የእለት ዜና

የአእምሮ ቁስለት – ያልታከምነው ሕመም!

ቴዎድሮስ ድልነሳው ይባላል። ‹የሳይኮሎጂ፣ የሕይወትና የፍልስፍና ተማሪ ነኝ› በማለት ራሱን ይገልጻል። ሦስቱም ትምህርቶችና ጉዳዮች ተምረው የማይጨርሷቸው የሕይወት ሙሉ ዘመን ትምህርቶች ናቸውና እርሱም ከእነዚህ ጉዳዮች ጋር ወዳጅነቱን አጽንቷል። እናም የመጀመሪያ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሳይኮሎጂ ትምህርት ያጠናቀቀ ሲሆን፣ አሁን ላይ ኹለተኛ ዲግሪውን በማማከር (Councelling) እየተማረ ይገኛል። ከዚህም በተጓዳኝ በማርኬቲንግ ተጨማሪ ዲግሪውን ይዟል።

ሥራው በቀጥታ ከሥነልቦና ጋር የተያያዘ ነው። ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ላይ በሚሠራው በአለኝታ ሆትላይን (6388) ላይ የምክክር ባለሞያ ነው። በዚህም የጭንቀትና ውጥረት እንዲሁም የድባቴ ምልክቶች ያሉባቸውና የተፈናቀሉ ሰዎችን ለማገዝ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቅሷል። በቋሚነት ደግሞ በእርቅ ማዕድ ሚድያና ኮምዩኒኬሽን አማካሪ ነው። በኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በላይ ባስቆጠረውና በሰሜኑ ክፍል ተቀስቅሶ ወደ አማራ እንዲሁም አፋር ክልሎች ያቀናው ጦርነት፣ ብዙ ምስቅልቅሎሽ መፍጠሩ ግልጽ ነው። ከሚታየው ቁሳዊ ውድመት፣ ከጠፋው የሰው ልጆች ሕይወት በተጓዳኝ የሥነልቦና እና አእምሮ ጤና ችግር መከሰቱ የሚጠበቅ ጉዳይ ሆኗል። ትራውማም ከዚህ ውስጥ ይገኛል። ለመሆኑ ትራውማ ምንድን ነው? እንደ አገርና እንደ ማኅበረሰብ በጋራ ትራውማ ውስጥ ልንገኝ እንደምንችልስ ምን ያህል እናውቃለን?
የሥነልቦና ባለሞያው ቴዎድሮስ ድልነሳው ከአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጋር በነበረው ቆይታ ትራውማን በተመለከተ ከትርጓሜው አንስቶ እንደ አገር የሚኖረውን ተጽእኖ በቀረቡለት ጥያቄዎች መካከል እንደሚከተለው አንስቷል፤ መልካም ቆይታ!

በግል ጥያቄ ልጀምር፤ በሥነልቦናና ማማከር ውስጥ የምትገኙ ባለሞያዎች ያለማቋረጥ የሰዎችን ሕመም ትሰማላችሁ። እንዴት ነው የምትችሉት ወይም ራሳችሁን እንዴት ነው የምታክሙት?
የሚረብሹ ነገሮች ይኖራሉ። ያለቀስንባቸው ታሪኮችም አሉ። ነገር ግን የምንቋቋምበት መንገድ አለ። ባለሞያዎች ስንገናኝም ከምናወራባቸው ነገሮች መካከል አንዱ ይህ ነው። ራሳችንን የምናዝናናበት ወይም ነገሮችን የምናይበት መንገድ፣ የፍልስፍና ዕይታችን ሁሉ ይወስነዋል። ሁላችንም ነገሮችን የምናይበትና ጉዳዮችን (ኬዞችን) የምንረዳበት የየራሳችን መንገድ አለን።

ለምሳሌ እኔ ከቤተሰብ ጋር መጫወት፣ ማሰላሰል፣ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ባለሞያዎችን ማናገር የመሳሰሉትን እጠቀማለሁ። በማማከሩም የሚከታተሉንና ‹አለኝታ ሆትላይ› እና ‹የእርቅ ማዕድ› ላይ አብረውን የሚሠሩ፤ በተጨማሪም ከውጪ የማማከር አገልግሎት የሚሰጡን አሉ። የሚከብዱንን ጉዳዮች/ኬዞች ለእነርሱ እናጋራለን።

ከዚህ በተጓዳኝ ቅርብ ጊዜ ተቋረጠ እንጂ በእርቅ ማዕድ በኹለት ሳምንት አንድ ቀን ማክሰኞ እለት መደበኛ ያልሆነ መድረክ ነበረን። በዚህም ምቹና ጥሩ አየር ባለበት ስፍራ ሰብሰብ ብለን የከበደንንና የሚረብሸንን ኬዝ የምንወያይበት፣ ሻይ ቡና እየጠጣን የምንነጋገርበት አውድ ነበር።

እኔ በግሌ የራሴ ሳይካትሪስትም አማካሪም አለኝ። እናም ስለራሳችን የአእምሮ ጤና ይገደናል። ምክንያቱም በአግባቡ ራሳችንን ካልተንከባከብን የሚያመጣውን ጥፋት እናውቀዋለን። ደግሞ ሙያዊ ሥነምግባርም አይደለም። የተስተካከለ ሁኔታ ውስጥ ካልሆንሽ፣ ዕይታሸ ከተዛባ፣ ሕመም ካለ፣ ያልተፈታ ጉዳይ ካለብሽ፤ ይህ ሁሉ እያለ ሌላ ሰው ማየት/ማከም አግባብ አይሆንም። በዚህ ዘርፍ ለረጅም ጊዜ የቆዩ ባለሞያዎችም ጤናቸውን መከታተልና መንከባከብ ግድ ይላቸዋል።

ትራውማ ራሱ ምን ማለት ነው? ከቃሉ ትርጓሜ ጀምሮ በአገርኛስ ምን ብለን እንጥራው?
ትራውማ ቃሉ ኢንግሊዘኛ ነው። በየጊዜው ሥነልቦናዊ ይዘት ያላቸው ቃላት ይፈጠራሉ። ይህንን ‹ሳይኮሎጂካል ኮንስትራክት› እንለዋለን። ይህን ቃል የምንጠቀምበት በአእምሮ ውስጥ ያለውን ሂደት ለመግለጽ ነው።
ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በኋላ ወታደሮች ሲመጡ ነው ሐሳቡ የተነሳው። በጊዜው ‹ሼል ሾክ› ነበር የሚሉት። ወታደሩ በልዩ ሁኔታ ደንግጦ ከሰው ሲርቅና አዲስ ባህሪ ሲያመጣ ተመልክተው ነው። ከዛ በኋላ ባለሞያዎቹ ምልክቱ የታየባቸውን ሰዎች አጠኑ፣ አእምሮ ላይ ያለውን ጉዳትና በየትኛው ክፍል ላይ ተጽእኖ እንደሚፈጥር ተመራመሩ።

ወደእኛ አገር ስንመጣ፣ ለብዙ ሰው አዲስ ነው። ትራውማ ሲባል እንደውም ሐኪሞች አካላዊ ጉዳትን ነው የሚረዱት። አዎን! ቁስል ትራውማ ነው። ግን እኛ የምንለው ‹ሳይኮሎጂካል› ወይም ‹ኢሞሽናል› ትራውማን ነው። ይህን የስሜት ቁስል፣ የመንፈስ ስብራት ልንለው እንችላለን። አሁን በብዛት የምንጠቀምበት የአእምሮ ቁስለት የሚለውን ቃል ነው።

ትራውማን፣ በአንድ ወይም በብዙ የሕይወት ክስተቶች፣ ከግለሰብ አቅም በላይ ለመቋቋም የከበደ ውጥረትን የሚፈጥሩ አጋጣሚዎች ሲኖሩና እነዛ አጋጣሚዎች አእምሮ ላይ በሚያስከትሉት ጉዳት የሚፈጠሩ የተለያዩ ምልክቶች ስብስብ የሆነ አእምሮአዊ ሕመም ልንለው እንችላለን።

እንዲሁም አእምሮአዊ ሂደት ነው። ያጋጠመን ነገር ቀጣይ የሕይወት መስመር ላይ በሚፈጥረው ተጽእኖ ይታያል። ለዛ ነው ሕክምና ሲጀመር ‹Post traumatic stress disorder› (PTSD) የሚባለው። ይህ ማለት ትራውማ ከተፈጠረ በኋላ የሚፈጠር የውጥረት፣ የስሜት መዛባት፣ የባህሪ መቀየር፣ የማስታወስ እክልና የመሳሰለው ጋር የሚገናኝ ነው።

ትራውማ ከሰው ሰውም ይለያያል። አንድ ሰው ትራውማ ሊሆን የሚችል ነገር ስለገጠመው የግድ ትራውማ ውስጥ ይገባል ወይም ምልክቶቹ ይኖሩታል ማለት አይደለም። አብዛኞቹ ሰዎች ውስጣቸው ራሱን የማገገም፣ የማዳን፣ ነገሮችን የመቋቋም አቅም አለው። ስለዚህ የተወሰኑ ሰዎች ምንአልባት በአማካይ 20 በመቶ የማይሆኑ ሰዎች ናቸው ትራውማ ውስጥ የሚሆኑት። ብዙ ሰው መኪና አደጋ ደርሶበት ከዛ ውስጥ የተወሰኑት ሰዎች ናቸው ድኅረ ትራውማ ምልክት የሚኖራቸው። ግን ጦርነትና ግጭት ሲኖር፣ ብዙ ሰው በዛ ውስጥ ሊሆንና በመቶኛ ሲታይ ከ30 በመቶ በላይ ሊሆን ይችላል።

ራስን ከትራውማ ቀድሞ መጠበቅ ወይም መከላከል ይችላል?
ትራውማ ክስተት ነው፤ የሕይወት ገጠመኝ። ስለዚህ ዋናው የመከላከያ መንገድ ሥነልቦናዊ ጫና ሊፈጥር የሚችል ማንኛውንም ነገር ከሕይወታችን ለማራቅ መሞከር ነው። ለምሳሌ የልጅነት ዘመን ትራውማ (Childhood Trauma) አንዱ ትልቅ ተጽእኖ የሚያሳድር ድግግሞሽ ያለው ትራውማ ነው። እንዲሀ ያሉ ትራውማዎች በጣም ስሜትን የመጉዳትና ዘላቂ ጉዳት የማምጣት ነገር አላቸው። እነዚህን ታድያ ልጆች እንዳይጎዱ በማድረግ፣ ቤተሰብ ልጅን ባለመሳደብና የመሳሰሉትን በማድረግ መከላከል ይቻላል።
እንደግለሰብም ስሜትንና ውስጥን ከሚጎዱ ነገሮች መጠበቅ፣ ራስን ሊረብሹ የሚችሉ የሕይወት ገጠመኞች እንዳይከሰቱ ማድረግና ከሕይወት ማራቅ ትልቁ መከላከያ ሊሆን ይችላል ብዬ አምናለሁ።

ግን የመቋቋም አቅም ከሰው ሰው ይለያያል። በማኅበረሰብ ውስጥ በማንኛውም ጊዜ ብዙ ሰው ትራውማ አይከሰትበትም። ግን እንደዛም ሆኖ ስለትራውማ ግንዛቤን ማስፋፋት አንዱ ትልቅ ነገር ነው። በጠቅላላ እንደ አገር ትምህርት ውስጥ ቢካተት ጥሩ ይሆናል።
ትራውማ የገነነ ፍርሃት ነው። ለምሳሌ ሰው ሲደነግጥ ይሮጣል፤ ያመልጣል ወይ ደንግጦ ፈዝዞ ይቆማል። አልያም ይጋፈጣል፤ ይደባደባል። ይህ ተፈጥሮአዊ ምላሽ ነው። ይህ የፍርሃት ምላሽ ግን ችግሩ ከተፈጠረ በኋላም አይሄድም/አይጠፋም። ውስጣችን ከዛ በኋላ ነገሮችን በተጠንቀቅ ነው የሚጠብቀው። የተለያየ የሐሳብና የስሜት መዛባት ይከሰታል። ግለሰቡም ነገሮችን ለመሸሽ፣ ላለማስታወስ ይሞክራል ወይም የተፈጠረውን ነገር ደጋግሞ ያስባል። አእምሮም አዲስ መረጃ መቀበል ይከብደዋል። ግንዛቤ ሲሰጥም እንዲህ ያሉ ነገሮች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ማሳወቅ ተገቢ ነው።

በሌላ በኩል ሕይወት ውስጥ ከባድ አጋጣሚ ከተፈጠረ በኋላ እንዴት እንቋቋመው የሚል ነው። ማለትም ትራውማን የተከተሉ ችግሮች ሳይፈጠሩ ወይም ‹Post traumatic stress disorder› ሙሉ ለሙሉ ሳይከሰት በፊት ማለት ነው። ቀድሞ እንዳልኩት አንደኛ ግንዛቤ መፍጠር ነው። ‹‹ይህ ነገር ሊከሰት ይችላል! ያሳለፋችሁት ነገር አእምሮ ላይ ተጽእኖ አለው! ንብረት መውደም፣ ሕይወት መጥፋት ወይም አካል ጉዳት ብቻ አይደለም፤ ስሜትን፣ ሐሳብና ባህሪንም ይቀይራል›› ብሎ ማሳወቅ ሌላው መንገድ ነው።

ከዚህ ጋር ተያይዞ፣ ማኅበረሰቡ እርስ በእርስ የሚያወራበት አውድ መፍጠር ነው። አብዛኛው ነገር በውይይት የሚፈታ ነው። በቡድን የማማከር መንገድ መጠቀምም ያግዛል። ባለሞያዎች ድኅረ ትራውማ ምልክቶች ከመታየታቸው በፊትም በዚህ መንገድ ሊያግዙ ይችላሉ።
ሌላ ‹ኢንተርቬንሽን› የምንለው ነው። ይህም ድኅረ ትራውማ ምልክቶች የታዩባቸውን ሰዎች ማገዝ ነው። ችግሩ ተፈጥሯል፤ ከዚህ በኋላ ምንአልበት ምልክቶቹ ከወራት በኋላ ይታያሉ። ያኔ አግባብ የሆነ የሥነልቦና ሕክምና ይሰጣል።
በጠቅላላው ግን ብዙ መከላከያ መንገዶች የሉም። ጭንቀትን ለመቋቋም የምናደርጋቸው ሁሉ በዚህ ሊካተቱ ይችላሉ። ግን እንዲህ ትራውማ እንዳይከሰት ይህን ይህን እናድርግ ተብለው የተጠቀሱ መከላከያ መንገዶች የሉም።

የትራውማ ዓይነቶች ምን ምን ናቸው? በጦርነት ወቅት የሚፈጠር ትራውማና በአዘቦቱ የሕይወት አጋጣሚ የሚፈጠረው ትራውማስ ልዩነት አላቸው?
ትራውማ ብዙ ዓይነት አለው። ሲከፈልም በምክንያቶቹ ነው። ብዙ ጊዜ ምልክቱ ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል። በጠቅላላው ታድያ ነጠላ ክስተት መነሻ የሚሆንባቸው (Single Cause Trauma) ትራውማዎች አሉ። ለምሳሌ አንድ ጊዜ ብቻ ሰው ሲሞት ዐይቶ ወይም አንድ ጊዜ ሰው መኪና ሲገጭ ዐይቶ ሊሆን ይችላል። አንድ ጊዜ ብቻ በተፈጠረ የሕይወት ገጠመኝ የተነሳ፤ ያ ጉዳይ ከውስጡ አይወጣም። መልሶ መላልሶ ያንን ማሰብ ወይም ያንን ለመርሳት በጣም መሞከር ይኖራል። ባህሪና ስሜት ይቀያየራል፣ በቂ እንቅልፍ መተኛት አይኖርም፣ ክስተቱ ድጋሚ ይፈጠር ይሆናል ብሎ ማሰብ አለ።

ሌላው እድገት ላይ ያሉ ትራውማዎች (Developmental Trauma) አሉ። እነዚህ የልጅነት ትውስታ ላይ ያሉ ናቸው። ብዙ ጊዜ ለሥነልቦና ባለሞያዎች ፈታኝ የሚሆኑት ልጅነት ላይ የተፈጠሩ ነገሮች ናቸው። ምክንያቱም ስብእና፣ ማንነትን የመረበሽ አቅም አላቸው። በዛም ላይ ተደጋግመው ነው የሚከሰቱት፤ ድግግሞሽ ይኖራቸዋል።

‹ኮምፕሌክስ ትራውማ› የምንለው የብዙ ትራውማዎች ስብሰብ ነው። ልጅነት ላይም ችግር ነበር፣ በሂደትም በተለያየ አጋጣሚና ክስተት በሕይወት ችግሮች ሊደራረቡ ይችላሉ። አንዳንዴ ሕይወቱ ሁሉ እጅግ አሳዛኝ/ትራጄዲ የሆነ ሰው አለ። እነዚህ ክስተቶች ውስብስብ ስለሚሆኑ ‹ኮምፕሌክስ› እንለዋለን።

‹ሰከንደሪ ትራውማ› የሚባለው ደግሞ ሌሎች ሰዎች ላይ ሲፈጠር ባየነው የሚከሰት ነው። ለምሳሌ አንዲት ሴት እህቷ በሌባ ስትደበደብ ዐይታ ሊሆን ይችላል፣ በዛ በተፈጠረው ነገር በጣም ልትረበሽ ትችላለች። ከዚህ በተጨማሪ በሥራ አጋጣሚ ብዙ ሰዎች ትራውማ ያጋጥማቸዋል።

ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ጠባሳ/ቁስልም (Generational Trauma) አለ። ይህ በታሪኮቻችን፣ አንዱ ለሌላው ባለው ጥላቻ ይተላለፋል። ብዙ መፍትሄ ያላገኙ ትራውማዎች አሉ ብዬ አምናለሁ።
ተያይዞ የተነሳው ጥያቄ በጦርነት ወቅት የሚከሰት ትራውማ፣ በሕይወት አጋጣሚ ከሚከሰተው ጋር ልዩነቱ ምንድን ነው የሚል ነው። የሕይወት አጋጠሚ ብዙ ጊዜ ግለሰብ ተኮር ነው፤ አንድ ሰው ላይ ነው የሚከሰተው። ብዙ ሰው በዚህ ገጠመኝ ላያልፍ ይችላል። በጦርነት ወቅት ግን ብዙ ሰዎች ናቸው የሚጎዱት፤ ቤተሰብ ነው የሚጎዳው። አባቶችና እናቶች ስለራሳቸው ላይሆን ይችላል የሚያስቡት፣ ስለልጆቻቸው ነው። ሰምተሸ ከሆነ፣ እናት ተደፍራ ‹ልጄን እንዴት ዐያታለሁ!› ብላ ራሷን አጠፋች የሚል ታሪክ በሰፊው ሲነገር ነበር።

በጦርነት ጊዜ ይህ ሐሳብ ግለሰብ ለብቻው የሚጋፈጠው አይደለም፣ እንደ ቤተሰብና እንደ ማኅበረሰብ እንጂ። የሚሰቃየው ሙሉ ቀበሌ፣ ሙሉ ወረዳ ወይ ሙሉ ከተማ ነው። ብዙ ሀብት፣ ንብረት ይወድማል። ገንዘብ ላይ ኪሳራ አለ፣ መፈናቀልም አለ። መኖሪያ ቦታ ይታጣል፤ ደኅንነት ይጠፋል። ይህ ሁኔታ ለሕክምና እንኳ አይመችም። ወደ ትራውማ ሕክምና የምንገባው ሰውየው በልቶ ጠግቦ ሲያድር ነው። አለበለዚያ ኪሳራ ነው የሚሆነው። መልሶ ይደነግጣል፤ ይጨነቃል።

እንዴት እሆናለሁ ብሎ ቢያስብም ትክክል ነው፤ መፍራትና ማሰብ አለበት። ተፈጥሮአዊ ምላሻችን ነው። የትራውማ ምልክት አለ ወይ ብሎ ለመለየት ተረጋግቶ ሲቀመጥ፣ ቤቱ ሲመለስ ወይ መጠለያ አግኝቶ ሲረጋጋ ነው ሕክምና የሚጀመረው። አለበለዚያ ትራውማ ሳይሆን ፈርቷል ወይም ደንግጧል ነው። ይህ ደግሞ ትክክል ነው። ያ ሰው መጀመሪያ ራሱን መጠበቅ አለበት። አገሩ እየተታኮሰ፣ እናቱ እየተደፈረች ወይም ወንድሙ ውጊያ ላይ ሄዶ፣ ለምን ያ ሰው ይፈራል፣ ይደነግጣል ልንል አንችልም። ምክንያቱም ክስተቱ በሂደት ላይ ያለ ነው።
ነገሩ የሚነሳው ጦርነቱ ካበቃ ከ6 ወር በኋላ አሁንም ቤቴ ፈረሰ አልፈረሰ፣ አሁንም ገብተው እናቴን ደበደቡ ወይም ገደሉ፣ አሁንም የሆነ ነገር ተፈጠረ ብሎ የሚደነግጥ ከሆነ ነው። ‹ፖስት ትራውማ› ምልክቱ ያኔ ነው የሚፈጠረው።

ጦርነት አንድ ነገር ላይ አይደለም ተጽእኖ የሚኖረው። ለምሳሌ ትግራይ፣ አፋርና አማራ ውስጥ ‹ትራውማታይዝድ› የሆኑ ሰዎች አሉ። ጦርነቱ ዓመት ስለዘለቀ ብዙ ክስተቶች ነው ያሉት። እያንዳንዱ ክስተትም ከበድ ያለ ነው። ስለዚህ ከላይ ያነሳነው ‹ኮምፕሌክስ ትራውማ› የመፈጠር እድሉ ሰፊ ነው።

አንድ ቤተሰብ ውስጥ እናት ልጇ ወይም ባሏ ወታደር ሆኖ ሄዶ ሊሞት ይችላል፤ ራሷ ልትደበደብ፣ ልጇ ልትደፈር፣ ቤቷ ሊቃጠል፣ ንብረቷ ሊዘረፍና እርሷ ተሰድዳ ሌላ ቦታ እየኖረች ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ውስብስብ ትራውማዎች ይፈጠራሉ። በዚህ ምክንያት የሚፈጠር የአእምሮ ቁስለት በኋላ ላይ ለመፍታትም ይከብዳል። በጣም ጠንከር ያለ የሥነልቦና ድጋፍ የሚያስፈልገው ይሆናል።

አንዳንድ ጉዳዮችን የአንድ ሰሞን አድርገን ካለፈ በኋላ መልሰን የመተው ልምድ አለን። እናም ዛሬ የምናነሳውን ይህን የትራውማ ጉዳይም ነገ ነገሮች ሲረጋጉ ላናነሳ እንችላለን። በዚህ የተነሳ ለመታከም እድል የማንሰጥ ከሆነ ጊዜ መድኃኒት ነው ማለት እንችላለን? በጊዜ ሂደት ይስተካከላል?
ይህን ቡራዩ ላይ ካጋጠመን ልምድ ጋር አያይዤ ብመልሰው ደስ ይለኛል። አሁን ቡራዩ ላይ ከትራውማ በኋላ የሚከሰቱ ምልክቶች ያላቸውን ሰዎች እየደገፍን ነው። እንደውም ቅዳሜ (ይህ የአዲስ ማለዳ ዕትም ለንባብ በቀረበበት እለት) ነው የመጨረሻው መዝጊያና የስንብት ዝግጅት የሚካሄደው።

ቡራዩ ላይ የተፈጠረው ችግር አሁን ሦስት ዓመት ሞላው። በአካባቢው ሰዎች ሲገደሉ የተመለከቱ፣ የተደበደቡ፣ ንብረት የተዘረፉ፣ ቤታቸው የፈረሰና የተቃጠለ፣ ተሰደው ሁለት ሳምንት ትምህርት ቤት መሬት ላይ ያደሩ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ዜና ላይ ስላላየናቸው አይጠፉም፤ የትም አልሄዱም፤ አሉ።

በእኔ እምነት ጊዜ ብቻውን መድኃኒት አይደለም። ሰዎች በተፈጠረው ነገር ላይ የሆነ መፍትሄ ሲፈጥሩ ነው የሚድኑት። ለምሳሌ በአካላዊ ሕመም ስናመጣው፣ ኩላሊቱ የታመመ ሰው ‹ቁጭ ብልና ብተኛበት እድናለሁ› ብሎ ይቀመጣል? አይቀመጥም። ብዙ ጊዜ ለአእምሮ ሕመሞች ነው ጊዜ እንስጠው፣ ይረፍ የሚባለው። ሰው የተለያየ ድምጽ ይሰማል፣ የሚረብሹ ሐሳቦች አሉት፣ ከማይታዩ ሰዎች ጋር ያወራል። እነዚህ የአእምሮ መታወክ ምልክቶች ናቸው። እነዚህ ምልክቶች ሲታዩ ቤት ይረፍ፣ ይቀመጥ እንላለን። ትራውማ ብቻ ሳይሆን እንዲህ ለአእምሮ ጤና ሕመሞች ወይ ፀበል ነው ወይ እረፍት ነው የሚባለው። በበኩሌ ይህ መድኃኒት ይሆናል ብዬ አላምንም።

ምክንያቱም የዛሬ ሦስት ዓመት እንደ ማኅበረሰብ ትተናቸው የነበሩ ሰዎች (የቡራዩ ነዋሪዎች) መካከል 104 ሰዎችን ነው ‹ስክሪን› አድርገን ለሥልጠና የጀመርነው። ከ77 በላይ የሚሆኑ ግለሰቦች ከትራውማ በኋላ የሚከሰትና ሕክምና የሚፈልጉ ምልክቶችን ሙሉ በሙሉ ያሳዩ ነበር። የመጨነቅ፣ የመደንገጥ፣ የመበርገግ ምልክቶች አሉ። እንቅልፍ አይተኙም፣ ከአሁን አሁን እናቴ ተመታች ይላሉ። ሰው ሲገደል ዐይተዋል፣ ተዘርፈዋል፣ ተደብድበዋል፣ ጓደኞችና እህት ወንድሞቻቸው ሞተዋል።

እነዚህ ሰዎች ላይ ምልክቱ አለ፤ ይህን እንደማስረጃ ነው ያነሳሁት። ቁስለቱ ይቆያል። አንድ ወይም ሁለትና ሦስት ዓመት ሳይሆን ዓመታት ይቆያል። እንደውም ትራውማው ከትውልድ ትውልድም እንደ ውርስ ሊተላለፍ ይችላል። ምክንያቱም ስጉ የሆነች፣ ፍርሃት ያላት እናት ምን ዓይነት ልጅ ወልዳ ታሳድጋለች? ፈሪ፣ ስጉ፣ ነገሮችን አጥብቦ የሚያይ፣ ራስን ከመከላከልና ሕይወትን በትግል ከመኖር ጋር ብቻ አያይዞ የሚኖር፣ ደስታን ማጣጣምና ፍቅር መስጠት የሚከብደው ሰው ሊፈጠር ይችላል። ይህ ነገር ጥፋቱ ቀላል አይደለም። ስለዚህ ሕክምና ያስፈልገዋል፤ መድኃኒቱ በስርዓት መሰጠት አለበት።

በእርግጥ አንዳንድ ሰው በጊዜ ሂደት ይማራል። ራሱን ያስተምረል፣ ሰዎች ይተዋወቃል፣ ግንኙነቶችን እንደ አዲስ ይገነባል። እናም ላጋጠመው ክስተት ትርጉም ይሰጠዋል። ከእኔ አልፌ ሰዎችን ላስተምር ብሎ ይነሳል። ይህን ድኅረ ትራውማ ለውጥ/እድገት (Post Trauma Growth) እንለዋለን። በክስተቱ አጋጣሚ ወድቆ መዘረር ሳይሆን ነጥሮ ሲነሳ ማለት ነው።

እናም አንድ ሰው ለሚገጥመው ነገር ወይም ለተፈጠረው ክስተት ትርጉም ከሰጠ፣ ሁሌም መደበኛ የሆነ ሕክምና (Proper Treatment) ላያስፈልገው ይችላል። የሰው ልጅ ያገግማል። አካባቢው ላይ ጥሩ ግንኙነት ካለ፣ ማኅበረሰባዊ ትስስሩ ጥሩ ከሆነ፣ ነገሮችን አስፍቶ ካየ ያገግማል።

በተለይ እኔ የታዘብኩትና እንዲህ ያለ አጋጣሚ ሲኖር፣ በጣም በትልቁ ጉዳት የሚደርስበት ለሰው ልጅ ያለን ዕይታ ነው። ‹የሰው ልጅ ዋጋ የለውም፣ ጎጂ ነው› የሚል ዕይታ ይፈጥራል። አንዱ የትራውማ ምልክትም ይህ ነው። ስለራስና ስለሌሎች ያለንን ዕይታ ያበላሻል። ይህም ደግሞ ስለሕይወት ያለንን ዕይታ ያጠለሻል።

ስለዚህ ከዚህም ለመዳንና ለማገገም እንችላለን፣ በጊዜ ሂደት። ግን ጊዜ ብቻ አይደለም፣ አብሮ የሆነ ነገር ስናደርግ ነው። የጊዜ ብዛት እኛ ብዙ ነገሮችን የማወቅ፣ ራሳችንን የማሻሻል እድል ይሰጠናል። በዚህ ከላይ ባነሳነው በቡራዩ የማውቃቸው ባለታሪኮች አሉ። የደረሰባቸው ነገር ውስጣቸውን እንደረበሸ ስላወቁ መፍትሄ ፍለጋ ብዙ ሰዎችን ያናገሩ፣ ብዙ ሰዎችን በማውራትና ሐሳቦችን በመሞከራቸው ራሳቸውን ያከሙ ሰዎች። በዚህ መንገድ ራሳቸውን አክመው የሚያድኑ ሰዎች አሉ። እንጂ ጊዜ ብቻውን ያድናል የሚል እምነት የለኝም።

ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ማኅበረሰብና እንደ አገር ትራውማ የተፈጠረበትና አሁንም ያልተላቀቀን አጋጣሚ ይኖር ይሆን?
እንደ አገር ብዙ ትኩረት ያልተሰጣቸውና በአግባብ ያልተነሱ ጉዳዮች አሉ። ትራውማ ሆነው የሚቀሩ ወይም የትራውማ ተጽእኖው ሳይታይ የሚቀሩ ታሪኮች፣ ብዙ ጊዜ ከድነን ስናስቀምጣቸው ነው። ይህን በእኛ አገር አውድ በመሶብ እንወክለዋለን። መሶብ ተገጥሞ ወይም ታፍኖ ሲቀመጥ ልክ ትራውማውን አውጥተን አልተነጋገርነውም ማለት ነው። መሶቡ ሲከፈት ስንል ደግሞ የሚወክለው ትራውማውን አውጥተን ስንነጋገርበት ነው።

የሚረብሸን ነገሩ አእምሮ ውስጥ የተቀመጠበት መንገድና የተሰጠው ትርጉም ነው። ለምሳሌ ዝብርቅርቅ ብሎ የተቀመጠ ሰነድ ወይም መዝገብ አለ፤ የሚረብሽ። እንደዛ አስቢው። ሐሳቡ ያንን መዝገብ እያወጡ በትክክል መደርደሪያ ላይ እንደመደርደር ነው። ስለዚህ በትክክል ያልተደረደሩ ታሪኮች አሉን፣ በትክክል ያልተቀመጡና ትርጉም ሰጥተን ያላስቀመጥናቸው ታሪኮች አሁንም አሉን።

ወደኋላ መለስ ብለን ካየን በጣም ልንርቅ እንችላለን። ግን የቅርቡን ስናወሳ፣ እናት አባቶቻችን ያለፉት የቀይ ሽብርን ታሪክ ልናነሳ እንችላለን። በቀይ ሽብር ብዙ ሰው ነው የተጎዳው፣ ብዙ ሰው ነው የሞተው። ትርጉም አልባ ሞትና የሰው ልጅ ስቃይ ነው። ያንን የተፈጠረውን ነገር በደንብ አውርቶ፣ የተፈጠረባቸውንና የገጠማቸውን ሰዎች በሰፊው ዐይቶ፣ ያ ነገር ለምን እንደተፈጠረም ለመረዳትና ለመነጋገር የሚያስችል አጋጣሚ አልተፈጠረም።

ለምሳሌ በቀይ ሽብር ቤተሰቡን ያጣ ሰው ‹እንዲህ ባደርግ ኖሮ!› እያለ እስከአሁን ይቆጫል፤ በወንድም እህቱ ሞት ሊያዝን ይችላል። ግን ያ ነገር ተፈጥሯል፣ ሆኗል፤ እና ለመቀበል መሞከር ነው፤ እንደግሰብም እንደ አገርም። ብዙ ጊዜ ሰዎች የሚያፍሩባቸውን ታሪኮች አያነሷቸውም። አገርም እንደዛው ነው። አስተውለሽ ከሆነ በእኛ አገርም ሆነ በውጪ አገር የሚያሳፍሩ ታሪኮች ተብለው ሳይነሱ ያልፋሉ። በዛ ውስጥ ግን የተጎዳ ሰው ለዛ ነገር ትርጉም አጥቶ ሲጨነቅ፣ ሲያብሰለስል ይኖራል።

በማኅበረሰብ ደረጃ የተከሰቱትን መለስ ብለን ስናስታውስ፣ ጦርነቶቻችንን ማየት ይቻላል። ጥያቄው ምን አደረግን ነው፣ ከጦርነት ለተመለሱ ወታደሮች ምን አደረግን? ከቀይ ሽብር ጀምሮ፣ ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትና ሌሎችም ውጊያዎችን ብናይ፣ እንደ አገር ትልቅ ትራውማ ሊፈጥር የሚችል ክስተት ነው። ምን ተሠራ የሚለው አሁንም መታየት አለበት።

ተጽእኖ ምንድን ነው ስንል፣ አንድ ማኅበረሰብ ለዘመናት ትራውማ ውስጥ ሲያልፍ፣ አእምሮአዊ የአስተሳሰብ ሂደቱ ጤናማ አይሆንም። ለምሳሌ ትግራይ አካባቢ ያለውን ነገር ብናይ፣ ትግራይ አካባቢ ለዘመናት ጦርነት ነበር። ሕወሓት/ኢሕአዴግ ሥልጣን ከመያዙ ዘመናት በፊት ጀምሮ ጦርነት ነበር። ስለዚህ ማኅበረሰቡ ትራውማ ውስጥ ነበር ማለት ነው።

በትራውማ ውስጥ የሚያልፍ ማኅበረሰብ ምን ዓይነት ባህሪ ይኖረዋል ስንል፣ አንደኛ መጋፈጥ ወይም ማምለጥ (fight or flight) የሚል መንፈስ ላይ ነው የሚሆነው። ከልጅነት ጀምሮ ጦርነት ውስጥ ያለፈ ሰው፣ ለፍርሃት የሚሰጠው ምላሽ (Fear Response) ፈጣን ነው። ኹለተኛ በዛ ምክንያት አስቦና አገናዝቦ የመመለስ አቅሙ ዝቅ ይላል። በዚህ መልክ ነገሮችን ካደረገ በኋላ የሚያስብ ሰው ይፈጠራል። እንዲህ ያሉ ሰዎች በብዛት ሲፈጠሩ፣ በቀላሉ የመመራት እድል ይኖራቸዋል። የእኔ የሚሉትና የሚያምኑት ሰው ካለ፣ ያንን ሰው ያለምንም ምክንያት ሊያምኑትና ሊከተሉት ይችላሉ።

በአሁን ጊዜ ይህ አካል ለእነርሱ ሕወሓት ነው። ድርጅቱን ያምኑታል፣ ለዘመናት የእኛን ጥቅም ይጠብቃል ብለው ነው የተቀበሉት። ስለዚህ ያለምንም ምክንያት ተከትለዉታል። ይህ ደግሞ የሚፈጥረውን ተጽእኖ እያየነው ነው። አሁንም ዐይተን አልጨረስንም ብዬ አስባለሁ።
ትራውማው በግለሰብ ደረጃ ይሁን እንጂ፣ አንድ ሙሉ ብሔር ወይም ማኅበረሰብ ለከፍተኛ ትራውማ ምልክቶች ሊጋለጥ ይችላል። ይህ እንደ አገር የሚያመጣው ተጽእኖ የማያገናዝብ፣ ፈሪ፣ ጭንቀት ውስጥ ያለ፣ ተረጋግቶ የማይኖር፣ ፍቅር ለመስጠት የሚከብደው፣ ራስ ወዳድ ሕዝብ የመፈጠር እድሉ ከፍ ይላል።

በተለይ በልጅነታቸው በዚህ ውስጥ ያለፉ ሰዎች፣ ሲያድጉ ከበድ ያለ ነገር ውስጥ ይገባሉ። እና ጉዳዩን ቸል ማለት አያስፈልግም። በማኅበረሰብ ደረጃ ብዙ ችግሮችን አሳልፈናል። በየዘመናት ከተከሰቱ ድርቆች መጀመር እችላለን። በተለይ ጦርነቶቻችን፣ የድርቅ ረሃብ አደጋዎች አሁንም ድረስ የዘለቀ የፈጠሩት ተጽእኖ አለ ብዬ አምናለሁ።

ምን መደረግ አለበት ታድያ? ምን እናድርግ?
ትልቁ ነገር ይህ ነው፣ ምን እናድርግ የሚለው። እንደ አገር መንግሥት ይህን ያድርግ እገሌ ያንን ያድርግ ማለት ቀላል ነው። በተግባር ወርዶ ማድረጉ ነው ከባዱ። እኔ በቅርብ የማውቀውን ባነሳ፣ የኢትዮጵያ ሥነልቦና ማኅበር አለ። በዛ አብዛኞቹ ጓደኞቼ የሥነልበና ባለሞያዎች እንደ ሐኪሞች ሁሉ ጦርነት ወደተከሰተባቸው አካባቢዎች እየተሰማሩ ነው። ግን ቢሆንም እጥረቱ አለ። የሚያስፈልገው የሰው መጠን እና ያለው የሰው ኃይል መካከል ከፍተኛ ልዩነት አለ። ግን ከምንም ትንሽ ይሻላል ነው። እና ሄደው ችግር ወስጥ ያሉ ሰዎችን ለማገዝ እየሞከሩ ነው።

አስቀድሞ እንዳነሳነው መጀመሪያ መቀመጫዬን እንዳለችው ዝንጀሮ፣ መጀመሪያ ግን ሰዎቹ ማረፍ፣ ጥሩ እንቅልፍ ማግኘት፣ በልተው ማደር አለባቸው። እፎይ ብለው ሲያርፉ ነው ሕክምናው የሚጀምረው። አሁን ብዙ ቦታዎች ተለቀዋል እየተባለ ነውና ብዙ ሰዎች ወደቤታቸው የመመለስ እድል ይኖራቸዋል። ግን አሁንም ተመልሰን እንወረራለን የሚል ፍርሀት እንዳለ ነው። በተወሰነ መልኩ አግባብነት ያለው ስጋት ነው፣ ችግሩ ከተፈጠረ ብዙ ያልራቀ ስለሆነና ነገሮች ሰክነው ስላልጨረሱ። እናም የደፈረሰው እስኪጠራ አሁንም ነገሮች ያስቸግራሉ።
ሁኔታው ከተረጋጋ በኋላ ወደ ሥነልቦና ስንመለስ ሰዎች እርስ በእርስ የተፈጠሩ ነገሮችን የሚያወሩበት ጥሩ አውድ መሠራት አለበት ባይ ነኝ። በቅርብ እንደሰማሁት የሥነልቦና ጉዳይ በሰፊው መነሳትና በትክክል ምን ተፈጠረ፣ ምን ሆነ የሚለው ነገር መጣራት አለበት ተብሏል። ከዛ በኋላ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ዘዴዎችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል።

የቡድን ምክክር ሞዴል ለምሳሌ በጣም በቀላል ብዙ ሰዎችን ማከም የሚቻልበት ነው። በልምድ የሚሠለጥኑ ሰዎችን በየቦታው እያሰማራን መሥራት እንችላለን። ስለዚህ ኢትዮጵያዊ፣ ቡድን ዐቀፍ እና ማኅበረሰብ ላይ መሠረት ያደረገ መንገድ ያስፈልገናል። ምክንያቱም በግል አንጨርሰውም። በአገር ያለው የሥነልቦና ባለሞያ እንዳለ ተሰማርቶ፣ ከጎረቤትም ጭምር ባለሞያ ተበድረን ብንሞክር እንኳ አያልቅም። ደግሞ ከግለሰብም የተሻለ መፍትሄ ለመፈለግ በቡድን ይሻላል። የምክክርና ድጋፍ ቡድን መፍጠሩ ጥሩ ነው፤ እንደ ማኅበርም ይሁን እንደ ቡና ጠጡ የሚቀጥል ማኅበር እየፈጠርን ማለፍ መቻል አለብን።

ከዛ ደግሞ ቢቻል ሳይንሳዊ ቢሆን ይመረጣል። ጥናት የተጠናበት ነገር ከሆነ፣ እንዴት እና ምን እንደሚሠራ ይታወቃል። እኛ አገር ብዙ ጥናቶች የሉንም። ይህ ካልሆነም ያለውን ዘዴ መተግበር ይጠቅማል። ማኅበረሰቡን አውቀንና ተረድተን ነው ማገዝ ያለብን፣ ዘዴውን በየሁኔታው ማደስ ያስፈልጋል። ብዝኀ ባህል ተኮር፣ ጾታ ተኮር የሆነ ዘዴ ነው መጠቀም ያለብን። ከዚህ አንጻር ብዙ መሠራት አለበት።

መንግሥትም ትኩረት መስጠት አለበት። ይመስለኛል አሁን ሳይወዱ በግድ ትኩረት ለማድረግ እየሞከሩ ነው። ግን አሁንም ስብሰባዎች ላይ የሚነሳውና ሰዉ ትኩረት ያደረገው፤ መነቃቃት አለ፣ የአገር ፍቅር ስሜቱና አንድነቱ ጨምሯል የሚለውን ነው። አንድነታችን ቢጨምርም ሰዋዊ ኪሳራ/ወጪ (Human Cost) አለው። ሰዋዊና ከሰው ጋር የሚያገናኝ ሙያ ውስጥ እንዳለ ሰው፣ ይህን ሰዋዊ ኪሳራ ማየት መቻል አለብን እላለሁ። ትልቅ ኪሳራ እንደሆነ ማመን መቻል አለብን።

ይህ ለሰው ያለንን ዕይታ ያሳያል። ያለምንም ርህራሄ በየቤቱ እየገባ ሴትን መድፈር፣ ወንዶችን መንገድ ላይ እየረሸነ መግደልና የመሳሰሉ ነገሮች እንዲሁም ሙሉ ከተማ ሕዝብን ገድሎ በትልቅ ጉዳጓድ ቆፍሮ መቅበር የመሳሰሉ ዓይነት ነገሮች ሥነልቦናዊ ኪሳራ ናቸው። ይህን መረዳት ያስፈልጋል። እና እንደ ሕመም ታይቶ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሕክምና ያስፈልገዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 165 ታኅሣሥ 23 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!