሜኑ ባይሆንም ሕዝብ በገፍ እያለቀበት መሆኑ ይታወቃል። ታጣቂ ቡድኑ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ንጹኃን መሞት የጀመሩት ከዓመታት በፊት ቢሆንም፣ ትኩረት ባለማግኘቱ አሁንም ድረስ አሳሳቢነቱ እንደቀጠለ ነው። ይባሱኑ ትልልቅ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ያለምንም እክል እንደመንግስት ባለስልጣናት በታጣቂዎቹ ሲጎበኙ መታየቱ የሚያስተላልፈው መልዕክት አደገኛ ስለሚሆን እንዲታሰብበት ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

በአጠቃላይ፣ አገራችን አሁንም ጦርነት ላይ እንደመሆኗ፣ ዋናው ውጊያ ገና ስላላለቀም መዘናጋት እንዳይኖር ሊታሰብበት ይገባል። ጊዜ መስጠት ለራስ ወገን ዝግጅት ብቻ ሳይሆን፣ ጠላት ተብሎ ለተፈረጀም ሊጠቅም እንደሚችል ታስቦ ወደ ዕርምጃ ለማምራት ፍጥነት ቢታከልበት የተሻለ ይሆናል። የድንገተኛነት ጥቅም እንዳለ ሁኖ ነገሮች ያሉበትንና የቆሙበትን ቦታ ለማጥናት ቀላል እንዳይሆን ተለዋዋጭ ሒደትንና ኃይልን መጠቀም ጠቃሚ ሊያደርግ እንደሚችል ከወታደራዊ ጠበብቱ በላይ የሚያውቅ አይኖርም። ነገር ግን፣ በመንግሥት ማዕቀፍ ሥር ያለ ተዋጊ ኃይል እንዳይንቀሳቀስ ተገድቦ ባለበት ሁኔታ፣ ሌላው እንደልቡ እንዳይሆንና ላለፉት ወራት የነበርንበት መከራ ውስጥ መልሶ እንዳከተን በጥንቃቄ ሊታሰብበት እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።


ቅጽ 4 ቁጥር 165 ታኅሣሥ 23 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!