የእለት ዜና

“ጉንፋናማው ኮሮና”

ሠሞኑን በዓለም ላይ በከፍተኛ ፍጥነት እየተሠራጨ ያለው ኦሚክሮን የተሠኘው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ፣ አገራችን ገብቶ በሚያሳስብ መልኩ እየተሥፋፋ እንደሚገኝ ይታወቃል። እስከዛሬ ከታወቁት የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች ከሰው ወደ ሰው በመተላለፍ ፍጥነቱ በጣም አስጊ እየሆነ የመጣው ይህ ዝርያ፣ ከቁጥጥር ውጭ የወጣ እስኪመስል ድረስ ያልገባበት ቤት እንደሌለ እየተነገረ ይገኛል።

ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ጤና ጣቢያዎችን በተመርማሪዎች ብዛት ማጨናነቅ ጀመረው ወረርሽኙ፣ በሳምንት የጊዜ ልዩነት ውስጥ በስፋት ለመሠራጨቱ ልዩ የሆነ ጥናትን የሚጠይቅ አይደለም። ከአንድ ሳምንት በፊት ጥቂት ቁጥር ብቻ ያስተናግዱ የነበሩ በአዲስ አበባ በየወረዳው ያሉ ጤና ጣቢያዎች ሥራ እየበዛባቸው ከመሔዱ የተነሳ የመጣውን ኹሉ ለማስተናገድ አልተቻላቸውም። ከተመርማሪው ቁጥር መጨመር አኳያ ለኹሉም ምርመራ አካሒዶ ለመሸኘት ጤና ጣቢያዎቹ ባለመቻላቸው፣ በአንዳንድ ቦታዎች ሕብረተሰቡ ነገ ወይም ከሰዓት እየተባለ በመሸኘቱ ተሠላችቶ ምርመራ ከማድረግ ማመንታቱንም ለመታዘብ ይቻላል። በአንዳንዶቹ ጤና ጣቢያዎች አንዴ ተመርምሮ ቫይረሱ የተገኘበት (ፖዘቲቭ የተባለ) ከቀናት ቆይታ በኋላ ድጋሚ ተመርምሮ ነጻ ይሁን አይሁን ማረጋገጥ እንደማይችልም ጭምር እየተነገረ ነው።

በየመንገዱ፣ በየትራንስፖርቱ፣ እንዲሁም በተለያዩ መሰብሰቢያ ቦታዎች ጉንፋን ነው በሚል በርካቶች ሳይመረመሩ ራሳቸውን እያስታመሙ ይገኛሉ። በበርካታ መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞች እንዳመማቸው እያወቁ ከሥራ ገበታ ላለመቅረት ሥራ ቦታቸው ላይ ታመው ስለሚሠሩ ለሌላው ቫይረሱን በማስተላለፍ ረገድ ችግር እየሆኑ እንደሆኑ የሚናገሩ አሉ። በትምህርት ቤትም በበሽታው ተይዘው እያወቁ ለሌላ ተማሪ የሚያስተላልፉ መኖራቸውን የሚናገሩም አሉ። ከዚህ ቀደም የነበረ ክልከላና ጥንቃቄ እጅግ ስለላላ የዘንድሮውን ይህን ወረርሽኝ በተቻለ መጠን መቀነስ አለመቻሉ በምክንያትነት ይነሳል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ክልከላዎችን ተግባራዊ እያስደረገ ያለው ይህ የአዲሱ ዝርያ ማዕበል በአገራችን ተገቢውን ትኩረት እንዳልተሠጠው መታዘብ ይቻላል። እንደከዚህ ቀደሞቹ ለከፋ ጉዳት አይዳርግም፤ ሆስፒታልም አያስገባም፤ በሚል ብዙዎች ለበሽታው መጋለጣቸው ይታያል። መደረግ ከሚገባቸው ጥንቃቄዎች ጀምሮ ክልከላዎችና መመሪያዎች ተግባራዊ ባለመደረጋቸው በሚያስደነገጥ መልክ ዝርያው እየተስፋፋ ነው። በየመሥሪያ ቤቱ ታሞ የሚውል ሰው እጅግ እየተበራከተ በመምጣቱ ሒደቱ በዚህ ከቀጠለ ምን እንደሚሆን ብዙዎችን ሥጋት ላይ እየጣለ ነው።

አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ያን ያህል ትኩረት እንዳያገኝ ካደረጉት መካካል ቀላል ነው በሚል የተሠራጨው መረጃ እንደሆነ የሚናገሩ በርካቶች ናቸው። ከጉንፋን አይለይም በሚልም ሕብረተሰቡ እንደጉንፋን አንዲያየውና ጥንቃቄዎችን ከማድረግ እንዲዘናጋ ማድረጉ ይታመናል። በእርግጥ ኦሚክሮን አደገኛነቱ እንደከዚህ ቀደሞቹ አለመሆኑ ቢታወቅም፣ በዘላቂነት የሚያመጣው ችግር ግን ከጊዜው አጭርነት አኳያ አልታወቀም። ክትባትን የመቋቋም አቅሙ ከፍተኛ ከመሆኑ ባሻገር፣ እስካሁን የተመረቱ ክትባቶች ሥርጭቱን የማስቆም ብቃት እንደሌላቸው ባለፈው ሳምንት ዕትማችን አስነብበናችኋል።

አዲሱ የኦሚክሮን ቫይረስን ተመርምሮ ለማወቅና ለመጠንቀቅ አዳጋች ካደረገው ተግባር መካከል የሚያሳየው ምልክት ከጉንፋን ጋር መመሳሰሉ አንዱ ነው። ከጉንፋን ጋር ተቀራራቢ ምልክት በማሳየቱ አብዛኞች እንዲዘናጉ በማድረግ እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል የሚሉ የሕክምና ባለሙያዎችና ተቋማት፣ አስተያየታቸውንና ምክራቸውን ከመለገስ አልተቆጠቡም።

የቅዱስ ፓውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የሕክምና ኮሌጅ የሠሞኑ ጉንፋን በሚል ስለወረርሽኙ ይፋ ያደረገው መረጃ ነበር። “የሠሞኑ ጉንፋን ለየት የሚያደርገው ከፍተኛ ትኩሳት እና ጠንከር ያለ ሳል አለው” በማለት ከዚህ በታች የሠፈሩትም ምልክቶች እንደሚታዩበት አስፍሯል። ብርድ ብርድ ማለት፣ የመገጣጠሚያ፣ የጀርባና የጡንቻ ሕመም፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ኃይለኛ ራስ ምታት፣ እንዲሁም ፍዝዝ ማለት በአንድ ታማሚ ላይ ከሚታዩ ምልቶች መካከል በግንባር ቀደምትንት እንደሚጠቀሱ ተነግሯል።

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰር እና የሕፃናት ስፔሻሊስት ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ፋሲል መንበረ መንስዔው ምን ሊሆን ይችላል? በሚል ኃሳባቸውን አስፍረዋል። ጉንፋን ዋና መንስዔዎቹ በትንፋሽ፣ በሳል እና በማስነጠስ የሚተላለፉ ቫይረሶች ናቸው በማለት፣ ምሳሌ ያሉዋቸው ኮሮና ቫይረስ ፣ራይኖ ቫይረስ፣ ኢንፍሉዌንዛ አዴኖ ቫይረስ እና የመሳሰሉትን ነው።

የሠሞኑ ጉንፋን ኮሮና ይሁን አይሁን የሚታወቀው በምርመራ ብቻ ነው የሚሉት ሐኪሙ፣ መደረግ ያለበት ያሉትን ዘርዝረዋል። የመከላከያ መንገዶቹን መተግበር፣ ኹሌም አፍና አፍንጫን መሸፈን፣ የእጅ እና አካል ንክኪ መቀነስ፣ ሰው የሚሰበብበት ቦታ አለመገኘት፣ ሲያስሉ እና ሲያስነጥሱ አፍ እና አፍንጫን በክንድ/በጨርቅ መሸፈን፣ መንግሥት በነጻ ያቀረበውን የኮሮና ክትባትን መውሰድ ይመከራል ብለዋል።

ሕክምናውን ወይም መደረግ ያለበትን ለአዋቂዎችና ለሕፃናት ብለው የከፋፈሉት ሲሆን፣ ለልጆች እና ሕፃናት ቤት ዉስጥ መደረግ ያለበት ሕክምና ያሉት የሚከተለውን ነው።

ለብ ያለ ዉኃ ውስጥ ትንሽ ጨው አድርጎ አፍንጫቸው ቀዳዳ ዉስጥ 2 ጠብታ ማድረግ፤ በመቀጠል የአፍንጫ ቀዳዳዎችን በመምጠጫ ማጽዳት፤ ትኩሳትን የሚቀንስ መድኃኒት መጠቀም፤ ትኩስ ትኩስ ነገሮችን ማጠጣት፤ ተጨማሪ ምግቦችን በደንብ መመገብ፤ የሕፃናቱን ክፍል በደንብ ማፅዳትና ማናፈስ፤ ቤቱን በውኃ እንፋሎት ማጠን፤ ንፍጥ እና ትኩሳት በጣም አስፈላጊ ፈሳሾችን እና ንጥረ ነገሮችን ይዘው ስለሚወጡ ተጨማሪ ፈሳሽ ነገሮችን መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።

ለታዳጊ ሕፃናት እና ለአዋቂዎች ደግሞ ከላይ ከተዘረዘሩት በተጨማሪ ራስን በአንድ ክፍል ማግለል፤ ትኩስ ፈሳሽ ነገሮችን ደጋግሞ መውሰድ፤ ነጭ ሽንኩርት፣ ማር እና ዝንጅብል መጠቀም፤ በቂ ዕረፍት ማድረግ፤ የትኩሳት እና ራስ ምታት ማስታገሻ መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል። እነዚህን መፍትሔዎች ተጠቅማችሁ ምንም ለውጥ ከሌለው እና ሳሉ የመባስ፣ ትኩሳቱ የመጨመር ባህሪ ካለው ወይም ትንፋሽ የማጠር ምልክት በሕፃንም ሆነ በአዋቂ ላይ ከተከሰተ በአፋጣኝ ሆስፒታል መሔድ ያስፈልጋል ሲሉ ሐኪሙ መክረዋል።

የኦሚክሮን በጎ ጎን
ኦሚክሮን ከተከሠተ ወዲህ በርካታ ጉዳቶችን በኢኮኖሚውም ሆነ በሰዎች ላይ ቢያስከትልም በጎ ነገር ይዞ ሳይመጣ አይቀርም ሲሉ የደቡብ አፍሪካ ሳይንቲስቶች ተናገሩ ብሎ መረጃውን ‹ኤቢሲ ኒውስ› አስነብቧል። በአዲሱ ዝርያ የተያዙ ሰዎች አደገኛ ከሆነው ዴልታ ከተባለው ዝርያ የመያዝ ዕድላቸው ዝቅተኛ መሆኑን በምርምር አውቀናል ተብሏል። በቅድመ ምርመራ ሙከራ የታወቀውን ማረጋገጥ ከተቻለ በጊዜ ሒደት ዴልታ ዝርያን ኦሚክሮን እንደሚተካው ማወቅ ይቻላል ተብሏል። ጥናቱ የተካሄደው በአነስተኛ የናሙና ቁጥር እንደመሆኑ በሰፊው መጠናት አለበት የተባለ ሲሆን፣ ይህም ቢሆን ግን ተስፋ ሰጪ ነው ተብሎለታል።

በሌላ በኩል፣ ኹሉንም ዓይነት ዝርያ መከላከል የሚያስችል ክትባት ለማምረት ጫፍ መደረሱም ተነግሯል። ዝርያውም ሆነ ባህሪውን በሚቀያይርበት ወቅት የማይለዋወጥን ባህሪ በመለየት ክትባቱ በዘላቂነት እንዲያገለግል ሆኖ ለማዘጋጀት መቃረባቸውን ሳይንቲስቶች መናገራቸውን ‹ጆርናል ኔቸር› ላይ ወጥቷል ሲል ‹ዘ ዊክ› አስነብቧል።

ኦሚክሮን የተሰኘው አዲሱ ዝርያ በአንድ ሳምንት ብቻ ሥርጭቱ በ11 በመቶ መጨመር መቻሉን የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ አድርጓል። በባለፈው አንድ ሳምንት ብቻ 4.9 ሚሊዮን ሰዎች የተያዙ ሲሆን፣ 44 ሺሕ ሰዎችም ሞተዋል። ይህም የሞት መጠን ካለፈው ሳምንት ጋር ሲነጻጸር በ4 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል። በፈረንጆቹ የበዓል ሰሞን የታየው ጭማሪ በአንዳንድ አገራት ክብረ ወሠን (ሪከርድ) የሠበረ መሆኑ ተጠቁሟል። በአፍሪካ የጭማሪ መጠኑ 7 በመቶ ቢሆንም፣ የሟቾች አሃዝ ግን በ72 በመቶ መጨመሩ ተመዝግቧል። ይህ እውነታ ወደሆስፒታል የሚገቡ ቁጥር ከመቀነሱ አኳያ የተሠጠው መረጃ ጋር ቢጋጭም፣ ጊዜው ገና ስለሆነ እርግጠኛ ሆኖ መናገር እንደማያስችል ተነግሯል። ሕብረተሰቡ ቀላል ነው በሚል ከመጠንቀቅ መቆጠብ እንደሌለበት የተመከረ ሲሆን፣ የሚደረጉ ገደቦችና ክልከላዎች ተፈጻሚ መሆን ይገባቸዋልም ተብሏል።

በአፍሪካ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት እንደአዲስ አገርሽቶ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ እንደሚገኝ ይታወቃል። በያዝነው ሳምንት በበሽታው የተያዙት አፍሪካውያን ቁጥር ከ9.5 ሚሊዮን ያለፈ ሲሆን፣ በኢትዮጵያም ከ400 ሺሕ በላይ ሆኗል።


ቅጽ 4 ቁጥር 165 ታኅሣሥ 23 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!