የእለት ዜና

ጉንፋን ወይስ ኮሮና?

ባለፈው ሳምንት ውስጥ ጉንፋን መሠል ሕመም ያልደረሰበት ቤተሰብ የለም ማለት እስኪቻል ድረስ ብዙዎች ታመው ታይተዋል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ በርካቶች ምን መሆኑ ባልታወቀ፣ ነገር ግን ጉንፋን ሳይሆን አይቀርም በተባለ ከባድ በሽታ ተጠቅተው እንደነበር ይታወቃል፡፡
ኦሚክሮን የሚባለው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ እንደጉንፋን መሠል ምልክት ያሳያል እየተባለ ቢነገርም ያደመጠ ጥቂት ነበር፡፡ ወረርሽኙ በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ፍጥነት የተስፋፋ በመሆኑ እኛም አገር በተመሳሳይ ለመስፋፋት ጊዜ አልወሰደበትም ነበር፡፡ ይህ ቢሆንም ግን በሕብረተሰቡ ዘንድ የነበረው አመለካከት ግን ግራ አጋቢ ነበር፡፡

ከ10 ቀናት ገደማ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ በሥፋት መሠራጨት የጀመረው ጉንፋን መሠል በሽታ፣ በቀናት ውስጥ ብዙ ለውጦችን አስተናግዶ ነበር፡፡ ለክፉ የማይሰጥ አነስተኛ የሆኑ ጉንፋን መሠል ምልክቶችን ብቻ በማሳየቱ የተናቀ ሆኖ ነበር የሚሉ አሉ፡፡ በተቃራኒው ኮሮና ቢሆን ከባድ ይሆን ነበር በሚል፣ የያዛቸው ጉንፋን ሳይሆን እንደማይቀር በልበሙሉነት የሚናገሩም ነበሩ፡፡

የጤና ባለሙያዎች ከባድ ጉንፋን መጥቷል እያሉ ከማስጠንቀቅ ውጭ፣ ምልክቱ የዚህ የዚህ ነው ብለው በእርግጠኛነት ከመናገር ተቆጥበው ነበር፡፡ ይልቁንም፣ በምርመራ ካልሆነ ሊታወቅ ስለማይችል ጥንቃቄ ከማድረግ አትቆጠቡ ቢሉም፣ ተግባራዊ ሲሆን አልታየም፡፡ ሕብረተሰቡ ይበልጥ መጠንቀቅ ሲኖርበት በሽታውን ንቆ መዘናጋት ይታይበት እንደነበር የሚናገሩ አሉ፡፡ አሁንም ድረስ ተመርምረው የሚያረጋግጡት ካልሆኑ በቀር፣ ምልክቱ የታየባቸው “ኃይለኛ ጉንፋን” ይዞኛል በማለት በሽታውን ሲያቃልሉት ይሠማል፡፡

ኮቪድ ሊሆንበት የሚችልበት አጋጣሚ ሠፊ ሆኖ ሳለ፣ ሕብረተሰቡ እንዲህ የተዘናጋበትና መንግሥትም ቸል ያለበት ምክንያት ብዙዎችን ግራ እንዳጋባ ተነግሯል፡፡ በፊት በፊት ጉንፋን የያዘው ሰው እንኳን ሌላውን ላለማስያዝ ጥንቃቄ ሲያደርግ ይታይ ነበር፡፡ የታመመ በሥራም ሆነ ከትምህርት ገበታው ላይ ሌላውን እንዳያሲዝ ሲባል እንዲቀር ይደረግ እንደነበር ይታወሳል፡፡ አሁን ግን ሕብረተሰቡ ተሰላችቶ ይሁን የባሰ መከራን ሲሰማ በመቆየቱ ጉዳዩን አናንቆት፣ ብዙዎች በወረርሽኙ ተጠቅተዋል ሲሉ አንዳንዶች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡

በኮሮና መያዝ እንደበፊቱ አስደንጋጭ መሆኑ የቀረበት ጊዜ ላይ መድረሳችንን የሚያመላክቱ አስተያየቶችም ተሠንዝረዋል፡፡ እኛም ተቀላቀልን የሚሉ፣ ተይዘን ተርፈናል የሚሉ በርካታ ሐሳቦች የተነሱ ሲሆን፣ ስለውሸባም ሆነ ተለይቶ ስለመቆየቱ የተናረ አለመኖሩን እያነሱ የተቹም ነበሩ፡፡

አብዛኛው ሰው ከነቤተሰቡ ተይዞ ቢቆይም፣ ጠያቂ የማይኖርበት ጊዜ እንደመሆኑ እቤቱ ሆኖ የሚጠብቅ አልነበረም ተብሏል፡፡ እንደየሰው አመለካከት የሚለያይ ቢሆንም፣ በአብዛኛው የነበረው አመለካከት ጥንቃቄ የጎደለውና በሽታውን ያስፋፋ እንደነበር ይታመናል፡፡ ፍርሃትን ያስወገደ በሥነልቦና ረገድ ጥንካሬ የታየበት ወቅት እንደነበረም የሚያወሱ ነበሩ፡፡


ቅጽ 4 ቁጥር 165 ታኅሣሥ 23 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!